ዛሬም ያልታጠፉ እጆች ያልዛሉ ክንዶች

 ኅዳር 24 ቀን2007 ዓ.ም. 

 መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

aba mef1

በደቡብና በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከቶች የቅዱስ ጳውሎስን “ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ መልእክት በተግባር የሚኖሩ፤ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ንጹህ ስንዴን የዘሩ ትጉህ መምህር፣ ቀናዒ ለሃይማኖታቸው ፣ በርቱዕ አንደበት መምከርን፣ በትጋት ማስተባበርን፣ ከሚዘምሩት ጋር መዘመርን፣ ከሚያመሰግኑት ጋር ማመስገንን፣ ከሚያዝኑትም ጋር ማዘንን ግብር አድርገው፤ እንደ ሕፃን ከሕፃናት ጋር፣ እንደ ወጣት ከወጣቶች ጋር እንደ አበው ደግሞ ከሊቃውንት ጋር ተዋሕደው ቤተክርስቲያን እያገለገሉ ይገኛሉ::


እንዲመሰገኑ ሳይሠሩ፣ አስበው ተስፋ ሳይቆርጡ፣ ሠርተው ሳይደክሙ፣ ሰለችተው ሳያርፉ፣ አንዱን ሳይጨርሱ ስለሌላው እያሰቡ፣ ድንበርና ደብር ሳይገድባቸው፣ በዓላት በድምቀት ለመከበራቸው ምክንያትና ለሥራዎች ስኬታማነት ዋስትና ሆነው፣ ሲለምኑ አንጀት እያራሩ፣ የደከሙትን እያበረቱ፣ የተሳሳቱትንም እየገሰፁ ሁሉንም በፍቅር የማከናወን ጸጋ የተሰጣቸው፣ የ86 ዓመት አዛውንት ዛሬም ያልታጠፉ እጆች ያልዛሉ ክንዶች አገኘን ከደሴ ከተማ::

 

አባ መፍቀሬ /ባህታዊ መፍቀሬ ሰብእ ኪዳነ ወልድ ይባላሉ፡፡ የተወለዱት በ1921 ዓ.ም. ሰሜን ሸዋ ተጉለት ወርቅጉር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አለቃ ወርቅ አገኘሁ አገር ገዳምዬ ሚካኤል ፣ድንቡይ ጊዮርጊስ (አባ መፍቀሬ እንደነገሩን) ነበር:: በልጅነታቸው በገዳምዬ ሚካኤል ለዲቁና የሚያበቃውን ትምህርት ከተማሩ በኋላ ከግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ እጅ ዲቁናን ተቀብለው በአካባቢያቸው ባሉ አብያተክርስቲያናት እስከ 14 ዓመታቸው ድረስ ሲያገለግሉ ቆዩ፡፡
ከዚያ በኋላ ጥልቁንና አድካሚውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው ከሊቃውንት ጐራ ለመመደብ ቤተሰቦቻቸውን ትተው በ1935 ዓ.ም. ወደ በጌምድር / የአሁኑ ጎንደር/ ሄዱ፡፡

 

ጎንደር እንደደረሱ የፆመ ድጓ ትምህርታቸውን እየተማሩ የተወሰኑ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ በዙሪያቸው የፈራረሱ አብያተ ክርስቲያናትን በማየታቸው እጅግ ያዝኑና ይተክዙም ነበር፡፡ አንዳንዴም በመቆጨት “እንዴት ሕዝበ ክርስቲያን እያለ ቤተ ክርሰቲያን ይፈርሳል” እያሉ ይናገሩ ነበር፡፡ ያማከሯቸውም ሰዎች ከንፈር ከመምጠጥ ያለፈ ምላሽ ሊሰጧቸው ባለመቻላቸው ግራ ይጋቡ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እየቆዩ ሲሄዱ አንድ የጐደለ ነገር እንዳለ በመገንዘብ ከንፈር መምጠጥና ማዘን ብቻ የሚፈይደው አንዳች ነገር እንደሌለ ተረድተው፤ በድፍረት ወደ አውደ ምሕረት በመውጣት ሕዝቡን በመቀስቀስና በማስተማር አብያተ ክርስቲያናትን ማሠራት ጀመሩ፡፡ የተጠሩት ለዚህ ነውና::

