ዋሻ አምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም

  ታኅሣሥ 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

ጅብና የነብር መንጋዎች እማሆይን ሳያተናኮሉ ያላምዷቸው ነበር፡

 

“ሳልማር ማንበብ ቻልኩ”

 

በደን ልማት፣ በባዮ ጋዝና በትጋታቸው ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋ ሥራቸው ቀርቧል፡፡


ክፍል አንድ

urael ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር የሚወስደውን የአስፋልት መንገድ ይዘው ሲጓዙ ፍቼ፣ ደብረ ጉራቻ፣ጎሀ ጽዮን ከተሞችን አልፈው የዓባይን በረሃ ካጠናቀቁ በኋላ የደጀን ከተማን ያገኛሉ፡፡ ጉዞዎን በመቀጠል ...


የምሥራቅ ጎጃም ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስን እንዳለፉ አማኑኤል ከተማ ይደርሳሉ፡፡ የአማኑኤል ከተማ ከአዲስ አበባ 330 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ የማቻክል ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ ከአማኑኤል ከተማ ወደ ግራ ታጥፈው በጠጠራማው መንገድ ዐሥር ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ አማሬ የምትባል አነስተኛ የገጠር መንደር ያገኛሉ፡፡

ትንሽ እንደተጓዙም ግራራም ማርያም ቀበሌ ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ በርካታ ተፈጥሮአዊ ጸጋዎች ይገኛሉ፡፡ በደን የተሸፈኑ ተራሮችን ፣ በመካከላቸውም ድንቅ ሸለቆ ፈጥሮ የሚያልፈው ‹‹የሸማ ማጠቢያ›› ወንዝ ይገኛል፡፡ ወንዙ ከፀሐይ መግቢያ ወደ ፀሐይ መውጫ ቁልቁል ሲፈስ ላየው ተፈጥሯዊ ውበቱ ይማርካል፡፡ የሸማ ማጠቢያ ወንዝ ከተፈጥሯዊ ውበቱ ባሻገር ለአካባቢው አርሶ አደሮች የፍራፍሬና አትክልት ልማት አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡


ጥቂት እንደተጓዙ ድንገት የሚታይ የቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ይደርሳሉ፡፡ ከቅዱስ ዑራኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በግራ በኩል ደግሞ የዋሻ አምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳምን የእንስሳት ማደሪያ የሆነውን ቆርቆሮ ቤት ያያሉ፡፡ የከብቶችን ቤት ወደ ግራ እየተው ደረጃውን ቁልቁል መንገድ ይዘው ሲጓዙ ቀጭን መንገድ ያገኛሉ፡፡


ከዚያም በቆርቆሮ ክዳን የተሠራውን የተግባር ቤት የገዳሙ ምዕመናን ምግብ የሚዘጋጅበትና የሚታደልበት ቤት ነው፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ መቀነታቸውን ታጥቀው፣ ቆባቸውን ደፍተው፣ እንጀራ የሚጋግሩ፣ ወጥ የሚሠሩ፣ ማገዶ የሚያቀርቡ እንስት ባሕታውያን በየዕለቱ በትጋት ሲሠሩ ይመለከታሉ፡፡


fawafwate a ከተግባር ቤቱ ወደ ፀሐይ መግቢያ ታጥፈው የአቀበቱን ጉዞ መያያዝ ግድ ይልዎታል፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ሲጓዙም በግራ ቀኝ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያገኛሉ፡፡ ወደፊት ጥቂት እንደተጓዙም የተለያዩ ምንጮች ከከፍታ ቦታ በስተቀኝ በኩል ሁለት ሰፋፊ ዋሻዎችን ያያሉ፡፡ የመጀመሪያው ዋሻ ወደ ገዳሙ የሚመጡ ጠበልተኞች የሚያርፉበትና ምግባቸውን የሚያበስሉበት ትልቁ ዋሻ ነው፡፡ በዚህ የዋሻ በር የቀኝ ጠርዝ ላይ ከምድር እስከ ዋሻ ጣራ ድረስ በድንጋይ ካብ የተሠራና ጠንካራ የጣውላ መዝጊያ የተገጠመላት ትንሽ ቤት ያያሉ፡፡ ይህች አነስተኛ ቤት የገዳሙ መሥራች ቤት ናት፡፡


