ሕግና ሥርዓት - በሐበሻ አሜሪካ

አሜሪካ ውስጥ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ስዘዋወር ከአስተባባሪዎቹ የምሰማው ተመሳሳይ ሮሮ አለ፡፡ ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው ሕንጻ እስኪያገኙ ድረስ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተከራይተው ይገለገላሉ፡፡ የራሳቸው ሕንጸ ያላቸውም ቢሆኑ ከአሜሪካዊው ማኅበረሰብ ጋር ይጎራበታሉ፡፡ በሰንበት ቅዳሴና የንግሥ በዓላት በሚከበሩባቸው ቀናት በመኪና ማቆሚያ፣ በድምጽ፣ በአካባቢው በብዛት በመገኘትና በጽዳት ጉዳዮች አብያተ ክርስቲያናቱ ካሉባቸው መንደሮች ነዋሪዎች ጋር ይገናኛሉ፡፡

እነዚህ ግንኙነቶች ግን ብዙውን ጊዜ ሰላማውያን አይሆኑም፡፡ አልፎ አልፎ ችግሩ ከሌሎች ወገን ቢመነጭም ዋናው ችግር ግን ከራሳችን የሚመጣ መሆኑን አስተባባሪዎችም ማኅበረሰቡም ያምኑበታል፡፡ ፈታኙ ነገር ችግሩን ለማስተካከል አለመቻሉ ነው፡፡ ‹ከተማ የጉርብትና ሥርዓት ነው› የሚለውን የከተሞችን አንዱን መርሕ በጉልሕ ለማየት ከሚቻልባው ሀገሮች አንዷ በሆነችው አሜሪካ የመንደርተኞች ሕጎችና ባሕሎች ጥብቅ ናቸው፡፡ በተለይም ግለሰባዊ ኑሮን መሠረት ባደረገው የአሜሪካ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ በአንድ መንደር የሚከናወኑ ተግባራት የግለሰቦችን መብቶች እንዳይነኩ ጥንቃቄ ይደረግባቸዋል፡፡

አንድ የመንደሩ ነዋሪ የራሱን መብት አስጠብቆ፣ በሌሎቹ መብት ላይ ሳይደርስ፣ ነገር ግን ደግሞ አካባቢያዊ ግዴታውን ተወጥቶ የሚኖርበት የመንደር ሕግ ነው ያላቸው፡፡ እያንዳንዱ ነዋሪ ቤቱንና በቤቱ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ያጸዳል፡፡ በተመደበለትና በተፈቀደለት ቦታ ብቻ መኪናውን ያቆማል፡፡ በተመደበው ጊዜ ቆሻሻውን ለሰብሳቢዎቹ ያስረክባል፡፡ ከተፈቀደለት መጠንና ሰዓት በላይ ድምፅ አያወጣም ፤ አይጠቀምም፤ በአካባቢው የተለየ እንቅስቃሴ ሲኖር ለፖሊስ ያሳውቃል፤ መንደሩን የሚነካ ጉዳይ ሲኖረው አስቀድሞ ያሳውቃል፤ በአካባቢው  የመንደሩን ገጽታና አነዋዋር የሚቀይር ነገር ሲኖር መንደርተኛው ይጠየቃል፤ ይወስናልም፡፡ እነዚህን መሰሉ መንደር ተኮር ሕጎች ናቸው ነዋሪዎቹ ተከባብረውና ተጠባብቀው በሰላም እንዲኖሩ የሚያደርጓቸው፡፡  


በሌላ በኩል ግን በሀገራችን መንደርን መንደር ያደረገው በታሪክ አጋጣሚ በአንድ አካባቢ ተሠርቶ መገኘቱ፤ ያለበለዚያም  በሆነ ፕሮጀክት በአንድ አካባቢ እነዚህ ቤቶች በመገንባታቸው እንጂ መንደርተኛውን የሚያስተባበረው፣ ተከባብሮና መብቱን ተጠባብቆ እንዲኖር፣ ግዴታውንም እንዲወጣ የሚያደርገው የመንደር ባሕልና ሕግ የለውም፡፡ አብዛኞቹ የመንደር ሕጎች እንደ ዕድርና ዕቁብ፣ ማኅበራዊ ኑሮን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የጉርብትና ሕጎች አይደሉም፡፡ ቀበሌ ሲመሠረት ዝቅተኛ የመንደር መዋቅርን ለመትከል ታስቦ እንደነበረ ይነገራል፡፡ በኋላ ግን ከመንደር አልፎ የአንድ ከተማ መዋቅር ያዘ፤ አሁን ደግሞ የወረዳ መዋቅር ሆኗል፡፡