 

የውጤታማነታቸው ዜና በአካባቢው በስፋት በመወራቱም ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ እርሳቸው እየመጣ “እባክህ በዚህ አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ፈርሷልና ሕዝቡን ቀስቅስልን” እያሉ ይጠይቋቸው ስለነበረ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ አብያተ ክርስቲያናትን ማሠራት ጀመሩ፡፡ይህም አዲሱ አገልግሎት ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ለመመለስ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን ዘግይተውም ቢሆን ለተረዱት ለባሕታዊ መፍቀሬ ሰብዕ ሊለቁት የማይችሉት የነብር ጅራት ሆነባቸው፡፡ የጓጉለትንና ከትውልድ ቀያቸው የተሰደዱለትን ትምህርት ትተው በጎንደር አብያተ ክርስቲያናትን ማሠራትን ቀጠሉ፡፡

 

አብያተ ክርስቲያናትን የማሠራትና የማሳደስ አገልግሎት

 

ባሕታዊ መፍቀሬ ሰብእ በጎንደር፣ በአንዳ ቤት በሙጃ፣ በዙር አምባ ወዘተ እየተዘዋወሩ አብያተ ክርስቲያናትን ማሠራት ጀመሩ:: ወደ ወሎ በመምጣት ቆቦ መድኃኔዓለምና ወልድያ ኪዳነ ምሕረት አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበር አሠርተዋል፡፡አለማጣ መድኃኔዓለምና ወልድያ መድኃኔዓለም አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ሕዝቡን በመቀስቀስና በማስተባበር እንዲሁም ውጫሌ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ከግብፁ አቡነ አትናቴዎስ ጋር በመሆን ያሠሩ ሲሆን ባቲ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ ሕዝቡን በማስተባበር አሠርትዋል፡፡ 

 

ኮምቦልቻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ከአቶ ተክሌ ዕቁባይ እና ከሌሎች ምእመናን ጋር በመሆን ከደሴ ኮምቦልቻ በቀን እስከ 3 ጊዜ እየተመላለሱ አሠርትዋል፡፡ ባሕታዊ መፍቀሬ ሰብዕ ችግር ባለበት ቦታ ላይና አስተባባሪ ያሻዋል ብለው ባመኑበት ሁሉ ያስተባብራሉ::የሚሠራ ቤተ ክርስቲያን አይተው ሳያስተባብሩ፣ ሳይቀሰቅሱና ልምዳቸውን ሳያካፍሉ አያልፉም፡፡

አባ መፍቀሬ በአገልግሎት ዘመናት ሁሉ ስለ ቆቦ መድኃኔዓለም ማውራት ይወዳሉ፡፡ ታሪኩም እንዲህ ነው፤ ጥንት ከደሴ ወደ ላሊበላ የሚኬደው በቆቦ በኩል ዞሮ ነበርና ወደ ላሊበላ ለክብረ በዓሉ ለሚያገለግል የማሾ ማብራት (የሚገለገሉት በማሾ ነበር) ነጭ ጋዝ ከደሴ ገዝተው ሲሄዱ እግረ መንገዳቸውን ቆቦ አረፉ፡፡ ከዚያም ዕቃቸውን አስቀምጠው ቆቦ መድኃኔዓለምን ሊሳለሙ ይሄዳሉ፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሲደርሱ የፈራረሰውን የቆቦ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ከብቶች ከፀሐይ ተጠልለውበት ያገኙታል፡፡

 