ትልቁንም ዋሻ በቀኝ በመተው፤ ወደ ግራ ደግሞ ገደላማውን ቦታ እየቃኙ ወደፊት ጥቂት እንደተራመዱ ሁለተኛውን ዋሻ ያገኛሉ፡፡ ይህ ዋሻ ከመጀመሪያው ዋሻ ጋር በተፈጥሮ ግድግዳ ተያይዟል፡፡ በዚህ ዋሻ ፊት ለፊት ደግሞ ከከፍታ ቦታ እየተወረወሩ ወደ ገደሉ የሚወርዱ ሦስት ትንንሽ ጅረቶችን ያገኛሉ፡፡ አንደኛውን ፏፏቴ እልፍ እንዳሉም የዋሻ አምባ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳምን ያገኛሉ፡፡ ይህ ገዳም ሁለት በሮች አሉት፡፡


በመጀመሪያ ከውጪ ወደ ዋናው የሚገባ ሰው ምንም ነገር ማየት አይችልም፡፡ ለዓይን የማይታይበት ድቅድቅ ጨለማ ነው የሚያጋጥመው፡፡ ድቅድቁ ጨለማ ቀስ በቀስ እየተገፈፈና ዓይን ጨለማውን እየተለማመደ ሲሔድ የዋሻውን ምዕራባዊ ዳርቻ ይመለከታሉ፡፡ ዋሻው ከምዕራብ ወይም ከፀሐይ መግቢያ ወደ ምሥራቅ ወይም ፀሐይ መውጫ በቁመት ከፍ እያለ ይሔድና ከበሮቹ ላይ በሚገናኝበት ቦታ ላይ ከሁለት ሜትር ርቀት የበለጠ ቁመት አለው፡፡


ከምስራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ዋሻ ሲገባ ያለው የጣራ ርዝማኔ እየቀነሰ ይሔድና ከተፈጥሮ የድንጋይ ግድግዳ ጋር ይዋቀራል፡፡ ሰፊው የዋሻ ክፍል የቅዳሴ አገልግሎት የሚሰጥበት ሲሆን በዋሻው የግራ ጠርዝ መጨረሻ ላይ ያለው ደግሞ የተለያዩ ጽላቶች የሚገኙበት ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ያላየናቸው ዋሻዎችና ሌሎች ምሥጢራዊ ሀብቶችን ባለቤቱ ያውቀዋል፡፡ ቅዱሳን ያውቁታል፡፡ እማሆይም ሊያውቁት ይችላሉ፡፡


washa2 ከዋሻው በር በውጭ የቀኝ አቅጣጫ በአናት በኩል ሁለት ጅረቶች ከከፍታ ቦታ ወደ ታች እየተወረወሩ ፊት ለፊት ካለው ገደል የመዋኛ ገንዳ ከሚመስለው ይቀላቀላሉ፡፡ አንደኛው የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት ጠበል ሲሆን፤ ከዚያ እልፍ ብሎ ደግሞ ከአንድ ምሰሶ ሥር የሚፈልቅ የቅዱስ ዑራኤል ጠበል ይገኛል፡፡


ከመጀመሪያው ዋሻ ወደ ገዳሙ ዋሻ ሲኬድ በሁለተኛ መስመር ላይ ከሚገኘው አነስተኛ ምንጭ ሥር አንድ ዛፍ ከዚህ ውሃ እየተመገበ ሥር ሰዶ ድንጋዮችን ሰንጥቆ ገብቶ አድጎ ይታያል፡፡ ይህ እንጨት ከድንጋይ በላይ ያለው አካሉ የመስቀል ቅርፅ ያለው ነው፡፡
የዋሻ አምባ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በአማራ ብሔራዊ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻክል ወረዳ ግራራም ቀበሌ የወንዶችና የሴቶች ገዳም ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡


ገዳሙ እንዴት ተመሠረተ? በማንስ ተመሠረተ?


