ዳገቱን መወጣት ግድ የሚለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት

ታኅሣሥ 23 ቀን 2007 ዓ.ም.

 •    ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል መምሪያ የበላይ ሓላፊ ከስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

 

abune markos gojam ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷን፣ ሥርዓቷንና ትውፊቷን ከምታስተላልፍባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር ታላላቅ ነቢያትን፤ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን እያስነሣ ሲመክር፣ ሲገሥጽ፣ እውነተኛውን መንገድ በአባቶቻችን ላይ አድሮ ሲመራ እንመለክታለን፡፡

 

አባቶቻችን ነቢያት ሱባኤ እየገቡ፤ ምሥጢር እየተገለጠላቸው ስለትናንቱ አገልግሎትና ወደፊት ስለሚሆነው ሁሉ በብዙ ምሳሌ አስተምረዋል፡፡ በኋላም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመረጣቸው ሐዋርያት በአንድ ጊዜ ሦስት ሺሕ አማንያንን ማስገኘት ችለዋል፡፡ ለዚህም የአባቶቻችን ሕይወትና ቅዱሳት መጻሕፍት ምሥክሮች ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የክርስትና ሃይማኖትን ከተቀበለችበት ጊዜ አንሥቶ ወንጌልን ያልሰበከችበት ወቅት የለም፡፡ በተለይ የሐዋርያት አብነቶች የሆኑት የመካከለኛው ዘመን የወንጌል አርበኞች ለዚህ ምስክሮቻችን ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ቤተ ክርቲያን ችግር ላይ በነበረችበት ዘመናት እንኳን በየጫካውና በየዋሻው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ አባቶቻችን ለምእመናን ወንጌልን ለማዳረስ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ከፍለው አልፈዋል፡፡ እነሱ የዘሩት ዘር ዛሬም ሳይደርቅ ፍሬ በማፍራት ላይ ይገኛል፡፡

 

ምንም እንኳን እርሾው ባይነጥፍም በቤተ ክርስቲያናችን አሁን ያለውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በምንዳስስበት ጊዜ በእውኑ ቤተ ክርስቲያን በስብከተ ወንጌል መድረስ የሚገባትን ያህል ሔዳለች ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ምእመናኑንስ በስብከተ ወንጌል ማርካት ተችሏል ወይ? እውን አሁን ያለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ያለ ነው? የምእመናን ሕይወትስ ምን ይመስላል? ይህንን ሓላፊነት ወስዶ እየሰራ ያለው የስብከተ ወንጌል መምሪያ ምን ምን ተግባራት እያከናወነ ይገኛል? የሚሉትና በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ዙርያ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጐጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በጠቅላይ ቤተ ክህት የስብከተ ወንጌል መምሪያ የበላይ ሓላፊ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡

 

ዛሬ ላይ ያለውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዴት ያዩታል?

 

በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እየተሰጠ ያለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንደተጠበቀው አይደለም፡፡ ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡትን ያህል በቤተ ክርስቲያናችን የሚሰጠው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በሌሎች መርሐ ግብሮች የተዋጠ ነው፡፡ ካህናቱና መምህራኑ ከስብከተ ወንጌል አገልግሎት ይልቅ በማኅሌቱና በዜማ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ወንጌሉንና የቤተ መቅደስ አገልግሎቱን ጐን ለጐን ማስኬድ አልተቻለም፡፡ ወንጌል ለሃይማኖት፣ ለሥነ ምግባር፣ ለሰላም ያለው ስፍራ ከፍተኛ ነው፡፡ የሰው ሕይወትም የሚስተካከለው ወንጌል ሲሰበክ ነው፡፡ የሰው አእምሮ በወንጌል ካልታረሰ አይለማም፡፡ በወንጌል ካለማ ደግሞ ያልታረሰ መሬት ወይም ጫካ ይሆናል፡፡ ባልታረሰ መሬት ላይ እህል ቢዘሩ ትርፉ ድካም ነው፡፡