አባ መፍቀሬ “አዬ መድኃኔዓለም ዛሬም በከብቶች በረት ነው ያለኸው” ብለው “እባክህ ፈጣሪዬ ይህን ቤተ ክርስቲያን እንድሠራ ፍቀድልኝ” ብለው ተመኙ፡፡ ከዚያም ቤተ ክርስቲያኑን ተሳልመው እንቅልፍ ሸለብ ያደርጋቸዋል፡፡ በህልማቸው አንድ ሕፃን ልጅ መጥቶ “አንተ የቆቦ መድኃኔዓለምን እንድትሠራ ተፈቅዶልሃል” ይላቸዋል፡፡ ቢነቁ በአጠገባቸው ምንም የለም፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ስለተረዱ ሥራውን ጀምረው በግሩም ሁኔታ አጠናቀቁ፡፡

 

abamef5 በደሴ ከተማ ለቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ እንዲሰጡቸው የተለያዩ ሰዎችንና ባለሥልጣናትን በተለያዩ ጊዜያት ጠይቀው ሳያሳካላቸው ቀርቷል፡፡ሆኖም ግን ፈጣሪአቸው ይህን ቦታ ለቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ይሰጣቸው ዘንድ ለ30 ዓመታት ሲጸልዩ ቆይተዋል፡፡ ልመናቸውም ምላሽ አግኝቶ ከ30 ዓመታት በኋላ ቦታውን በመረከብ ሕንፃው በበጐ አድራጊዎች እንዲሠራ አስተባብረዋል፡፡ አባ መፍቀሬ የደሴ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የደሴ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ፣ የደሴ ቅድስት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያንን አሠርተዋል፡፡ 

የደሴ መንበረ ፀሐይ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የቀደመ ቦታው ተንዶ ከፈረሰ በኋላ አዲስ የሚሠራበትን ቦታ ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን ለማረጋገጥ ባህታውያን ሱባኤ እንዲይዙላቸው ለማሳሰብ ጎንደር ድረስ ሄደዋል፡፡ ከዚያ እንደተመለሱም የቀድሞውን መቃረቢያ ቤተ ክርስቲያን አሠርተው አሁንም በመጠናቀቅ ያለውን ቤተ ክርስቲያን እያሳነፁ መሆኑ ፡፡

 

የደሴ ደብረ ቤቴል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ያሠሩት ከ30 ዓመታት በላይ ገንዘብ በማሰባሰብና ምእመናንን በማስተባበርና ከማገልገላቸው በተጨማሪ “ዝክረ መፍቀሬ ሰብእ” በሚለው መርሐ ግብር ራሳቸውን ለሽያጭ(ፎቶአቸው) በማቅረብ ሕዝቡም ለአባ መፍቀሬ ካለው ፍቅርና አክብሮት የተነሳ ከ1.2 ሚሊየን ብር በላይ በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲሰባሰብ ምክንያት የሆኑ አባት ናቸው፡፡
የደሴ ደብረ ቤቴል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ለባህታዊ መፍቀሬ ሰብእ የልጅነት ህልማቸውን እውን ያደረገላቸው፣ በውስጣቸው የነበረውን መንፈሳዊ ቅንዐትም የፈፀመላቸው ነውና “ዳግማዊ ላሊበላ” እያሉ ይጠሩታል፡፡ በስስት ዓይን የሚያዩት እንደ ልጅ ወልደው ያሳደጉትና ፍጻሜውንም ለማየት ሲጓጉለት እንደነበረ ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

 

የአፀደ አብያተ ክርስቲያናት ተከላና እንክብካቤ አገልግሎት

 

የደን ልማት ለአባ መፍቀሬ ልዩ ፀጋ ነው፡፡ደንን ያለ አግባብ የሚቆርጥና የሚጨፈጭፍ ከአባ መፍቀሬ ጋራ ይጣላል፡፡አበ መፍቀሬ ዛፍ ተክለው ጠዋትና ማታ ይንከባከቡታል፡፡ለሕዝቡም ስለ ደን ጥቅም ያስረዳሉ፡፡ ይህን አገልግሎት ከጀመሩ 56 ዓመት የሆናቸው አባ መፍቀሬ ወደ አገልግሎቱ መጀመሪያ የገቡት ላሊበላ ነበር፡፡