ወይዘሮ ድንቃየሁ ከዋሻ አምባ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በአጭር ርቀት ላይ በሚገኘውና ቂርቆስ በተባለው የገጠር ቀበሌ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ውስጥ ነው የተወለዱት፡፡ ለዘመናዊም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት አልታደሉም፡፡ ዕድሜአቸው ለቅመ ሔዋን ሲደርስ ወላጆቻቸው በአካባቢው ባሕልና ወግ መሠረት ዳሩአቸው፡፡ ከዚያም ወይዘሮ ድንቃየሁ ቤት ሠርተው ጎመን ዘርተው የሞቀ ትዳር ባለቤት ሆኑ፡፡ ሁለት ልጆችንም አፈሩ፡፡ በዚህ የትዳር ሕይወታቸው ላይ እያሉ በተደጋጋሚ በሕልም ይታያቸው ነበር፡፡

ወሩን ቀኑንና ዓመተ ምሕረቱን ለይተው በማያውቁት አንድ ሌሊት በርካታ ካህናትና ቀሳውስት በተሰበሰቡበት ቦታ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከፊሎቹ ቀዮች ከፊሎቹ ደግሞ ጥቁሮች ነበሩ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ በእነዚህ ሰዎች መካከል ለመቀመጥ ሲሞክሩ አንድ ክንፍ ያለው ቀይ ሰው እጃቸውን ይዞ እየመራ ከዋክብት ወዳሉበት አንድ ቦታ ያደርሳቸዋል፡፡

 

ከዚያም ይህ ሰው ከመሬት ወደ ሰማይ የተዘረጋ ቀጭን የብረት መሰላል እያሳየ በዚያ መሰላል ላይ ወደ ላይ እንዲወጡ ይነግራቸዋል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ እንደታዘዙት መሰላሉን እየፈሩ እየቸሩ ወደ ላይ መውጣት ይጀምራሉ፡፡ የመሰላሉን ግማሽ ያህል እንደወጡ ወደታች ሲመለከቱ ጥቋቁር ሰዎች ያሉበትን ገደላማ መሬት ያያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በመንታ ሃሳብ ውስጥ ሆነው ቆም ብለው ወደላይ ለመቀጠል እንዳልቻሉ ሲያስቡ ወደታች ለመመለስ በመሬት ላይ ሆነው የሚጠባበቋቸው ጥቋቁር ሰዎች ጉዳት እንደሚያደርሱባቸውና ገደል እንደሚገቡ እየተጨነቁ እያሉ ያው እየመራ ያወጣቸው ሰው ‹‹ቀጥይ አትፍሪ›› በሚል ያበረታታቸዋል፡፡

 

emahoyc ወይዘሮ ድንቃየሁ የጀመሩትን የመሰላል መውጣት ትግል ቀጥለው መጨረሻ ላይ አራት ዙር አጥር የመሰለ ነገር ላይ ያርፋሉ፡፡ በዚያ ቦታ ቤተ መንግሥት አለ፡፡ በእያንዳንዱ አጥር በር ላይ ዘበኞች ቆመዋል፡፡ የመጀመሪያው ዘበኛ ወደ ሁለተኛ የሁለተኛው ወደ ሦስተኛ የሦስተኛው ወደ አራተኛ ዘበኛ በር እየከፈቱላቸው መንገድ እየመሩ ካስተላለፏቸው በኋላ መጀመሪያ መሰላሉን እንዲወጡ ያዘዛቸው ቀይ ሰው ወደ ከበሮ መሰል ቤት ያስገባቸውና ‹‹አይዞሽ አትፍሪ፤ ከእንግዲህ የሚያገኝሽ የለም በቃ›› የሚል ማጽናኛ ቃል ይነግራቸዋል፡፡ ወዲያው ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ፡፡“ምን ይሆን እያልኩ አደንቃለሁ እፈራም ነበር” አሉ እማሆይ፡፡

 

ሌላ ጊዜ ደግሞ ትዳራቸውን ትተው ለመውጣት ምክንያት የሆናቸውን ሕልም አዩ ሀገር በእሳት ሲለበለብና ሕዝቡ ሁሉ ከዚህ እሳት ለማምልጥ ሲሮጥ ይመለከታሉ፡፡ እሳቸውም ከእሳቱ ሮጠው አምልጠው ሲሄዱ በተደጋጋሚ ያያሉ፡፡“ይህ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው፡፡” ብለው ሀብት ንብረቴን፤ ልጆቼን ሳይሉ ትዳራቸውን ትተው ወደ ወላጆቻቸው ቤት ይመለሳሉ፡፡ የፈጣሪያቸውን መንገድ መርጠውና ፈቅደው የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞአቸውን ለመጀመር ጎጇቸውን ተሰናበቱ፡፡