 

ምእመናን ፈጣሪያቸውን ዐውቀው ለተራቡት የሚያበሉት፣ ለተጠሙት የሚያጠጡት፣ በሃይማኖታቸው ጸንተው የሚቆሙት፣ ፈቃደ ሥጋ ለፈቃደ ነፍስ እንዲገዛ ማድረግ የሚችሉት ወንጌል ሲሰበኩ ነው፡፡ በእኔ እይታ የስብከተ ወንጌል በሌሎች አገልግሎቶች የተወጠ ነው፡፡ ምእመናን በሚፈልጉት ልክ አልሠራንበትም፡፡ መድረኩን የሚይዙትም በሕይወታቸው የሚሰብኩ፣ እኔን ምሰሉ የሚሉ አይደሉም፡፡ ወንጌል ከመናገር ይልቅ በመሆን ሲሰበክ ነው ፍሬ የሚኖረው፤ ስለዚህ ገና ነን ብዙ ይቀረናል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅማ ስብከተ ወንጌልን በማዳረስ ረገድ ወደ ኋላ ቀርታለች የሚሉም አሉ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

 

ቤተ ክርስቲያን በስብከት አገልግሎት ወደ ኋላ ቀርታለች ማለት አይቻልም፡፡ በቴክኖሎጂው እስከ ዛሬ አለመጠቀሟ እውነት ቢሆንም ስብከተ ወንጌሉ ግን እየተሠራበት ነው፡፡ በእርግጥ ቴክኖሎጂው በአንድ ጊዜ ብዙ ምእመናንን ለማግኘትና ለመድረስ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የስብከተ ወንጌል ዓላማ በምእመናን (በተሰባኪው) ሕይወት ላይ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በቴክኖሎጂው ስለተሰበከ ለውጥ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ በቅድሚያ ለእግዚአብሔር የሚመች ሕይወት አለን ወይ ነው ጥያቄው፡፡ እንደቀደሙት አባቶቻችን የክርስትናው ሕይወት ሲኖረን ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው፡፡ እንጂ ቴክኖሎጂው ብቻውን ለውጥ አያመጣም፡፡


ልጆች ለእናት ለአባታቸው ታዝዘው፤ በሥነ ምግባር ታንጸው በእግዚአብሔር ሕግ ሲኖሩ መስተካከል ይችላል፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ የተደበላለቀ ነው፡፡ ልጆች አዋቂዎች ነን የሚሉበት፤ እናትና አባት ተሰሚነት ያጡበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ይህም ወጣቶች እምነታቸውን ጥለው ወደ አዳዲስ የእምነት ተቋማት በተለያየ ስልት እንዲወሰዱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመገናኛ ብዙኀን መሰበኩ መልካም ቢሆንም የቤተ ክርስቲናችን ትምህርት ጽናትን፤ ጾም ጸሎትንና ትእግሥትን ይጠይቃል፡፡ በዘመናችን ደግሞ መጾም፤ መጸለይ እንደኋላ ቀርነት እየታየ ነው፡፡


ስለዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥቅሙ ለሰው በቀላሉ ስለሚደርስ እንጂ የትምህርት እጥረት ኖሮ አይደለም ተመራጭ የሚሆነው፡፡ ሙሉ አገልግሎቱ በቤተ ክርስቲያናችን ዛሬም ሳይቋረጥ ሥርዓቱን እንደጠበቀ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ትምህርት የሚባለው ትምህርቱን መጥኖ በማቅረብ፤ ለምእመናን በሚመች መልኩ በማስተማር የጊዜ አጠቃቀማችንን ልናሻሽለው እንችላለን እንጂ ሃይማኖቱ ይዘምናል ማለት አይደለም፡፡ ሃይማኖት አንዲት ናት፤ የማትለወጥ የማትሻር፡፡ አባቶቻችን በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ያቀኗትና ልክ አበጅተውላት ትናንትም ዛሬም ነገም ለዘላለሙ የማትለወጥ ሃይማኖት ናት ያለችን፡፡


