አዲሱ ዓመት Part 2

ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን መውቀስም አለ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “እንዴት ብሎ? ርግጥ ነው ብዙውን ጊዜ ሠራተኞቻችንን እንወቅሳለን፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ብሎ መውቀስስ እንደምን ያለ ነው?” አዎ! የሚሰክር ወይም የሚሰርቅ ሠራተኛ ወይም ጓደኛ ብናይ ወይም ከዘመዳችን አንዱ ወደ ተውኔት ቤት፣ ወይም ለነፍሱ ምንም ረብሕ ወደማያገኝበት ሥፍራ ሲሮጥ፣ በከንቱ ሲምል፣ የሐሰት ምስክርነትን ሲሰጥ፣ ወይም ሲዋሽ፣ ወይም ሲቈጣ ብናየው ዠርባችንን ብንሰጠውና ብንገሥፀው ወቀሳችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡

ዳግመኛም አንድ ሰው ቢበድለን፣ ርሱ ራሱ የሠራውንም ጥፋት በእኛ ቢያመካኝ ስለ እግዚአብሔር ብለን ይቅር ልንለው ይገባል፡፡ ብዙዎቻችን ግን ለጓደኞቻችን፣ ለሠራተኞቻችን የዚኽ ተቃራኒውን ነው የምናደርገው፡፡ ጓደኞቻችን ወይም ሠራተኞቻችን ቢበድሉን እናንባርቃለን፤ ይቅርታ የሌለው ፍርድም እንፈርድባቸዋለን፡፡ እኛው ራሳችን እግዚአብሔርን በገቢር ስንሰድብ አንድም ስናሰድብ ወይም ነፍሳችንን ስንጐዳ ግን እንደበደልን አይሰማንም፡፡ ይኽ ግን በአዲሱ ዓመት ልናስተካክለው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ዕለት ዕለትም ልንለማመደው ይገባል፡፡ የበደሉንን ሰዎችስ ወዳጅ ማድረግ ይገባልን? አዎ! ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል የበደሉንን ሰዎች ወዳጅ ማድረግ ይገባናል፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል ሰውን ጠላት ማድረግስ? አዎ! ይቻላል፡፡ ለመኾኑ ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን ወዳጅና ጠላት ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?ሰውን ወዳጅ ማድረግ ሲባል ያንን ሰው ከገንዘባችን፣ ከማዕዳችን እንዲካፈል በእኛም እንዲደገፍ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ አንድን ሰው እውነተኛ ወዳጅ ኾንነው አንድም አደረግነው የሚባለው ነፍሱን እንዳይጐዳ ብንገሥፀውና ብንመክረው፣ ቢበድል (በበደሉ የሚጐዳው ርሱ ራሱ ነውና) እንደ ጠላት ሳይኾን እንደ ወዳጅ ቀረብ ብለን የሚረባውን ብንነግረው፣ ከወደቀበት የኀጢአት አረንቋ እንዲነሣ ብናደርግ ለዚኽም ዘወትር በጸሎት ብንረዳውና ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርብ ብናደርግ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ ሰውን ጠላት ማድረግም ይፈቀዳል፡፡ ይኽን ከዚኽ በፊት ያላከናወንነው ከኾነም ከአኹኑ አዲሱ ዓመት መዠመር እንችላለን፤ ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ሰውን ጠላት ማድረግ፡፡ ለምሳሌ አንድ ጋጠ ወጥ፣ ክፋትን የተመላ፣ ንግግሩ (ትምህርቱ) ኹሉ በምንፍቅና መርዝ የተለወሰ፣ ዘወትር ነፍሳችንን የሚያውካትና የሚጐዳት ሰው ካለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ቀኝ ዓይንኅም ብታሰናክልኽ አውጥተኽ ከአንተ ጣላት” እንዳለ /ማቴ.5፡29/ እነዚኽን ሰዎች መራቅ ጠላትም ማድረግ ይፈቀዳል፡፡ እነዚኽ ሰዎች ቀኝ ዓይን ተብለው መጠቀሳቸውም ምንም እንኳን እንደ ዓይናችን የምናያቸው ወዳጆቻችን ቢኾኑም ነፍሳችንን የሚጐዷት ከኾነ ከእኛ ዘንድ ልናርቃቸው ይገባል፡፡