 

ወይዘሮ ድንቃየሁ ወደ ወላጆቻቸው ቤት እንደተመለሱ ቀን ቀን አብዛኛውን ጊዜአቸውን ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ በማስቀደስና ስብከተ ወንጌልን በማዳመጥ ማሳለፍ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው አደረጉት፡፡ ድንገት ተነስተው ግን ወደ ሌላ ቦታ ተጓዙ፡፡ ቦታው አሁን ካለበት በግምት ከ65 ኪሎ ሜትር በላይ በሚርቀውና ‹‹ሰሳ ገዳም›› እየተባለ በሚጠራ ቦታ ነው፡፡ ሰሳ ገዳም ከደረሱ በኋላም ለሰባት ወር በዚያም ተቀመጡ፡፡ ሰሳ ገዳም ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ አባ አስራት ገዳም ከሚባለው ጥንታዊ ገዳም አካባቢ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡ ከሰባት ወር የገዳም ቆይታቸው በኋላም እንደገና ወደ ወላጆቻቸው ቤት ተመለሱ፡፡

 

ወደ ወላጆቻቸው ቤት እንደተመለሱም እንደተለመደው ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን እየተመላለሱ ማስቀደስና በዚያው ጸሎት ሲያደርሱ መዋል የዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ሆነ፡፡ ይህ በእንዲህ ታላቅ እኅታቸው “ሰኔ ጎልጎታ መጸሐፍ ገዝተሸ አንብቢ” ብላቸው ስለነበር እንዳለ አንድ ቀን እናታቸው ወደ ከተማ ለገበያ ለመሔድ ሲዘጋጁ መጽሐፍ እንዲገዙላቸው ይጠይቃሉ፡፡ እናትም ‹‹አንቺ አልተማርሽ፤ ፊደል አትለዪ መጽሐፍ ምን ያደርግልሻል?›› ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁም ግድየለም መጽሐፉን ባየው ብሳለመውስ? የሚል መልስ ይሰጧቸውና እናት ወደ ገበያ ሊወጡ ሲሉ የምትገዢልኝ ደግሞ የሰኔ ጎለጎታ መጽሐፍን ነው ብለዋቸው ይለያያሉ፡፡ እናትም የሰኔ ጎለጎታን መጽሐፍ ከገበያ አጠያይቀውና ገዝተው ያመጡላቸዋል፡፡ መጽሐፉን እየገለጡ ሲመለከቱ ከቆዩ በኋላ “ድንግል ሆይ ምንም እንኳን እንደምኞቴ ጸሎትሽን ማንበብና መድገም ባልችልም ጸሎትሽን እንደጸለይኩ አድርገሽ ቁጠሪልኝ፡፡” እያሉ በመማጸን መጽሐፉን ይዘጋሉ፡፡

 

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ተአምር ይከሰታል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ እናታቸው የገዙላቸውን የሰኔ ጎልጎታ የቅድሰት ድንግል ማርያም የጸሎት መጽሐፍ እየገለጡ ገጽ በገጽ እያገላበጡ ሲመለከቱ ይቆዩና አጥፈው መማጸናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ ሳያስቡት የሰኔ ጎልጎታን ከገጽ እስከ ገጽ ማንበብ ጀመሩ፡፡ ይህን የሰሙ እናታቸውም “ዛሬ ደግሞ ከማን ጋር ታወሪያለሽ” ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ “እዪው መጽሐፉን ማንበብ ቻልኩ እኮ፡፡ ስሚ” በማለት የንባብ ችሎታቸውን ያሰሟቸዋል፡፡ እናትም በነገሩ ተደንቀው ልጃቸውን ወይዘሮ ድንቃየሁን ወደ ንስሐ አባታቸው ይዘው ይሔዳሉ፡፡ የንስሐ አባታቸውን በቤተ ክርስቲያን ያገኙና የሆነውን ሁሉ ይነግሯቸዋል፡፡ ቄሱ ነገሩን ማመን ቢሳናቸውም የተባለውን ድንቅ ተአምር ለመስማት መርጠው ወይዘሮ ድንቃየሁ መጽሐፉን በንባብ እንዲያሰሟቸው ጠየቋቸው፡፡