የዘመኑን ቴክኖሎጅ ተጠቅመን ትምህርተ ወንጌሉን ለሁሉም ለማድረስ ግን በእቅድ ላይ ነን፡፡ በቅርቡ ወደ ተግባር እንገባለን ባይ ነኝ፡፡ አገልግሎታችን ግን ከምእመናን ሕይወት ጋር አብሮ እንዲሄድ በማድረግ ማኅሌቱ፣ ቅዳሴው፣ የስብከት አገልግሎቱ በተያዘላቸው ጊዜና ሰዓት ጠብቆ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡


በአሁኑ ጊዜ በዐውደ ዓመት ላይም ሆነ በወርሃዊ በዓላት ስብከተ ወንጌል ላይ ትኩረት ማድረግ ሲገባ መድረኩ ለልመና ሲውል ይታያል፡፡ በዚህ ላይ ምእመናን ሲያማርሩ ይሰማል፡፡ የእርስዎ አሳብ ምንድን ነው?

 

በዚህ ጉዳይ ላይ እኔ ራሴ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በጣም ከማዝንባቸው ነገሮች አንዱ ነው፡፡ እባካችሁ መድረኩን የልመና መድረክ አታድርጉት ሲባል አይሰሙም፡፡ በመምሪያ ደረጃም ይህንን ለማስቆም በሚያጋጥመን ቦታ ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ምእመናን እግዚአብሔርን ፍለጋ ነው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡት፡፡ ልመና በየአካባቢው ሰልችቷቸዋል፡፡ በእውነቱ ምእመናን በዚህ ጉዳይ በመማረራቸው ምክንያት መስማት የሚገባቸውን ቃለ እግዚአብሔር ሳይሰሙ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ ይህ ትልቅ ድክመት ነው፡፡


ወደፊት እንደ ስብከተ ወንጌል መምሪያ በአዲስ አበባ ላይ መድረክ ፈጥረን የሁሉንም አድባራትና ገዳማት ሰባኪያንን ሰብስበን ለመምከር አስበናል፡፡ መመካከር ብቻም ሳይሆን ወጥ የሆነ መመሪያ አዘጋጅቶ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በእውነት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት ከሆኑት ነገሮች አንዱ መድረኩን ለልመና ማዋላችን ነው፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በቤተ መቅደስ በክብር አምልኮት የሚፈጸምባቸው በማእጠንት የከበሩ ቅዱሳት ሥዕላት በየሜዳውና በየታክሲው ቅጥ ባጣ ሁኔታ ተዘርግተው መለመኛ ሆነው ማየት ያሰቅቃል፡፡ ይሔን ሁላችንም ማስተካከል እንችል ነበር ግን አንዱ አንዱን ሲጠብቅ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ሊቀጥል ችሏል፡፡


በተለይ ለወጣቶቻችን የማስተላልፈው ነገር ቢኖር ለሃይማኖታቸው ቀናተኞች በመሆናቸው ከሥራዓት ውጪ የሚሆኑትን በመምከርና በመገሰጽ ወደ ትክክለኛው አገልግሎት መስመር እንዲገቡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በየመንገዱ ቅዱሳት ሥዕላትን ይዘው የሚለምኑትን በመከላከል፣ ማንነታቸውን በመጠየቅ ሕግ ፊት እስከ ማቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የወጣቶች እገዛ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በዐውደ ዓመትና በወርኀዊ በዓላት ላይ ከልመና ይልቅ ሰፊ ጊዜውን ለወንጌል አገልግሎት እንዲውል ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡


በአሁኑ ጊዜ ሰባክያን የሚሰብኩትን ያህል በምእመናኑ ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል?