ንግግራችንም ዝምታችንም ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ብሎ መናገር ሲባል ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ከአንድ ጓደኛችን ጋር ቁጭ ብለን ስንጨዋወት “ማን ሥልጣን ላይ ወጣ፣ ማን ወረደ፣ ማን አለፈ፣ ማን ምን ክብር አገኘ” እያልን ከምንጨዋወት ይልቅ ስለ ነገረ ሃይማኖት፣ ስለ ገሃነመ እሳት፣ ስለ መንግሥተ ሰማያት ብንጨዋወት መናገሩ ጥቅምን ይሰጣል፡፡ ነፍሳችንን በማይጠቅማት ነገር አላስጨነቅናትምና፡፡ ይኽን ዓይነት ኅብረት ባንተወዉም አንጐዳንም፡፡ በኋለኛው ቀን ላይ ይኽ ኹሉ ማድረጋችን አንዳች ጥቅም ይሰጠናልና፡፡ ስለዚኽ ለነፍሳችን አንዳች የሚጠቅም ነገር በሌለው ስብስብ መካከል መቀመጡና ማውራቱ ለእኛ ጉዳት እንጂ ረብሕ የለውም፡፡ የዚኽ ስብስብ መንፈስ ለውጦ ስለ ነገረ እግዚአብሔር ማውራቱም ስለ እግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል፡፡ ዝምታችንም ለእግዚአብሔር ክብር መኾን ይገቧል፡፡ ምንም ሳንበድለው ክፉ ለሚያደርግብን ሰው፣ ሳንወቅሰውና ሳናንጐራጉርበት በትዕግሥት ዝም ብንል ዝምታችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡

ማመስገንና መገሠፅ፣ ወይም ከቤት ውስጥ መኾንና አለመኾን ወይም መናገርና አርምሞ ብቻ አይደለም፤ ኀዘናችንም ደስታችንም ስለ እግዚአብሔር ክብር ሊኾን ይገባል፡፡ አንድ ወንድማችን ኀጢአት እየሠራ ብናየው ወይም እኛው ራሳችን በበደል ስንወድቅ ብናለቅስና ብናዝን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የኾነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፣ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና” /2ኛ ቆሮ.7፡10/ ኀዘናችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡ አንድ ወንድማችን መልካም ነገርን ስላገኘ ልክ ለእኛ እንደተደረገ አድርገን እግዚአብሔርን ብናመሰግንም ደስታችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡ ከዚኽ ደስታም እጅግ ብዙ ጥቅምን እናገኝበታለን፤ እንኪያስ ይኽን በአዲሱ ዓመት እንለማመደዋ!!!

በወንድሙ ደስታ መደሰት ሲገባው ወንድሙ ስለ ተጠቀመ ብቻ በቅናት ከሚቃጠል ሰው በላይ አሳዛኝ ሰው ማን አለ? እስኪ ንገሩኝ! በወንድሙ ደስታ በማዘኑ የእግዚአብሔርን ፍርድ በራሱ ላይ በመጨመር በነፍስ በሥጋ ከሚጐዳ ቅናተኛ ሰው በላይ የሚያሳዝን ፍጥረት ማን አለ? ወንድማችን ስለ ተጠቀመ ብናመሰግን ወይም ብንደሰት፣ ወንድማችን ስለ ተጐዳም ብናዝን እና ብናለቅስ ይኽንንም ለእግዚአብሔር ክብር ብለን ብናደርገው አንጠቀምምን?

ፀጉርን ከማሳጠር በላይ ምን ትንሽ ነገር አለ? ነገር ግን ይኽም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ሴቶች በፀጉራቸው ምክንያት ወንዶች የሚሰነካከሉ ከኾነና ይኽንን ዐውቀው ባይቈርጡትም ወንዶቹ በማይሰናከሉበት መንገድ ቢሸላለሙት፣ ደካማ ወንድሞቻቸው በማይሰናከሉበት መንገድ ራሳቸውን ቢያጌጡ ይኽን ለእግዚአብሔር ክብር አድርገዉታልና ሹመት ሽልማታቸው የበዛ ነው፡፡ የክፉ ምኞት ፍላጻን ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል አስቀርተዉታልና ዋጋቸው በሰማያት ዘንድ ታላቅ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ አንዲት ኩባያ ውኃን የሰጠ ሰው ርስት መንግሥተ ሰማያትን የሚያገኝ ከኾነ፥ የምናደረግው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር ብለን የምናከናውነው ከኾነማ ሹመት ሽልማታችን እንደምን አይበዛ?

ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ መሔድም አለመሔድም አለ፡፡ ምን ማለት ነው? ወደ ክፋት የማንሔድ ከኾነ፣ የቆነጃጅትን ውበት በማድነቅ ስም ልቡናችን በምኞት መንፈስ የማንጠመድ ከኾነ፣ አንዲት ቆንጆ ልጅ በፊታችን ብናይና እንደምታሰናክለን ተረድተን ዓይናችንን ከርሷ ዞር የምናደርግ ከኾነ ውበትን ለእግዚአብሔር ክብር አዋልነው ይባላል፡፡

አለባበሳችንም ቢኾን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እጂግ ውድ የኾኑ አልባሳትን ባንለብስ፣ ሰውነታችንን እጂግ ሳናራቁት፣ በአጭሩ ሰውን የማያሰናክል አለባበስን ብንከተል አለባበሳችን ስለ እግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል (በነገራችን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአጸደ ሥጋ በዚኽ ዘመን ቢኖርና ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ የምናየውን የእኅቶቻችንን አለባበስ ቢያይ ምን ብሎ ሊገሥፅ እንደሚችል አስቡት፡፡ ምክንያቱም እኅቶቻችን በስመ ዘመናዊነት የሚለብሱት እጅግ በጣም አጭር ቀሚስ ወይም ሱሪ የብዙ ደካማ ወንዶችን ልብ በዝሙት ይፈታተናልና)፡፡

የምጫማው ጫማ እንኳን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለሚያደርጉት ጫማ ከዓቅም በላይ ሲጨናነቁ አያለኹ፡፡ ፊታቸውን በተለያየ መንገድ ለማሸብረቅ የሚወዱትን ያኽል ስለ ጫማቸው ውበት እጂግ የሚጨነቁ ሰዎችን አያለኹ፡፡ ምንም እንኳን ይኽ እንደ ትንሽ ነገር አድርገን ብናስበውም ዘወትር በወንዶችም በሴቶችም የምናየው ነገር ነው፡፡ ስለዚኽ ጫማችን እንኳን ሳይቀር ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል ማለት ነው፡፡ በአካሔዳችንም፣ በአለባበሳችንም፣ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት እንደሚቻል ሲናገር ጠቢቡ ምን እንደሚለን እስኪ እናድምጠው፡- “ከአለባበሱና ከአካሔዱ ከአሳሳቁም የተነሣ የሰው ጠባዩ ይታወቃል” /ሲራክ 19፡27/፡፡ ስለዚኽ በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ የምናደርገው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር የምናደርገው ከኾነ አሕዛቡም፣ መናፍቁም፣ ፈላስፋውም አስቦበት ሳይኾን እንዲኹ በእኛ ይደነቃል፡፡

ትዳራችን እንኳን ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ መኝታችን (በትዳር ውስጥ የሚደረገው ሩካቤ) ንጹሕ ማድረግ፣ ትዳርን ለብር ወይም ሌላ ምድራዊ ነገርን ለማግኘት ሳይኾን ነፍሳችንን ለማዳን፣ እግዚአብሔርን ለማግኘት የሚደረግ ከኾነ ለእግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል፡፡ የትዳር አጋራችንን ከዘለዓለማዊ ሕይወት አንጻር እንጂ ከውበት፣ ከሃብት፣ ወይም ከሌላ ጊዜአዊ ጥቅም አንጻር የማንመለከት ከኾነ ትዳራችን ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው ይባላል፡፡ በአዲሱ ዓመት ይኽን ልንለማመድ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር የሚወዳችኁ እናንተም የሚምትወዱት ልጆቼ! ይኽን ኹሉ በዝርዝር የምነግራችኁ ለምን ይመስላችኋል? ይኽን ኹሉ በዝርዝር መናገሬ በዘዴ ኹላችንም የምናደርገውን ማናቸውም እንቅስቃሴያችን ለእግዚአብሔር ክብር እናደርገው ዘንድ ስለምሻ ነው፡፡ በባሕር የሚነግዱ ነጋዴዎች ንብረታቸውን ወደ ከተማ ዳር መልሕቅ ካመጡ በኋላ መዠመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር በቀጥታ ወደ ገበያ ሥፍራ መሔድ አይደለም፡፡ ወደ ገበያ ሥፍራ ከመሔዳቸው በፊት ስለ ትርፋቸው ያስባሉ እንጂ፡፡ እኛም በምናደርገው ኹሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ የምናገኘውን ጥቅም ማሰብ አለብን፡፡