 

መጽሐፉን ቃል በቃል እያሰሙ ገጾችን እያገላበጡ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አነበቡ፡፡ ቄሱም እየተደነቁና እየተገረሙ ሁሉንም ካዳመጡ በኋላ ‹‹እግዚአብሔር የጀመረልሽን ፀጋ ከዳር ያድርስልሽ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም አትለይሽ፡፡ ያነበብሽው ጸሎት ድንግል ማርያም በአማልጅነቷ ለአማኞች ያቀረበችው ጸሎት ነው፡፡ በስሟ መጽሐፍ ለጻፉ፣ ቤተ ክርስቲያን ለሠሩ፣ በስሟ ምጽዋት ለመጸወቱ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕጣን፣ ጧፍ ላበረከቱ ምሕረት ጸጋ ይሰጥ ዘንድ ለልጇ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብሩ በጎልጎታ ላይ ሆና ያቀረበችለት ልመና ነው፡፡ ልጇም እናቱ የጠየቀችውን ሁሉ ለመፈጸም ቃል ገብቶላታል፡፡ በቃለ መሃላም አረጋግጦላታል፡፡ ይህን ነው አሁን ያነበብሽው፡፡ ጸሎትና ክርስቶስም ለእናቱ የገባውን ቃል ኪዳን ለአንችም ይፈጽምልሽ ዘንድ ጸሎቴ አይለይሽም፡፡ የጀመርሽው መንፈሳዊ ጉዞ በእግዚአብሔር የተፈቀደ በመሆኑ ያለጥርጥር ይሳካል›› ሲሉ አባ ለወይዘሮ ድንቃየሁ ቡራኬ ሰጥተው አሰናበቷቸው፡፡ በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻል የለ፡፡

 

ወይዘሮ ድንቃየሁ ሕልም ማየታቸውን አላቋረጡም፡፡ አንድ ቀን አባ ይትባረክ የተባሉ መነኩሴ ከሩቅ ቦታ መጥተው በወላጆቻቸው ቤት የእግዚአብሔር እንግዳ ብለው ይገባሉ፡፡ እማሆይም እራታቸውን አብልተው እግራቸውን አጥበውና ምኞታቸውን አዘጋጅተው እንዲያድሩ ያደርጋሉ፡፡

 

የአባ ይትባረክ ወደዚያ አካባቢ መምጣት የተለመደ ነበር፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት በወይዘሮ ድንቃየሁ አባት የተጀመረውን የቅዱስ ቂርቆስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራትና ሕዝቡን ለማስተማር ብዙ ጊዜ ተመላልሰዋል፡፡

 

ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ሳይጀመር ይቀራል፡፡ የወይዘሮ ድንቃየሁ ወላጅ አባትና አባ ይትባረክ የተነሱለት ዓላማ ባለመሳካቱ ተስፋ ቆርጠው ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡ አባ ይትባረክ በእንግዳነት ባደሩበት ሌሊት ወይዘሮ ድንቃየሁ ሕልም ያያሉ፡፡ ሕልሙ ወይዘሮ ድንቃየሁ ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ አዘውትረው የሚሔዱቡት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ መግቢያ በር ላይ እንደደረሱ ሦስት ሰዎች ቀድመዋቸው በቀጥታ ወደ መቅደስ ይገባሉ፡፡ ከዚያም ወይዘሮ ድንቃየሁ ተከትለው ለመግባት ሲሞክሩ በሩ ላይ ሁለት እርጉዝ ሴቶች ለመውለድ ምጥ ተይዘው ያገኛሉ፡፡

 

ሁለቱን ሴቶች ምጥ ተይዛችሁ ለምን እዚህ መጣችሁ? እያሉ በመጠየቅ ላይ እንዳሉ ሴቶቹ ይገላገላሉ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ አሁን ተገላግላችኋል፡፡ ምስጋና ለአምላክ ይሁን፡፡ ተነሱና የማርያም መሸኛ እናዘጋጅ ይሏቸዋል፡፡ ሁለቱ አራስ ሴቶች እኛ ማተብ ሳናስር ከዚህ አንወጣም በማለት ለመውጣት ፈቃደኛ አልሆኑም፡:

 

ወይዘሮ ድንቃየሁ እምቢ ሲሏቸው ከቤተ ክርስቲያኑ ወጥተው ወደ ቤታቸው ለመሔድ ጉዞ ሲጀመሩ አንድ ወጣት ቀይ ግምጃ የለበሰ ወጣት ጠርቶ ያስቆማቸዋል፡፡ ከዚያም ሰውየው ወደ አጠገባቸው ይቀርብና “እንኪ ይህን መስቀል ለአባ ይትባረክ ስጫቸው፡፡” ይላቸዋል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ “ እኔ ቄስ ወይም ዲያቆን አይደለሁም፡፡ መስቀል እንዴት እይዛለሁ?” በማለት እምቢታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሰውየው አሁንም ጥያቄውን እየደጋገመ ያስቸግራቸዋል፡፡ ወዲያው “አባ ይትባረክን መስቀሉን ይዘህ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ጊዜ እየዞርህ ባርከው የታሰበው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይሠራል፡፡ የተቀበረውም ይመክናል ብለሽ ንገሪው፡፡” ብሎ መልእክቱን እንደነገራቸው ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ፡፡

 

ጥዋት ቀደም ብለው አባ ይትባረክና ወይዘሮ ድንቃየሁ ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ለኪዳን ሲሄዱ ፤ ሌሊት ያዩትን ሕልም ለአባ ይትባረክ ይነግሯቸዋል፡፡ አባ ይትባረክ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ ትርጉሙን ለወይዘሮ ድንቃየሁ ይነግራሉ፡፡ “ትርጉሙም የተገላገሉት እኛ የደከምንበት፣ ብዙ ያሰብንበት የዚህ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ከዳር መድረሱን እኛም ከሀሳብ መገላገላችንን የሚያመለክት ነው፡፡ የታሰበው በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ መጀመርና መጠናቀቅም አንቺን አምላክ ምክንያት ያደርጋል፡፡ በአንቺ ቅስቀሳና ማስተባበር የሕዝቡ ልቡና ቀንቶ አሳባችን ይሳካል፡፡” በማለት ተረጎሙላቸው፡፡

 

በሚቀጥለው የሰንበት ቀን ሕዝቡ በተሰበሰበበት አባ ይትባረክና ወይዘሮ ድንቃየሁ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ የሚጀመርበትን ሀሳብ ለቀበሌው ሕዝብ ያቀርባሉ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ልብ አስቦ በአንድ መንፈስ ተመካክሮ ለስምንት ዓመት ሲጓተት የቆየው ሥራ እንዲጀመር አስተባባሪ ሽማግሌዎችን ሰይሞ ይለያያል፡፡

 

የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ ተጀመረ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሥራ አደራ ከአምላክና ከቀበሌው ሰበካ ጉባኤ ሕዝብ ከተቀበሉ በኋላ እርዳታ ለማሰባሰብ በተለያዩ ከተሞች ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡
የአካባቢው አርሶ አደሮችም በገንዘባቸው፣በጉልበታቸው ሙሉ ትብብር በማድረግ የቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ተመረቀ፡፡

 

የቅዱስ ቂርቆስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን የተመለከተው የጎረቤት ቀበሌ ማለትም የግራራም ማርያም ሕዝብም ለእማሆይ ወለተ ማርያም ጥያቄ አቀረበ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በዕድሜ ብዛት ማርጀቱንና በአዲስ መልክ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ፤ ለዚህም ሥራ ወይዘሮ ድንቃየሁ እርዳታ እንዲያስተባብሩላቸው ይጠይቃሉ፡፡ እሳቸውም ሕዝብ በተሰበሰበበት የሕንፃ ቤተ ክርቲያኑን ሥራ ለማስተባበር እርዳታም የሚቻላቸውን ሁሉ ለማፈላለግ ቃል ይገባሉ፡ የአምላክ ፈቃድ ታክሎበት የግራራማ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ይመረቃል፡፡

 