 

በቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገለግሎት ቀጥሏል ስንል በምእመናን ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥተናል ማለት አይቻልም፡፡ እንደ መሰበኩ ለውጥ መጥቶ ቢሆን ኖሮ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ የሆነ አንድም ሰው አይገኝም ነበር፡፡ የሰባክያኑም ሕይወት አስቸጋሪ ነው፡፡ አሰባበካቸው የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት የጠበቀ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ዛሬ በየማሰልጠኛ ተቋሞቻችን ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰባክያን እየተመረቁ ነው፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ወይም ዐራት ሰባኪያን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሰባኪያን እንኳን ለአንድ አጥቢያ ለአንድ ወረዳ ይበቃሉ፡፡


እንደ መስበካቸው ውጤት ሲያመጡ አይታይም፤ ምክንያቱም ከሰባክያኑ የሚጠበቀው ሕይወት ስላልተገኘ ነው፡፡ የእኛን ሳይሆን የመናፈቃንን የአሰባበክ መንገድ ተከትለው የሚሄዱም አሉ፡፡ መድረክ ላይ አጊጠው፤ ቀሚስ ለብሰው ሰባክያን ሆነው ይቆማሉ፡፡ ከመድረክ ሲወርዱ ከአንድ ሰባኪ የሚፈለገው ሕይወት የማይታይባቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ በዚህ ምእመናን ግራ እየተጋቡ ነው፡፡ አልፎ አልፎም የቤተ ክርስቲያን ፈቃድ ሳይኖራቸው መድረክ የያዙ አሉ፡፡ ከአንዱ አጥቢያ ሲከለከሉ ወደ ማይታወቁበት ሌላ አጥቢያ እየሔዱ እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ሳይሆን እነሱ የሚፈልጉትን ዓላማ ይፈጽማሉ፡፡ እነዚህ አካላት ከሚታወቁባቸው መንገዶች አንዱ በስብከታቸው መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ ላይ አባቶችን በመንቀፍ ይታወቃሉ፡፡ ስለዚህ ለየወንጌል አገልግሎት ሥርዓት ቀጥሏል ካልን በምእመኑ ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል? ካልሆነስ ለምን? ለውጥ አምጥተናል ማለት አንችልም፡፡ የምእመናንን ሕይወት የሚለውጥ ስብከት እየተሰበከ አይደለም፡፡


ምክንያቱም፡- ለውጥ የሚባለው ወንጌልን እንደ ወንጌልነቱ ሲሰብኩት ነው፡፡ መድረኩ የወንጌል መድረክ ከሆነ አባቶቻችን እንደሰበኩት ለንስሐ የሚያበቃ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ፤ ከጊዜው ጋር የተገናዘበ ሲሆን ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ በስብከትም በሕይወትም እንደ አባቶቻችን ለምእመናን ምሳሌዎች መሆን ስንችል ነው፡፡ ያኔ ምእመናንም በትክክል ይቀበሉታል፡፡


ሰባክያን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አድገው፤ የአባቶችን ሙያ ዜማውን፤ ቅኔውንና ትርጓሜውን ማወቅ አለባቸው፡፡ አሁን የምናየው ሰባኪ በዚያ የተገራ አይደለም፡፡ አንድ ሰባኪ ቤተ ክርስቲያኒቷ ሳታስተምረው ከሌላው ሰባኪ እንደ ጉልት ገበያ እየለቃቀመ መድረኩን  አንቆ ይይዛል፡፡ የገበያ ጠባይ ስላለው ምእመናኑም ቤተ ክርስቲያኒቱም ተጠቃሚ አይደሉም፡፡


ቀድሞ አንድ ጊዜ የተሰበከው ለብዙ ምእመናን ሕይወት ይሰጥ ነበር፡፡ ሰባኪውም ተሰባኪውም በሕይወታቸው ይኖሩታል፡፡ አሁን እያየን ያለነው ምእመናን እምነታቸውን ስለሚወዱና እጅግ ጥልቅ የሆነ የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ስላላቸው ይሰባሰባሉ እንጂ ተሰብከው አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ምእመናን አልፎ አልፎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያዩት ያልተገባ የአገልጋዮችና የሰባክያን ድርጊት እየተሰላቹ ነው ማለት ይቻላል፡፡


ሰባኪያን ያለ ፈቃድ እንዳያስተምሩ አንድ መመሪያ ወጥቶ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ተፈጻሚነቱ የት ደረሰ ነው?

