አነ ጽጌ ገዳም … ወከመ ጽጌ ደንጐላት በማእከለ አሥዋክ ከማሁ አንቲኒ እንተ ኀቤየ በማእከለ አዋልድ

መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ን በረከት አዝመራው

 

  • "እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ … በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ ያማረ የተወደደ እንደሆነ አንችም በቈነጃጅት መካከል በእኔ ዘንድ እንደዚያ የተወደድሽ ነሽ፡፡" (መኃልይ. ፪፥፩)


ታላቁ የቤተክርስቲያን አባት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ "አይንህን አንስተህ ፍጥረታትን ተመልከት፤ስለ እግዚአብሔር የሚናገሩ አሻራዎቹን በየቦታው ታገኛለህ፤ አይንህን ዝቅ አድርገህ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንብብ፤ ስለ እርሱ የሚናገሩ ምሳሌዎችን ታገኛለህ" ይላል (Hymns Against Heresies)፡፡ ለኑሮ ፍጆታ ከሚጠቅመን በተጨማሪ ሥነ ፍጥረት የረቀቀውን ለመመሰል፣ ለአንክሮ ለተዘክሮ (እግዚአብሔርን በፍጥረቱ ለማመስገን) ይጠቅመናል፡፡

 

ለዐይናችን ደስታ፣ ለልቡናችን መደነቂያ ይሆኑ ዘንድ ምድርን በአበቦች ሰማይን በከዋክብት ያስጌጠ ሰውን ወዳጁ አምላክ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከዓመት እስከ ዓመት እግዚአብሔርን ስለመግቦቱ እና ስለ ድንቅ የእጆቹ ሥራዎች ማመስገንን አታስታጉልም፡፡ በዚህ የአበባ ወቅትም እንዲህ እያለች ትዘምራለች፦

“ነአኲተከ እግዚኦ አምላክነ
አሠርጎካ ለምድር በሥነ ጽጌያት
እኩት ወስቡሕ ስመ ዚአከ እግዚኦ” (ዝማሬ ዘዘመነ ጽጌ)


ትርጉሙም "ምድርን በአበቦች ውበት ያስጌጥካት አምላካችን አቤቱ እናመሰግንሃለን፤ አቤቱ ስምህ የተመሰገነ ፣የከበረ ነው" ማለት ነው፡፡ በሌላም ምስጋና፦

"ወጻእኩ ውስተ ገዳም እንዘ እሴብሖ ለእግዚአብሔር
ወበህየ ርኢኩ ኃይለ እግዚአብሔር
አዳም ግብሩ ዘኢኮነ ኃይሉ ከመ ኃይለ ሰብእ
አሠርገዎ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ አሠርገዋ በሥነ ጽጌያት
አዳም ግብሩ አዳም ግብሩ ለወልደ እግዚአብሔር"(እስመ ለዓለም ዘዘመነ ጽጌ)


ትርጉሙ "እግዚአብሔርን አመሰግን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወጥቼ በዚያ የእግዚአብሔርን ኃይል አየሁ፤ ሥራው መልካም ነው፤ ኃይሉም እንደ ሰው ኃይል አይደለም፤ ሰማይን በከዋክብት ምድርንም በአበቦች ውበት አስጌጣት፤ የእግዚአብሔር ልጅ ሥራዉ ያማረ ነው" ማለት ነው፡፡


ከምስጋናው ወደ ምሳሌው ስንሔድ ከጥንት ጀምሮ ልዑል እግዚአብሔር በነቢያት እና በሐዋርያት አድሮ ራሱን ሌሎችንም በፍጥረታት እየመሰለ ተናግሯል፡፡ በርእሱ በጠቀስነው የመጽሐፍ ቃል በጠቢቡ የእስራኤል ንጉሥ በሰሎሞን አድሮ ‹‹እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ፤ በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ ያማረ የተወደደ እንደሆነ አንችም በቈነጃጅት መካከል በእኔ ዘንድ እንደዚያ የተወደድሽ ነሽ፡፡›› ይላል፡፡ ዘመኑ ዘመነ ጽጌ (የአበባ ዘመን) ነውና በዚህ ጽሑፍ የአበባን ምሳሌነትና አበባ በቅዱሳት መጻሕፍት ያለውን መልእክት እንመለከታለን፡፡