ወይዘሮ ድንቃየሁ በሕልማቸው ሁልጊዜ የሚያዩት ተራራ፣ደን፣ዋሻ ነበር፡፡ ዋሻው በደን (የወደፊቱ እየታያቸው) የተከበበና አራዊት የሚኖሩበት፣ የተለያዩ ጅረቶች የሚፈሱበት፣ በተራሮች አካባቢ እንደሚገኝም ይታያቸዋል፡፡ “የት ይሆን?” እያሉ ያስቡ ነበር፡፡ ያዩትን ሕልም መሠረት አድርገው የአካባቢውን ነዋሪዎችን ”እንዲህ ዓይነት ቦታ አለን? በግራራም ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ክልል ውስጥ ይገኝ ይሆንን?” ብለው ጠየቁ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም “አዎን” ብለው ቦታውን ሊያሳይዋቸው ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞም ያዘጋጀው ቦታ ስለሆነ ገና ሲያዩት የቦታውን ክብር ተረዱ ሕልማቸውም እውነተኛ ሆነ፡፡

 

እማሆይ ወድ ገዳሙ ሲደርሱ የአካባቢው ሰዎችም ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ጅብና የነብር መንጋዎች ግን እማሆይን ሳያተናኮሉ ያላምዷቸው ነበር፡፡እማሆይ የአራዊቱ በቦታው መኖር አላስፈራቸውም፡፡ በእምነታቸው ጸንተው በጻድቃን ሰማዕታትና በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ጥበቃ በጫካ ውስጥ ያሉ አራዊቶች በሙሉ ተገዙላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጽበት ቦታ በመሆኑ እግዚአብሔር እማሆይን መንገድ ጠራጊ አደረገ፡፡

 

ዋሻዎቹ በጥንት ዘመን ሰዎች ከጦርነት ወረራና ጥቃት ለማምለጥ ይጠለሉበት የነበረ መሆኑን አንዳንድ ካህናት ይጠቁማሉ፡፡ ዋሻው ውስጥ የእህል ማከማቻ ጎተራ የምግብ ማብሰያ ሸክላና ማገዶ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁስ ተገኝተዋል፡፡

 

ከዋሻው አናት በላይ ከረጅም ርቀት እየተወረወሩ ቁልቁል የሚፈሱት ጅረቶች መውረጃ መንገዳቸውን ስተው ወደ ዋሻው ውስጥ በመፍሰሳቸው ዋሻው በደለል ተሞልቷል፡፡ ዋሻውን ከደለል አጽድቶ ቅርጽ እንዲይዝ የእማሆይ ቀጣዩ ተግባር ነበር፡፡ ለዚህ ሥራ የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር ደለሉ ተጠረገ፡፡ እማሆይም መኖሪያቸውን ከአራዊት ጋር አደረጉ፡፡

 

እማሆይ ወለተ ማርያም ደለል ጠርገው መኖሪያ ባደረጉት ዋሻ ውስጥ ቀድመው ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ የዱር አራዊት ማታ ከጫካ ሲመለሱ፣ ጥዋት ወደ መዋያቸው ሲሰማሩ በእማሆይ ላይ ምንም ጥቃት አላደረሱም፡፡ በድምፁ የረበሸ፣ ፀጥታ የነፈገ አውሬ ሳይኖር እማሆይና አራዊቱ ዓይን ለዓይን እየተያዩ ለሁለት ዓመታት በሠላም አብረው ቆዩ፡፡

 