እናንተ ሥራ ውላችሁ ስትመጡ ድንገት የመንደራችሁ መንገድ ተቆፍሮ ልታገኙት ትችላላችሁ፡፡ ቀድሞ ለማሳወቅ ግዴታ ያለበት አካል የለም፡፡ ወይም ከበራችሁ አጠገብ የዕድር ድንኳን ሊተከል መሆኑን የሚነግራችሁ የለም፡፡ ልጆቻችን እናጫውትበታለን ያላችሁት ሜዳ በድንገት አንድ ቀን የሠፈሩን ማንነት የሚቀይር ሕንፃ እንዲሠራበት ሲቆፈር ታዩት ይሆናል፡፡ ጎረቤቶቻችሁ ሦስት መኪኖቻቸውን አቁመው እርስዎ ለአንድ መኪና ቦታ ቢያጡ የማመልከቻ ቢሮ የለዎት ይሆናል፡፡ የሠፈሩ ሜዳ በሙሉ የቴሌቭዥን ዲሽ መትከያ ሲሆን ሥርዓት የሚያስይዝ አካል አይኖርም፤ ድግስ በተደገሰ፣ ማኅበር በተጠጣ፣ ሰው በተሰበሰበ ቁጥር እስከ ላንቃው በተከፈተ ሙዚቃና ጭፈራ ሲረበሹ ወይ ቀድሞ የሚነግርዎት አለያም እስከ መቼ አንድሚቀጥል የሚያሳውቅዎት አይኖርም፡፡

ይህንን በመሰለው የመንደር አኗኗር የኖረው ማኅበረሰባችን ነው እዚህ አሜሪካ ሲመጣ ችግር የሚገጥመው፡፡ 

ምንም እንኳን በአብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ለመኪና ማቆሚያ የተፈቀደና የተከለከለውን ሥፍራ የሚገልጥ ማስታወቂያ ቢኖርም በተከለከለው ቦታ መኪኖቹ ይቆማሉ፡፡ ሲብስም የነዋሪዎቹ የግል የመኪና ማቆሚያ ላይ እንዲቆሙ ይደረጋሉ፡፡ የከፋው ዘመዳችንም የነዋሪዎቹን የመውጫ መግቢያ በር ዘግቶ መኪናውን ያቆማል፡፡ በብዙዎቹ መንደሮች በሣር ላይ መጓዝና መንዳት ክልክል ቢሆንም እኛ ስንሰበሰብ ግን ሣሮች መከራቸውን ያያሉ፤ አንዳንዴም ቀድመው እንዲያውቁ ሳይደረግ ድንገት የከበሮው ድምጽ አካባቢውን ያናውጠዋል፡፡ የመኪና ጥሩንባ ሠፈሩን ያተራምሰዋል፡፡ 

ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ምግብና መጠጥ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ይከለክላሉ፤ በጉልሕ ጽፈው በሚታይ ቦታ ያስቀምጣሉ፡፡ እኛ ግን ጥሰን ይዘን እንገባለን፡፡ የሚያስደንቀው ደግሞ እዚያው ጥለነው እንወጣለን፡፡ መጽሐፎቻቸው ይበላሻሉ፤ ዕቃዎቻቸው ይተራመሳሉ፤ መጸዳጃዎቻቸው ይዝረከረካሉ፤ ጽዳቱ ይጓደላል፤ ዕቃቸው ይሰበራል፡፡  

አሜሪካውያን ሌሎች ማኅበረሰቦችን በፍርሃት ማየታቸው፣ በሌላም በኩል በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮበት ፖሊስ በአካባቢው ሰዎች የቅሬታ ስልክ ይጨናነቃል፡፡ የፈቀዱ አካላትም ጫና ይበዛባቸዋል፡፡ ያስፈቀዱ አካላትም ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ አንድ ላይ ተዳምሮም በአንዳንድ አካባቢዎች ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች አዳራሽ የሚያከራይ፣ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ የሚሸጥ፣ መስኮችንና ሜዳዎችን የሚፈቅድ እየጠፋ መጥቷል፡፡ ቢፈቀድ እንኳን እጅግ ጥብቅ በሆነ ግዴታና እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ እየሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎችም የፖሊስ ኃይል ለማቆም፣ የጽዳት ሰዎች ለመመደብ፤ እንቅስቃሴውን የሚከታተሉ የድርጅቱ ሰዎችን ለማሠማራትና የሚበላሹ ዕቃዎችን ለመከታተል እያሉ የሚቆልሉት ዋጋ አስመራሪ ሆኗል፡፡

በአንድ በኩል በጉርብትና ሕግ ውስጥ አለማደጋችንና የልምድ ችግራችን ለዚህ ዳርጎናል፡፡ ለሕግና ሥርዓት ያለን ቦታና የተገዥነት ልምድ ማነስ ጉዳት አስከትሎብናል፡፡ ከሕግ አውጭው እስከ ሕግ ተመሪው ድረስ ሕግንና ሥርዓትን መጣስ ልማድ በሆነበት ማኅረሰብ ውስጥ ማደጋችንም አጋልጦናል፡፡ የሠለጠነ ማኅበረሰብ ከሚገለጥባቸው ነገሮች አንዱ ‹በሕግና ሥርዓት መመራት› ነው፡፡ እኛ ዘንድ ግን በተለይ ‹ከተሜ በሚባለው አካባቢ› በሕግና ሥርዓት አስከባሪው እንጂ በሕጉና ሥርዓቱ የመመራቱ ባሕል እምብዛም ነው፡፡ ከሕጉ ይልቅ የሕግ አስከባሪው ይፈራል፤ ይከበራልም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕጉ ሰውየው ሆኗል፡፡ ለዚህም ይመስላል የትራፊክ ፖሊስ ሲኖርና ሳይኖር የትራፊክ ሕጉ አከባበር የሚለየው፡፡ ሕጉ የባለሥልጣኑ መሪ ሳይሆን፣ ሕጉ የባለሥልጣኑ ተገዥ ነው፡፡ 