ከእናንተ መካከል፡- “ኹሉንም ነገር ስለ እግዚአብሔር ክብር ብሎ ማድረግ ግን የሚቻል አይደለም” የሚል ፈጽሞ አይገኝ፡፡ ጫማችንን ብንጫማ፣ ፀጕራችንን ብናስተካክል፣ ልብሳችንን ብንለብስ፣ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ብንጓጓዝ፣ የቁመናችን አኳኋን፣ ንግግራችን፣ ስብስባችን፣ መግባታችን፣ መውጣታችን፣ መገሠፃችን፣ ማመስገናችን፣ መውቀሳችን፣ አለ መውቀሳችን፣ ሰውን ወዳጅ ወይም ጠላት ማድረጋችን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ የሚቻለን ከኾነ እኛ ከፈቀድን ለእግዚአብሔር ክብር ተብሎ የማይደረግ ምን ይቀራል? የወኅኒ አለቃ ከመኾን ምን የከፋ አለ? የወኅኒ ጠባቂ ሕይወት እጅግ የምትከብድ አትመስልምን? ነገር ግን የልቡና ፈቃደኝነት ካለን የወኅኒ አለቃም ተኩኖ ኹሉንም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻላል፡፡ እስረኞችን ማዳን ይቻላል፡፡ ያለ አግባብ የታሰሩትን መንከባከብ ይቻላል፡፡ ንጹሐን ሰዎችን አለ አግባብ ከሚያሰቃዩ ክፉዎች ጋር አለመተባበር ይቻላል፡፡ እስረኞችን እንደ አለቃ ሳይኾን እንደ ወንድምና እኅት ማገልገል ይቻላል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሃይማኖት የመለሰውን የወኅኒ ጠባቂ ስንመለከት እንደዚኽ ዓይነት ሰው ነበር /ሐዋ.16፡25-40/፡፡ ስለዚኽ በአዲሱ ዓመት ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር እናድርገው ብንል ይቻለናል ማለት ነው፡፡

እስኪ ንገሩኝ! ከነፍሰ ግድያ በላይ ምን የከፋ ነገር አለ? ነገር ግን በዚኽ የነፍስ ግድያ እንኳን የጽድቅን ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡ አትደንግጡ! ግድያ እንኳን ለእግዚአብሔር ክብር ተብሎ ሊደረግ ይችላል፡፡ ከእናንተ መካከል “ነፍሰ ገዳይ ሰው እንዴት አድርጐ ነው በነፍሰ ገዳይነቱ ጽድቅ ሠራ ተብሎ ሊነገርለት የሚችለው?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ የተመዘገበውን አንድ ታሪክ አንሥቼ ልነግራችኁ እወዳለኹ፡፡ አንድ ጊዜ ምድያማውያን ከእስራኤል ጋር ጦርነት ይገጥሙ ዘንድ እግዚአብሔርን ለቁጣ ቀስቅሰዉት ነበር፡፡ በጦርነቱም ልዕልናቸውን በማሳየት፥ የእግዚአብሔርን መልካም ፈቃድ ለማስቀረት አስበው ሴቶቻቸውን በማሳመር በድንኳኑ ፊት ቆመው ነበር፡፡ በዚኽም እስራኤላውያንን በዝሙት እስከ መሳብና ለጣዖት እንዲሰግዱ እስከ ማታለል ደርሰው ነበር፡፡ ይኽም ብቻ ሳይኾን እስራኤላውያን ሃይማኖት የለሽ እንዲኾኑ ፈልገው ነበር፡፡ ፊንሐስ ግን ይኽን ባየ ጊዜ በእጁ ሰይፍ ይዞ ኹለት ሲያመነዝሩ የተገኙትን ሰዎች ሆዳቸውን በሰይፍ ወግቶ ገድሏቸዋል፡፡ በዚኽም የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደኾነ አረጋግጧል፡፡ ፊንሐስ ያደረገው ነገር ሰውን መግደል ነው፡፡ የዚኹ ግድያ ዓላማ ግን እስራኤልን በጠቅላላ ማዳን ነበር፡፡ በመኾኑም ከግድያ እንኳን ጽድቅን ማፍራት ይቻላል ማለት ነው /ዘኅ.25/፡፡