አበባ ሲያዩት እጅግ የሚያምር፣ መዓዛዉ ልብን ደስ የሚያሰኝ፣ እፅዋት ፍሬ የሚያወጡበት ክፍል ነው፡፡ አበቦችን የፈጠረ ልዑል አምላክ ‹‹እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ›› ይላል፡፡ የአበባ ውበቱ እይታን ይማርካል፤ ረቂቅ ተመስጦን ያመጣል፡፡ እግዚአብሔርም በንጽህና በቅድስና ሆነው በዓይነ ልቡናቸው ሥራውን ለሚያስተውሉ፣ በንጹህ ልባቸው ላይ የጌትነቱን ብርሃን ለገለጠላቸው እርሱን ማወቅ ለልቡና ድንቅ፣ ለአእምሮ ረቂቅ ነውና ራሱን በምድረ በዳ አበባ መሰለ፡፡ ነገር ግን በቅድስናም ቢሆን ሥራውን ማስተዋል፣ የጌትነቱን ክብር ማድነቅ ይቻላል እንጂ መለኮታዊ ባህርዩን ማየትና መመርመር ግን ከፍጥረታት አቅም በላይ ነው፡፡


የአበባ መዓዛ ልቡናን ደስ ያሰኛል፤ ንቦችን ከሩቅ ይጣራል፡፡ የልዑል እግዚአብሔርም መዓዛ-ትምህርቱ (ቃሉ) ልቡናን ደስ ያሰኛል፤ጠቢባን ሰዎችን ከሩቅ ይጣራል፤ ‹‹ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ›› እንዳለ ንጉሥ ዳዊት። (መዝ.፻፲፱፥፻፫)


ከአበባ ዘርና ፍሬ ይገኛል፡፡ በእግዚአብሔር ኃይልም እነሆ ፍጥረታት ካለመኖር ወደ መኖር መጥተዋል፡፡ ከአበባ መዓዛ እና ፍሬ እንደሚገኙ ሃይማኖት እና ምግባር በእግዚአብሔር አጋዥነት ይፈጸማሉ፡፡


ሰው ከመሆኑ(ከሥጋዌ) ከ፲፻ ዓመት በፊት ‹‹እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ›› ሲል እግዚአብሔር በዳዊት ልጅ በሰሎሞን አንደበት የተናገረው ቃል ከዳዊት ዘር ሰው ስለመሆኑ ቀድሞ የተነገረ ትንቢት ተደርጎ ይተረጐማል፤ አበባ ፍሬን እንዲያስገኝ በክርስቶስ ሰው መሆንም ሥጋውን ደሙን ሰጥቶናልና፡፡ በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ‹‹ እስመ ናሁ ክረምት ኀለፈ፤ ጽጌ አስተርአየ በውስተ ምድርነ፤ ጊዜ ገሚድ በጽሐ፤ ቃለ ማዕነቅ ተሰምዐ በምድርነ፤ በለስ አውጽዐ ሠርፀ፤ አውያን ጸገዩ ወወሀቡ መዓዛ፤ እነሆ ክረምቱ አልፏልና፤ በምድራችን አበባ ታየ፤ የዜማ ጊዜ ደረሰ፤ የዋኖስ ቃልም በምድራችን ተሰማ፤ በለስም ቡቃያውን አወጣ፤ ወይኖች አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፤››(መኃልይ. ፪፥፲፩-፲፫) የሚለውን ሊቃውንት ‹‹የአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ዝናመ መከራ ወደ ዲያብሎስ ተመልሷልና፤ ጽጌ ክርስቶስ በሀገራችን ተገለጸ፤ አንድም በእኛ ሥጋ ተገለጸ፡፡ ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት ጊዜ ደረሰ፡፡ ‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ› ብሎ ሲያስተምር የዮሐንስ ቃልም ተሰማ፤ ሐዋርያት አስተማሩ፤ ምእመናን ለእግዚአብሔር ምግባር ሃይማኖት አቀረቡ፤›› ብለው ተርጉመውታል፡፡(መጻሕፍተ ሰሎሞን ወሲራክ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡


አበባ ከምድር ይበቅላልና፤ ጌታም ምድር ከተባለ ከእኛ ሥጋ ሰው መሆኑን በነቢዩ ሰሎሞን አንደበት ሲናገር ‹‹እኔ የምድረ በዳ አበባ ነኝ›› አለ፡፡ ‹የምድረ በዳ› ማለቱም እርሱ የእኛን ሥጋ ከመልበሱ በፊት ልምላሜ-ሃይማኖት እና መዓዛ-ምግባር በምድር ላይ መጥፋቱን ለመናገር እንደሆነ ሊቃውንት ተርጉመዋል፡፡አበባ ሲያቆስሉት መዓዛው ይበረታል፤ ጌታችንም መከራ መስቀልን በተቀበለ ጊዜ የፍቅሩ መዓዛ ዓለምን አውዷል፤ ‹‹ንጉሥ ውእቱ ዘለዓለም ክርስቶስ ፤አሠርገወ ሰማየ በድዱ ወጽጌያት ዘበበዘመዱ…መርዓዊሃ ለቤተ ክርስቲያን መዓዛሆሙ ለቅዱሳን፤ ንጉሥ ውእቱ ዘለዓለም ክርስቶስ ንጉሥ ውእቱ ኢይሠዓር መንግሥቱ፤ ክርስቶስ የዘላለም ንጉሥ ነው፤ የሰማይን መሠረት አሳመረ፤ አበቦችንም በልዩ ልዩ ኅብር አስጌጠ… የቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ፣ የቅዱሳን መዓዛቸው ነው፤ ክርስቶስ መንግሥቱ የማይሻር የዘላለም ንጉሥ ነው›› እንዲል የዘመነ ጽጌ አቡን፡፡


አሁን ደግሞ ‹‹በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ ያማረ የተወደደ እንደሆነ አንችም በቈነጃጅት መካከል በእኔ ዘንድ እንደዚያ የተወደድሽ ነሽ›› ወደሚለው ቀሪው የርዕሳችን ክፍል እንመለስ፡፡ ይህ ቃል ለጊዜው ለቤተ እስራኤል የተነገረ ነው፡፡ ይህንን ቃል ሊቃውንት ‹‹በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ ያማረ የተወደደ እንደሆነ በሞአብ በአሞን መካከል ያለሽ ቤተ እስራኤል አንችም በእኔ ዘንድ እንደዚያ የተወደድሽ ነሽ፡፡›› ብለው ተርጉመውታል፡፡(መጻሕፍተ ሰሎሞን ወሲራክ አንድምታ ተርጓሜ)


ለፍጻሜው ግን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ›› እንዳለ ከአብርሃም ዘር ከደጋግ እስራኤላውያን ለተወለደች ለቅድስት ድንግል ማርያም እና የአብርሃምን እምነትና ተስፋ ለያዘች እስራእል ዘነፍስ ለተባለች ለቤተ ክርስቲያን የተነገረ የልዑል አምላክ የፍቅር ንግግር ነው፡፡


ከእመቤታችን ስንጀምር ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በሰንበተ ክርስቲያን በሚነበብ የውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ‹‹አንቲ ውእቱ ጽጌ መዓዛ ሠናይ እንተ ሠረፀት እምሥርወ ዕሤይ፤ ከዕሤይ ሥር የወጣች መዓዛዋ ያማረ አበባ አንቺ ነሽ›› እንዳለ ‹‹በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ ያማረ የተወደደ እንደሆነ አንችም በቈነጃጅት መካከል በእኔ ዘንድ እንደዚያ የተወደድሽ ነሽ›› የተባለችው በሥጋ እስራኤላውያን ይሁኑ እንጂ በእምነታቸው እና በግብራቸው ‹‹እሾህ›› በተባሉ አይሁድ መካከል ሆና በቤተ መቅደስ በትህትና የኖረች በኋላም በቅድስና በንጽህና አምላክን የወለደች ድንግል ማርያምን ነው፡፡ በሥጋዌ ትርጓሜ ጌታችንን ‹አበባ› ካልን እመቤታችንን ‹ሳይተክሏት ውሃ ሳያጠጧት አብባ የተገኘች የአሮን በትር› እንላለን፤ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ደግሞ ‹ፍሬ› እንላለን፡፡ በዚህ የትርጓሜ መስመር የማኅሌተ ጽጌ ደራሲ አባ ጽጌ ድንግል እንዲህ ብሎ እመቤታችንን አመስግኗታል፦

"ተፈሥሒ ድንግል እንተ ኢተአምሪ ብእሴ
ዘጸገይኪ ለነ አሐደ እምነ ሥላሴ፤"


ትርጉሙ ‹‹አበባ ከዕፅ እንደሚገኝ ከሥላሴ አካላት አንዱን በሥጋ የወለድሽልን ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ›› ማለት ነው፡፡


