ከ2004- 2007 ዓ.ም. በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት 16,630 አዳዲስ አማንያን ተጠመቁ

 ኅዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

jinka tim02 2 የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመተባበር ከ2004- 2007 ዓ.ም. 16,630 አዳዲስ አማንያንን በማስተማር መጠመቃቸውን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡


ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ቅዳሴ ቤቱ ሲመረቅም በሀገረ ስብከቱ እና በማኅበረ ቅዱሳን አማካይነት የቀረቡትን 1350 አዳዲስ አማንያን በቅዱስነታቸው እና በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነትን አግኝተዋል፡፡


ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት ቃለ ምእዳን “ይህ ቀን የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የተፈጸመበት ቀን ነው፡፡ የመድኀኔዓለምን ቤተ ክርስቲያን ገንዘባችሁን፤ እውቀታችሁንና ጉልበታችሁን አስተባብራችሁ የሠራችሁበትና 1350 አዲስ ክርስቲያኖች የተጨመሩበት ቀን ስለሆነ ለቤተ ክርስቲናችን ታላቅ የደስታ ቀን ነው” ብለዋል፡፡


የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉኀን ወንድወሰን ገ/ሥላሴ የዕለቱን መርሐ ግብር ሲያስተዋውቁ ከ2004-2007 ዓ.ም. ድረስ ሀገረ ስብከቱ ከማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል ጋር በመተባበር 16,630 አዳዲስ አማንያንን በማስተማር እንዲጠመቁ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም ከታቀደለት ጊዜ በፊት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


jinka tim02 1 የጂንካ ደብረ ቀራንዮ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጀማል ዑመር /ዐምደ ሚካኤል/ ባቀረቡት ሪፖርት የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እገዛ ላደረጉ ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በተመለከተም ሲገልጹ “የወንጌል አርበኞች የሆኑት የማኅበረ ቅዱሳን ጂንካ ማእከል አባላት የቤተ ክርስቲያኑን ዲዛይን በነጻ በመሥራት እገዛ አድርገዋል” ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1604-2004-2007-16630-