ፊንሐስ በፈጸመው ግድያ እጁ አልረከሰም፡፡ ይልቁንም ያ “ነፍሰ ገዳዩ” ፊንሐስ እስራኤላውያንን ከዝሙት ጠንቅ ጠብቆ ንጹሐን አደረጋቸው እንጂ፡፡ ፊንሐስ እነዚያ ኹለቱንም የገደላቸው ጠልቷቸው አልነበረም፤ የተቀሩትን የእስራኤል ሰዎች ለማዳን እንጂ፡፡ ኹለቱንም ብቻ በመግደል እልፍ እስራኤልን በነፍስ በሥጋ ከመሞት ለመታደግ እንጂ፡፡ ይኸውም ሐኪሞች እንደሚያደርጉት ነው፡፡ ሐኪሞች አንድ በቁስል መበስበስ (በጋንግሪን) የተጠቃን የሰውነት ክፍል ቈርጠው ቢያስወግዱት የተቀረውን ሰውነት ለማዳን ነው፡፡ ፊንሐስም ያደረገው እንደዚኹ ነው፡፡ መዝሙረኛው ክቡር ዳዊት ይኽንን በተመለከተ ሲናገር፡- “ፊንሐስም ተነሥቶ ፈረደባቸው፤ ቸነፈሩም ተወ፡፡ ያም እስከ ዘለዓለም ለልጅ ልጅ ጽድቅ ኾኖ ተቈጠረለት” ብሏል /መዝ.106፡30-31/፡፡ ፊንሐስ ያደረገው ነገር ትክክል ነው ተብሎ እስከ ዘለዓለም ሲነገርለት ይኖራል፡፡ (በነገራችን ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አልመለስ ያሉትን መናፍቃን ከቤተ ክርስቲያን አውግዛ የምትለያቸው ቀሪውን ምእመን እንዳይበክሉ እንጂ ጠልታቸው አይደለም፡፡ በቅርብ ጊዜ የተወገዙት የተሐድሶ አራማጆች የተወገዙትም ከዚኹ አንጻር ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ውግዘቱ ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ ነው፡፡)

ዳግመኛም አንድ ሰው በመጸለዩ ምክንያት እግዚአብሔርን አስቈጥቷል፡፡ ምክንያቱም ጸሎቱ ለእግዚአብሔር ክብር የተደረገ አልነበረም፤ ርሱም ፈሪሳዊው ነው /ሉቃ.18/፡፡ ፊንሐስ ግድያን ስለ ፈጸመ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አገኘ፤ ፈሪሳዊው ደግሞ በአንጻሩ ስለ ጸለየ እግዚአብሔርን አስቈጣ፡፡ ስለዚኽ ማናቸውም የምናደርገው ነገር ምንም መንፈሳዊ ቢኾንም ለእግዚአብሔር ክብር እስካልተደረገ ድረስ ትርፉ ጉዳት ነው፡፡ ሥጋዊ ሥራም ብንሠራ ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ ሰውን ከመግደል በላይ እጅግ ክፉና ዘግናኝ ነገር ምን አለ? ነገር ግን ይኽ ለእግዚአብሔር ክብር የሚደረግ ከኾነ ከዚኹ ግድያ እንኳን ጽድቅን ማግኘት ይቻላል፡፡