እመቤታችንን ‹አበባ› ካልን ደግሞ ጌታን ‹ፍሬ› እንላለን፤ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ ‹‹አንቲ ውእቱ ዕፅ ቡሩክ ዕፀ ሕይወት ወዕፀ መድኀኒት…ፍሬኪኒ ፍሬ ሕይወት ውእቱ ወዘበልዐ እምኔሁ ሕይወተ ዘለዓለም የሐዩ፤ የተባረክሽ የሕይወትና የመድኀኒት ዕፅ አንቺ ነሺ…ፍሬሽም የሕይወት ፍሬ ነው፤ ከእርሱ የበላ ለዘላለም በሕይወት ይኖራል›› እንዳለ፡፡ በተጨማሪም አባ ጽጌ ድንግል በዚሁ በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ ደግሞ እንዲህ ይላል፦

ተፈሥሓት ምድር ወሰማይ አንፈርዓፀ
በዕለተ ጸገዩኪ አብላስ ወአውፅኡ ሠርፀ


ትርጉሙም ‹‹በለሶች(ኢያቄምና ሃና) አበባ አንቺን በወለዱ ጊዜ፣ ቡቃያ አንቺን ባስገኙ ጊዜ፣ ምድር ደስ ተሰኘች፤ ሰማይም በደስታ ዘለለ›› ማለት ነው፡፡


ሌላዋ ‹‹በሾህ መካከል ያለ የሱፍ አበባ›› የተባለች እመቤታችንንም የምታጠቃልለው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በዚህ ትርጉም ‹ቤተ ክርስቲያን› የሚለው ማኅበረ ምእመናንንም እያንዳንዳቸውን ቅዱሳንንም ያጠቃልላል፡፡ሙሽራዋ ወልደ እግዚአብሔር ሙሽሪት ቤተ ክርስቲያንን ‹እሾህ› በተባለ ክፉ ዓለም መካከል የምትኖሪ ‹የሱፍ አበባ› ነሽ ሲላት ነው፡፡


በዚህም ምክንያት የሁለተኛው የጽጌ እሁድ ምንባባት ስለ ክርስቶስ እና ቤተክርስቲያን በሙሽሮች የተመሰለ ፍቅር የሚያትቱ ናቸው፡፡ የዚህ እሁድ ምስባክ ‹‹የድካምህንም ፍሬ ትመገባለህ፤ ምስጉን ነህ መልካምም ይሆንልሃል። ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት፤ ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው።›› የሚል ነው(መዝ. ፻፳፯፥፪)፡፡ የእለቱ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም ‹‹ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ” የሚል ነው (ኤፌ. ፭፥፳፰-፴፫)፡፡ ወንጌሉ ደግሞ ‹‹ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ … ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል”ይላል (ዮሐ. ፫፥፳፯-፴)፡፡


ድንግል ማርያም ከፍጥረታት ሁሉ በላይ በቅድስና የከበረች መዓዛዋ የመላ (ምልዕተ ጸጋ የሆነች) አበባ ነች፡፡ ቤተክርያቲያንም የክርስቶስን የቅድስና መዓዛ ይዛ ለዓለም የምታሰርጭ ንጽህት አበባ ናት፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነገር ግን በክርስቶስ ሁልጊዜ ድል በመንሣቱ ለሚያዞረን በእኛም በየስፍራው ሁሉ የእውቀቱን ሽታ ለሚገልጥ ለአምላክ ምስጋና ይሁን፤ በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ ለእነዚህ ለሞት የሚሆን የሞት ሽታ ለእነዚያም ለሕይወት የሚሆን የሕይወት ሽታ ነን። ለዚህም ነገር የሚበቃ ማን ነው?›› እንዲል(፪ኛ ቆሮ. ፪፥፲፬)፡፡


በዚህ የትርጓሜ መስመር ቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ አበቦች የሞሉባት ገነት (የአትክልት ቦታ)፣ ሙሽራዋ ክርስቶስ የአትክልት ቦታው ባለቤት፣ የአበቦቹ ውበትና መዓዛ የምእመናን ሃይማኖትና ምግባር ናቸው፡፡ በዘመነ ጽጌ ሊቃውንት በማኅሌት እንዲህ እያሉ ያመሰግናሉ፦

