የማቴዎስ ወንጌል

 

ታኅሣሥ 7 ቀን 2007 ዓ.ም.

ምዕራፍ 11

ዮሐንስ መጥምቅ በግዞት ቤት ሳለ ጌታችን ያደረገውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርት ሰምቶ “ትመጣለህ ብለን ተስፋ የምናደርግህ አንተ ነህ? ወይስ ተስፋ የምናደርገው ሌላ አለ?” ብላችሁ ጠይቁ ብሎ ከደቀመዛሙርቱ ሁለቱን ላከ፡፡ ስማቸውም አካውህ እና እስጢፋኖስ ይባላል፡፡ እኒህ ሁለቱ ተጠራጥረው ስለነበር አይተው አምላክነቱን ይረዱት ብሎ ነው እንጂ እርሱ ተጠራጥሮ አይደለም፡፡ ማቴ.14፡3፣ ዘዳ.18፡18፣ ዮሐ.6፡14፡፡


ጌታችንም “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውራነ ሥጋ፣ ሐንካሳነ ሥጋ፣ ልሙፃነ ነፍስ እና ሙትነ ነፍስ ደግሞ በትምህርት ይድናሉ፡፡ ነዳያነ ሥጋ በተአምራት፣ ነዳያነ ነፍስ በትምህርት ይከብራሉ፡፡ በእኔም የማይሰናከል ማለትም ሰውነቴን አይቶ ዕሩቅ ብእሲ ነው የማይለኝ ንዑድ ክቡር ነው” አላቸው ኢሳ.35፡5-6፣ 61፡1፣ ማቴ.13፡57፣ 26፡31፡፡


ጌታችን ከዮሐንስ ተልከው የመጡት ከሄዱ በኋላ የዮሐንስ መጥምቅን ነገር ማለትም ከነቢያት እንደሚበልጥ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለተናገረለት ትንቢት እና ከሴቶችም ከተወለዱት መካከል ከእርሱ የሚበልጥ እንዳልተነሣ ለሕዝቡ ነገራቸው፡፡ ይህንን እና ሌላም ተጨማሪ ነገር ከነገራቸው በኋላ “ብትቀበሉት ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፡፡ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” ብሏቸዋል፡፡ እንዲህም ማለቱ መጥምቁ ዮሐንስ ነቢዩ ኤልያስን ስለሚመስለው ነው፡፡


የመላእክት አለቃ ቅዲስ ገብርኤል ጻድቁ ካህን ዘካርያስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን እንደሚወልድ የምሥራቹን ነግሮት ነበር፡፡ ስለ ሕፃኑም ማንነት ገና ከመፀነሱ በፊት ሲነግረው “እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፣ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል” ብሎታል፡፡


መጥምቁ ዮሐንስ ነቢዩ ኤልያስን በምን ይመስለዋል ቢሉ ኤልያስ ፀጉራም ነው፡፡ ዮሐንስንም ልብሱ የግመል ፀጉር ነበረ ይለዋል፡፡ ኤልያስ ጸዋሚ፣ ተሐራሚ፣ ዝጉሐዊ፣ ባሕታዊ ነበር፡፡ ዮሐንስንም ጸዋሚ፣ ተሐራሚ፣ ዝጉሐዊ፣ ባሕታዊ ይለዋል፡፡ ኤልያስ መገሥፀ አክዓብ ወኤልዛቤል እንደሆነ ዮሐንስም መገሥፀ ሄሮድስ ወሄሮድያዳ ነውና፡፡ ኤልያስ ለደኃራዊ /ለኋለኛው/ ምጽአቱ መንፈቅ ተቀድሞ እንደሚያስተምር ዮሐንስም ለቀዳማዊ ምጽአቱ መንፈቅ ተቀድሞ አስተምሯልና፡፡


ጌታችን ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ከነገራቸው በኋላ ቃሉን ባልሰሙትና ትምህርቱን ባልተቀበሉት ሰዎች ላይ “እንቢልታን ነፋንላችሀ ዘፈንም አልዘፈናችሁም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም” ብሎ በምሳሌ ተናግሮባቸዋል፡፡ እነርሱም ጸሐፍት ፈሪሳውያን ናቸው፡፡ ምክንያቱም “አልዘፈናችሁም” ሲል በትምህርቱ በተአምራቱ አለመደሰታቸውን ሲያመለክት፣ “ዋይ ዋይም አላላችሁም” የሚለው ደግሞ ስለ ኃጢአታቸው አለማዘናቸውን ያመለክታል፡፡


ከዚህም ጋር የዮሐንስን አመጣጥ እና የእርሱን አመጣጥ ከነገራቸው በኋላ “ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች” ብሏቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ጥበብ ያለው እራሱን ሲሆን ልጆችዋ ያለው ደግሞ ሥራውን ነው፡፡ ይህም ወልድ በሥራው /በተአምራቱ/ ከበረ ማለት ነው፡፡ እውነትን ላለመቀበል ምክንያት እንደሚያበዙም ሲነግራቸው “ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ ቢመጣ ጋኔን አለበት አሉት፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ስለመጣ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፣ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል” ብሏቸዋል፡፡ ከዚያም አያይዞ ብዙ ተአምራት ተደርጐላቸው ንስሐ ገብተው ወደ ማመን ያልመጡትን የኮራዚ፣ ከተሞች ወቅሷቸዋል፡፡


በመጨረሻም “ጥበበኞችና ዐዋቂዎችን ነን” ከሚሉ ጸሐፍት ፈሪሳውያን የተሰወረ ምሥጢር ለሕፃናት /ለደቀመዛሙርቱ/ እንደተገለጠላቸው ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም” ብሏቸዋል፡፡ ይህም፡-


1ኛ. “ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጠኝ” ሲል መለኮት በማኅፀን ሥጋን በተዋሐደ ጊዜ ሥጋ ሥልጣን ማግኘቱን የሚያጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረ በተዋሕዶ ጊዜ ሥጋ የቃልን ቃልም የሥጋን ሀብት ገንዘብ አደርገዋልና፡፡


2ኛ. “ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም” ሲል አብን ወላዲ ካላለ ወልድን ተወላዲ ብሎ የሚያምን የለም፡፡ አንድም አብ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሳይመሰክር በፊት ወልድን የሚያውቀው አልነበረም፡፡ አንድም ያለ አብ ወልድን በባሕርዩ የሚያውቀው የለም ማለት ነው፡፡


3ኛ. “ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም” ሲል ወልድን ተወላዲ ካላለ አብን ወላዲ የሚል የለም፡፡ አንድም ወልድ “ከአብ ወጥቼ መጣሁ፣ አባቴ ላከኝ እኔን ያየ አብን አይቷል፣ እኔ እና አብ አንድ ነን” ብሎ ሳይመሰክር በፊት አብን የሚያውቅ አልነበረም፡፡ አንድም ያለ ወልድ አብን በባሕርይ የሚያውቀው የለም፡፡ ወልድ ሊገልጽለት ለወደደው ይገልጽለታል እንጂ ማለት ነው፡ ዮሐ.6፡46፣ 7፡28፣ 29፣ 8፡19፣ 10፡15፡፡


ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 4ኛ ዓመት ቁጥር 7 ነሐሴ 1980 ዓ.ም.

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/---mainmenu-27/1646-2014-12-16-09-19-50