 

የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲመለከቱ እጅግ በመገረም እና በመደነቅ “ፈጣሪዬ ይህን ካሳየኸኝ፤ ከእንግዲህ ወደ ሀገሬ አልመለስም፡፡” ብለው ቃል በመግባት ላሊበላ በተቀመጡበት ወቅት በዚህም በላሊበላ አካባቢ ሞላ የተባለ አህያ ገዝተው በአህያው ውሓ እያመላለሱ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዋንዛና ሾላ ተክለው በማሳደጋቸው ዛሬ ለከተማው ውበትና ማረፊ ሆኗል፡፡

በቆቦ ከ40 ሺ በላይ ችግኝ ተክለው አሳድገዋል፡፡በግሸን ደብረ ከርቤም በተለይ በእግዚአብሔር አብና በእመቤታችን ቅድስት ማርም ቤተክርስቲያን በርካታ ዛፎችን ተክለዋል፡፡በተጨማሪም አለቃ መዝሙር የተባሉ ሰዓሊ ግሸን ይዘው በመሄድ ቅዱሳት ሥዕላትን ለማሠራት 6 ወር ተቀምጠዋል፡፡

 

ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ በደሴ ደብረ ቤቴል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ በደሴ ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ኤልያስ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ የደን ልማት መርሐ ግብር ሥራ ዘርግተዋል፡፡ በተጨማሪም በሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዓ ገዳም ዛሬ ለምእመናንን ማረፊያ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት ትላለቅ ዋርካዎች እና ሸብሀዎች የተተከሉት በአባ መፍቀሬ ነው፡፡

 

በደን ልማት ተግባር ያላቸውን ጥልቅ እውቀት ብዙ የግብርና ባለሙያዎች ያደንቁላቸዋል፡፡በሌላ በኩል የቀድሞው ፓትርያረክ ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት “እንዲህ ነው ባሕታዊ” በሚል ርዕስ ሥራቸውን በጋዜጣ እንዲወጣ አድርገዋል፡፡ ሐመር እና መለከትንም ጨምሮ በርካታ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ስለ ሥራቸው ምስክርነት የሰጡ ሲሆን ለዚህ አገልግሎታቸው እውቅና በድርጅቶችና በመንግሥትም ከወረዳ እስከ ክልል ለመሸለም መብቃታቸው ለትጋታቸው የተሰጠ ማረጋገጫ ነው፡፡

 

በዓላትን በድምቀት የማስከበርና የማስተባበር አገልግሎት


ባሕታዊ መፍቀሬ ሰብዕ የቤተክርስተያንን በዓላት የማድመቅ አገልግሎት የጀመሩት ከዛሬ 53 ዓመት በፊት ላሊበላ ላይ የቅዱስ ላሊበላን ዕረፍት በዓል ሰኔ 12 ቀን ታቦት ወጥቶ እንዲከበር በማድረግ ጀምረዋል፡፡ ለጥምቀት በዓል በተለያዩ ድንኳኖች ይወጡ የነበሩትን የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት በአንድ ቦታ እንዲያድሩ በማሰብ ከደብሩ 3300 ብር አስፈቅደው በገዙት ቦታ በአንድ ላይ የጥምቀተ ባህሩ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ abamef4

 