እንግዲኽ ከነፍሰ ገዳይ እንኳን እንዲኽ ዓይነት ጽድቅ ከተገኘ እያንዳንዱ ግብራችን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ አይቻለንም እንደምን ማለት ይቻለናል? የልቡና ፈቃደኝነት ካለን ግን ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ ብንገዛም ብንሸጥም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ ከአግባብ በላይ ዋጋን በመጨመር ሸማቹን ማኅበረ ሰብ ባለ ማስቸገር ንግዳችን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል፡፡ አንድን ዕቃ በመደበቅ (አኹን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ኹኔታ ዘይትንና ስኳርን ማለት እንችላለን) አለአግባብ ለመክበር ብለን የምንደብቀው ከኾነ “እኽልን የሚያስቀር ሰው በሕዝቡ ዘንድ የተረገመ ነው” እንደተባለ /ምሳ.11፡26/ ንግዳችን እግዚአብሔር የከበረበት ንግድ አይደለም፡፡

ከእናንተ መካከል፡- “አባታችን! አንድ ምሳሌ መስለኽ ልታስተምረን ስትችል ወደዚኽ ኹሉ ዝርዝር መግባት ለምን አስፈለገኽ?” የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ አንድ የሕንፃ ተቋራጭ አንድን ሕንፃ ለመገንባት የሚዠምረው መሠረት በመጣል ነው፡፡ ከዚያም ደረጃ በደረጃ የተቀረውን የሕንፃን ክፍል ይገነባል፡፡ በመጨረሻም ሕንፃው እጅግ የሚያምር እንዲኾን የቅብ (finishing) ሥራን ይሠራል፡፡ እኛም ይኽን ኹሉ በዝርዝር ማየታችን በክፍል 2 ትምህርታችን፡- ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለኽ? ነፍስኅ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋኽን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለኽ? አስቀድመኽ ቤቱን (ነፍስኽን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመኽ ለነፍስኽ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለኽ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለኽ አስብ እንጂ እንዲኹ ከአኹን (ከአዲሱ ዓመት) በኋላ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለኁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲኽ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚኹ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ /1ኛ ቆሮ.10፡31/፤” የሚለውን መሠረት ይዘን ነው፡፡

ከእንግዲኽ ወዲኽ ብንጸልይም፣ ብንጦምም፣ ብንገሥፅም፣ ይቅር ብንልም፣ ብናመሰግንም፣ ብንወቅስም፣ ብንገባም፣ ብንወጣም፣ ብንሸጥም፣ ብንገዛም፣ ብንናገርም፣ ዝም ብንልም፣ ማናቸውን ነገር ብናደርግ ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርጋቸው ይገባናል፡፡ ይኽን ያልዠመርን ካለንም አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ እንዠምረው፡፡ ለእግዚአብሔር ክብር የማናደርገው ከኾነ ግን አንሥራው፤ በማኅበር መካከል እንድንናገር ብንገፋፋም አንናገር፡፡ የትም ብንሔድ ይኽቺውን የሐዋርያው ቃል በልቡናችን ጽላት ጽፈን ይዘናት እንሒድ፡፡ ርሷም (ኃይለ ቃልዋ) የምናደርገው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር እንድናደርገው ታሳስበናለች፡፡ የምናደርገው ኹሉ ለእግዚአብሔር ክብር የምናደርገው ከኾነም “ያከበሩኝን አከብራለኹ” ብሏልና /1ኛ ሳሙ.2፡30/ ከሰው እጅ ሳይኾን ከራሱ ከክብር ባለቤት ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ በዚኽም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ክብርን እንጐናጸፋለን፡፡ እንኪያስ ከእንግዲኽ ወዲኽ ክብር የክብር ክብር፣ አምልኮና ውዳሴ ለአምላካችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ይገባዋልና በቃል ብቻ ሳይኾን በገቢር ጽድቅ በምግባር በትሩፋት ዘወትር እናክብረው፡፡ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ አሜን!!!

መልካም አዲስ ዓመት ይኹንላችኁ፤ ይኹንልን!!!