"ወልድ እኁየ ወረደ ውስተ ገነት ከመ ይርዓይ ስነ ጽጌያት
ትብሎ መርዓት ለመርዓዊሃ ነዓ ወልድ እኁየ ንፃዕ ሐቅለ
ወናንሶሱ አእፃዳተ ወይን ኀበ ጸገየ ወይን ወፈርየ ሮማን
ዬ ዬ ዬ ውስተ ገነት ብሒል ውስተ ርስቶሙ ለኲሎሙ ሐዋርያት ብሒል" (ዚቅ ዘዘመነ ጽጌ)


ትርጉሙም  "ልጅ ወንድሜ የአበቦቹን ውበት ያይ ዘንድ ወደ ገነቱ ወረደ፤ ሙሽራይቱ ሙሽራውን፦ልጅ ወንድሜ ሆይ ና ወደ በረሐ እንውጣ፤ወይን ወደአበበባቸው፣ ሮማን ወደአፈራባቸው የወይን ቦታዎች እንዘዋወር፤ዬ ዬ ዬ ወደ ገነት ማለት ወደ ሐዋርያት ሁሉ ርስቶች (ሐዋርያት በእጣ ተከፋፍለው ወደ አስተማሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት) ማለት ነው" የሚል ይሆናል፡፡


ቅዱሳንንም "በእሾህ መካከል እንዳሉ የሱፍ አበቦች እናንተ ለእኔ እንደነዚያ ያማራችሁ ናችሁ" ይላቸዋል፡፡ ያማረ ውበታቸው እና መዓዛቸው የቀና ሃይማኖታቸው እና ምግባራቸው ነው፡፡

"መዓዛሆሙ ለቅዱሳን ከመ ጽጌ ደንጎላት ወከመ ሮማን ዘውስተ ገነት
ይትፌሥሑ ጻድቃን የዋሃን ውሉደ ብርሃን
በትፍሥሕት ዔሉ ውስተ አድባር"(ዚቅ ዘዘመነ ጽጌ)


ትርጉሙ "የቅዱሳን መዓዛቸው እንደ ሱፍ አበባ፣ በአትክልት ቦታ ውስጥ እንዳለ ሮማን ነው፤ የብርሃን ልጆች የሆኑ የዋሃን ጻድቃን ደስ ይበላቸው፤ በተራሮች ላይ ደስ እየተሰኙ ዞሩ" ማለት ነው፡፡


ምንም እንኳ ቤተ እስራኤል፣ እመቤታችን፣ ቤተክርስቲያን እና ቅዱሳን ብለን ከፋፍለን ብናያቸውም ፍሬ ነገሩ ግን የተከፋፈለ አይደለም፡፡ ልምላሜ፣ አበባ እና ፍሬ የሃይማኖት፣ የቅድስና እና የምግባር ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቤተ እስራኤልንም ሆነ ቤተክርስቲያንን፣ እመቤታችንንም ሆነ ቅዱሳንን በእግዚአብሔር ዘንድ ያስወደዷቸው የቀና ሃይማኖታቸው እና የተቀደሰ ሥራቸው ነውና፡፡


ከብዙ በጥቂቱ ስለ አበባና ምሳሌነቶቹ ለመናገር ሞክረናል፡፡ አበባ በቅዱሳት መጻሕፍት የያዛቸው ምሳሌያዊ ትርጎሞች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሊቃውንት ‹‹ምሳሌ ዘሐጽጽ፤ ምሳሌ ከተመሳዩ ያንሳል›› እንዲሉ ከእኛ ጋር ለመነጋገር ራሱን ዝቅ በማድረግ ራሱን በአበባ መስሎ ተናገረ እንጂ ምሳሌዎች ስለእርሱ ሊናገሩት የሚችሉት በጣም ጥቂት ነገር ብቻ ነው፤ ስለሌሎቹም እንደዚሁ፡፡


"ንጉሥ ውእቱ ዘለዓለም ክርስቶስ ፤አሠርገወ ሰማየ በድዱ ወጽጌያት ዘበበዘመዱ…መርዓዊሃ ለቤተ ክርስቲያን መዓዛሆሙ ለቅዱሳን፤ ንጉሥ ውእቱ ዘለዓለም ክርስቶስ ንጉሥ ውእቱ ኢይሠዓር መንግሥቱ፤ ክርስቶስ የዘላለም ንጉሥ ነው፤ የሰማይን መሠረት አሳመረ፤ አበቦችንም በልዩ ልዩ ኅብር አስጌጠ… የቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ፣ የቅዱሳን መዓዛቸው ነው፤ ክርስቶስ መንግሥቱ የማይሻር የዘላለም ንጉሥ ነው" አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1330-2013-10-09-08-46-51