በዚህም በቅዱስ ላሊበላ ባከናወኗቸው ተግባራት መነሻነት ሕዝቡ በጣም ይወዳቸው ስለነበርና በወቅቱ ልጅ ስለነበሩ “አባ ሕፃን” እያሉ እንደሚጠሯቸውና ትርጓሜውም “የላሊበላ ልጅ” ወይም “ሕፃን ዘላሊበላ” ማለት እንደሆነና በዚህም ስያሜ እስከ አሁን እንደሚጠሩበት ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ ባህታዊ መፍቀሬ ሰብእ በግሸን፣ በላሊበላ እንዲሁም በአጠቃላይ በደቡብና በሰሜን ወሎና በአካባቢው የሚገኙ መንፈሳዊ በዓላትን በሙሉ በግንባር ቀደምትነት የሚመሩና የሚያስተባብሩ ናቸው፡፡
ብዙዎች “ያለ አባ መፍቀሬ ሰብዕ በዓላት አይደምቁም” እንደሚሉት ኦርቶዶክሳዊ በዓላት ሥርዓታቸውና ትውፊታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለዚሁ ተግባር ሲሉ እንደ በዓሉ ይዘት የሚገለገሉባቸውንና ያዘጋጇቸውን አበባዎች፣ ሰንደቅ ዓላማዎች፣ መጋረጃና፣ ጥሩምባ ወዘተ ገዝተው በማስቀመጥ ለግዳጅ ዝግጁ እንደሆነ ወታደር ይዘው ይጓዛሉ፡፡

 

በዓውደ ምህረት የመስበክና የማስተማር አገልግሎት

 

ከ57 ዓመት በፊት ግሸን ላይ ከአቡነ ሚካኤል የማስተማር ፈቃድ ተሰጥቷቸው በጎንደርና በወሎ በአብዛኛው ቦታዎች እየተዘዋወሩ አስተምረዋል፡፡ ባሕታዊ መፍቀሬ ሰብዕ ዛሬም ለማስተማር ሲነሱ አንደበተ ርቱዕ ከመሆናቸው ሌላ የትምህርቶቻቸው ይዘትም በአብዛኛው ከአገልግሎታቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናትን ስለ ማነፅ፣ አፀደ አብያተ ክርስቲያናትን ስለ መትከልና መንከባከብ፣ ለቅርሶች መደረግ ስላለበት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ስለ መንፈሳዊ በዓላት አከባበርና ወጣቶችን ከመናፍቃን ሴራ ስለመታደግና ከአምልኮ ባዕድ ተግባራት ስለመራቅ በአፅንኦት ያስተምራሉ፡፡

ባሕታዊ መፍቀሬ ሰብእ መመስገን ያለበትን ለማመስገንና የተሳሳቱትን ለመውቀስ ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸውን ስሜታቸውን በሽንገላ ለመደበቅ የማይችሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በተለይም ደስታቸውን በዓውደ ምሕረት ላይ እንደ ሕፃን በመቦረቅ የመግለጻቸውን ያህል በሀዘን ጊዜ እንባቸው ቅርብ የመሆኑ ምስጢር ከብዙዎች ሰባክያንና መምህራን ልዩ የሚያደርጋቸው ባህሪያቸው ነው፡፡

 

ወደ ገዳማትና አድባራት የሚያስገቡ መንገዶች ሥራ አገልግሎት

 

abamef3 ባሕታዊ መፍቀሬ ሰብዕ ይህን አገልግሎት ከዛሬ 35 ዓመት በፊት የጀመሩት ሲሆን በወቅቱ የነበሩትን የደርግ ባለ ሥልጣናት በማግባባትና በማሳመን የግሸን ደብረ ከርቤ መንገድ እንዲሠራ ማድረግ መቻላቸው የኒህንን አባት ጥበብ እና አስተዋይነት የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡ ይህ መንገድ ከተሠራበት ከ1972 ዓ.ም. ጀመሮ እስከ አሁን ድረስ በየዓመቱ የየመሥሪያ ቤቱን በር በማንኳኳት በየግለሰቦች ቤት በመሄድ ለመንገዱ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ፡፡ 

አባ መፍቀሬ በአገልግሎት ዘመናቸው የራሴ የሚሉት ምንም ነገር የሌላቸው ሲሆኑ ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ በወሎ ሀገረ ስብከት ተመድበው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ዛሬም አባ መፍቀሬ ብርቱና ጠንካራ ናቸው፡፡

 

 

 

ምንጭ፡-
• ትንቢት መጽሔት መስከረም 2004 ዓ.ም.
• የቃል አስረጅ

 

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/--mainmenu-43/1631-2014-12-03-09-36-38