ዕቃ ስንገዛ ማንዋሉን፣ ልብስ ስንገዛ ስለ አስተጣጠብና አተኳኮሱ የሚገልጠውን አብሮት የተሰፋውን መግለጫ የማንበብና በዚያ የመመራት ልማድ ያለን ስንቶቻችን ነን?  

ሌላው ችግር ደግሞ ለራሳችን የምንሰጠው ዋጋ ነው፡፡ ጽዳት፣ ሥርዓት፣ ፕሮቶኮል፣ ውበትና ሥምረት ለራስ ከሚሰጥ ዋጋ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ጃፓኖች ተቀምጠውበት የነበረውን ስታዲዮም አጽደተው ሲወጡ የተመለከተው ዓለም አድናቆቱን ችሯቸዋል፡፡ ለራሳቸው ያላቸውን ዋጋም አሳይተውናል፡፡ እነርሱ ለዓለም በጎን ነገር እንጂ አንዳች ክፉ ነገርን ለማበርከት ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ነግረውናል፡፡ የሚመጥናቸው ምን እንደሆነ እንድናይም አድርገዋል፡፡

ሌላው ደግሞ መዋቅራዊ ያልሆነን ኃላፊነት የመወጣት ልማዳችን አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ መዋቅራዊ ኃላፊነት ማለት በአንድ የተወሰነ መዋቅር ወይም ድርጅት ወይም ደግሞ አሠራር ውስጥ በመመረጥ፣ በምደባ ወይም ደግሞ በሹመት የሚመጣ ኃላፊነት ነው፡፡ የዚህ ክፍል አባል፣ ኃላፊ፣ ጸሐፊ፣ ተጠሪ፣ ሰብሳቢ፣ እየተባለ የሚጠራው፡፡ ኃላፊነትን እንዲህ ላሉ አካላትና ግለሰቦች እንሰጥና ‹እኔን አይመለከተኝም› እንላለን፡፡ ሥልጡን ማኅበረሰብ ግን ኃላፊነት የሚሰማውን ዜጋ መፍጠር የቻለ ነው፡፡ ‹ለአካባቢው ሰላም፣ ጽዳት፣ ዕድገት፣ ጤናና ማኅበራዊ ደኅንነት እኔም ድርሻ አለኝ› የሚል ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ፡፡ እስኪታዘዝ፣ እስኪነገረው፣ እስኪጨቀጨቅ የማይጠብቅ ዜጋ፡፡

በገቢ ማሰባሰቢያ፣ በኮሚቴ ምሥረታ፣ በማኅበር ማቋቋም ወቅት ሰዎች ኃላፊነትን ወስደው፣ ቃል ገብተውና ምለው ተገዝተው ይመረጡና በኋላ ዘወር የሚሉት፣ ካልተለመኑና ካልተጨቀጨቁ የማይሰበሰቡትና የማይሠሩት ውስጣቸው ‹ኃላፊነት› የሚባለው ነገር ስለሌለ ነው፡፡ በየውይይቱ ‹እገሌ ለምን እንዲህ አያደርግም› እንጂ ‹እኔ ለምን እንዲህ አላደርግም› የሚል ቁጭት የጠፋው ‹ኃላፊነት መውሰድ› የሚባለው ነገር ስለሌለ ነው፡፡  

ሠለጠኑ በሚባሉ ሀገሮች ከሚገኙ ወገኖቻችን ከሽቱና ቦርሳ፣ ከልብስና ቀሚስ በላይ ዕውቀትና ሥልጣኔን እንጠብቃለን፡፡ ሌሎቹ ቁሳቁሶች እነዚህ ሲገኙ እዚያው ይመረታሉና፡፡ አልፎ አልፎ እንደሚታየው ግን ሕግና ሥርዓትን በማወቅና በማክበር ረገድ በአንድ ቀን የፖሊስ ትምህርት ተለውጦ የግራ ጠርዙን ይዞ የሚጓዘው የሀገሬ ገበሬ እጅግ ተሽሎ ይታያል፡፡ ያ ሁሉ ገበሬ መሥመር ጠብቆ ሲሄድ አንድም የትራፊክ ፖሊስ በአካባቢው አይታይም፡፡ ታድያ ቦታ ተቀያይራችሁ ትሞክሩት እንዴǃ  

ሚነሶታ፣ሚንያፖሊስ

Read more http://www.danielkibret.com/2014/08/blog-post_15.html