ከሁለት ዓመታት የጋራ ኑሮ በኋላ አራዊቱ ዋሻውን ለእማሆይ የብቸኝነት መኖሪያ ለቅቀውላቸው ወደ ሌላ አካባቢ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሰደዱ፡፡እንዲህ አሉ እማሆይ “ አንድ ቀን ጅቦቹና ነብሮቹ ተሰበሰቡ የዛን ቀን ልዩ ነገር አየሁ፤ መሬቱን ጫሩ፣ጮኹ፣አለቀሱ፡፡ ጩኸታቸው እንደዛ ቀን አስፈርቶኝ አያውቅም፡፡ ወዲያው ገዳሙን ለቀው ሄዱ፡፡ ያኔ ፈራሁ አለቀስኩ፡፡ ጓደኞቼ ነበሩና ሲለዩኝ አዘንኩ፡፡” እማሆይ በዚህን ጊዜ ነው የበለጠ የተጨነቁት፡፡ የአራዊቱ መውጣትና መግባት መቆም ለእማሆይ አሳሳቢ ፈተና ነበር፡፡ አራዊቱ ጥዋትና ማታ ሲወጡና ሲገቡ ለእማሆይ እንደ ቅርብ ዘመዶቻቸው ፍቅር አሳድረዋል፡፡ በዓይን በመተያየት ተላምደዋል፡፡ ባለመጣላታቸውና ጉዳት ለማድረስ ባለመሞከራቸው አራዊቱ ለእማሆይ ታላቅ ባለውለታዎች ሆነዋል፡፡ ኀጥዕ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፡፡ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለፍርሃት ይኖራል፡፡ እንዳለ መጽሐፈ ምሳሌ፡፡

 

እማሆይ ወለተ ማርያም ለሁለት ዓመታት በዋሻው ውስጥ ከቆዩ በኋላ በወቅቱ ወደ ነበሩት ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ እርዳታ ጠየቁ፡፡ ለሊቀ ጳጳሱ ስለ ዋሻው ምንነትና የወደፊት መንፈሳዊ ፀጋ አስረዱ፡፡ በመጨረሻም ሊቀ ጳጳሱ ዋሻውን እንደሚያዩላቸው ቃል ገቡላቸው፡፡ በቃላቸው መሠረትም ወደ አካባቢው ተጉዘው ዋሻውንና አካባቢውን ከተመለከቱ በኋላ “ይህማ ገዳመ ቆሮንቶስ ነው፡፡” ብለው እማሆይ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቁ፡፡ እማሆይ ወለተ ማርያምም “የእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ቢሆን እኔ የምመኘው የአባታችንን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትንና የቅዱስ ዑራኤልን ጽላት ቢገባልንና ቢገደም” አሉ፡፡

 

የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ግንቦት 22 ቀን 1987 ዓ.ም የተጠየቁትን ጽላቶች ይዘው ወደስፍራ በመሄድ ጽላቶቹን አስገብተው ገዳም መሆኑን አበሠሩ፡፡ በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ታላቅ በዓል ተደረገ፡፡ በዕለቱ የቅዱስ ዑራኤልና የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፀበሎች ተባርከው ለሕዝቡ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ ፡፡ እማሆይ ገዳሙን አስፍተው፤ሥርዐተ ገዳሙን አጠናክረው በልማት መስክ ተሰማርተው ሳለ “የቅዱስ ዑራኤልን ቤተክርስቲያን ብንሠራ” ብለው አሰቡ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውን አማከሩ፡፡ በገዳሙ የተፈወሱ ወንድሞች ዲዛይኑን ሠርተው በማስረከባቸውና ገንዘብ በማሰባሰባቸው እማሆይም አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለህንጻው የሚሆን የግንባታ ዕቃ በማሰባሰብ በአጭር ጊዜ ቤተክርስቲያኑ ተሠርቶ አለቀ፡፡

 

den ቤተክርስቲያኑን ድንገት ለሚያየው እጅግ ያማረ ሆኖ ደኑን ከጀርባው አድርጎ የበቀለ የሚመስል እጅግ የሚማርክና መንፈስን የሚያድስ ነው ፡፡ በዚያ ቦታ ያንን የመሰለ ቤተክርስቲያን መሠራቱ በእናቶቸ አስተባባሪነት፡፡ ያውም ፊደል ባልቆጠረ፡፡ እኔ ባየሁት ሁሉ ነፍሴ ረክታለች፡፡ ተስፋዬም ለምልሟል፡፡ደግ ሰው! የሃይማኖት ሰው! ታታሪ ሰው! እግዚአብሔር አላሳጣንምና፡፡ ገዳሙን ያስፋልን ሺህ እልፍ ያድርግልን፡፡

 

እማሆይ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ድርጅት ተምሳሌት ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሚለው መጽሐፍ ላይ በደን ልማት፣ በባዮ ጋዝና በትጋታቸው ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋራ ሥራቸውን አቀርቧል፡፡


ይቀጥላል

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/--mainmenu-43/1648-2014-12-17-07-52-57