 

ችግሩ አሁንም አለ፡፡ በማኅበር ቤተ ክርስቲያንን በመደገፍ ላይ የሚገኙትን ሰባክያን፣ በስብከተ ወንጌል ዕውቀት ያላቸውን ሰባክያን በተመለከተ መምሪያው እንደየሞያቸው ለማሰማራት አሰባስበን ምክር ሰጥተን ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው አንዳንዶቹ ትክክለኛ አድራሻ እንኳን የሌላቸው ናቸው፡፡ በሥርዓት እንዲገዙ ብንመክርም ብትን ስለሆነ ማሰባሰብ አልተቻለም፡፡ እኛም ጠንክረን አልተጓዝንበትም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ቤተ ክህነቱ ወጥ የሆነ ከወረቀት ያለፈ አመራር ባለመስጠቱ ነው፡፡ በየመምሪያው ያሉ ሰባክያንም ድፍረት ያንሳቸዋል፡፡ በተላኩበት ቦታ ባለቤት ሆነው መድረኩን የማስከበር አቅም የላቸውም፡፡


አሁን የታሰበው በመገናኛ ብዙኀን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለምእመናን ተደራሽ ካደረግን የዚህንም ችግር በዛው መቅረፍ ይቻላል፡፡ መገናኛ ብዙኀንን ተጠቅመን አንድ ውጤት ላይ እንደርሳለን የሚል ተስፋ አለን፡፡

    
የስብከተ ወንጌል ወቅታዊ ተግዳሮተች ምን ምንድን ናቸው?

 

ዛሬ ሃይማኖት በዝቶ እንመለከታለን፡፡ ሃይማኖት ግን አንዲት ናት፡፡ ሃይማኖት በሥራና በሥነ ምግባር እንጂ በማደናገር አትገለጥም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከሕገ ልቡና ጀምራ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ካለበት አንስቶ ብሉይ ኪዳንን፣ ሐዲስ ኪዳንን አምና፤ ሃይማኖቱ የሚፈቅደውን ሥርዐት ጠብቃ፤ እግዚአብሔርን አምና የኖረች ናት፡፡ ከጊዜ በኋላ ከአረማዊነት የመጡት ደግሞ በወንጌል እናምናለን ብለው ብዙ ቅርንጫፍ አበጅተው ነቀፌታ ላይ ያተኮረ ትምህርት እየሰጡ ምእመናንን እያስኮበለሉ ይገኛሉ፡፡ ይህ አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡


በዚህ ላይ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የምናየው አሠራር የምንጠብቀውን ያህል አይደለም፡፡ አሠራራችን ዘመናዊ ባለመሆኑ ችግሩ አብሮን ዘልቋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ምን እንደሆነች የማያውቁ ከውጭ ሆነው ነቀፌታ ሲሰነዝሩ ይሰማል፡፡ ትናንት የእምነቱ ተከታይ የነበሩ በመናፍቃን ትምህርት እየተበከሉ ተሰናካክለው የሚታዩ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ቀላል ተግዳሮት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን አንጋፋና ጥንታዊት እንደመሆኗ መጠን ዛሬ በትናንት መልኩ ምእመናን የሚጠብቁትን አገልግሎት እያገኙ አይደለም፡፡


መናፍቃኑ ስልት በመቀያየር አማኝ ነበርኩ እያሉ ቤተ ክርስቲያኗን ሲያስነቀፉ እንመለከታለን፡፡ በኑሮ የተጐዱትን ካህናት በጥቅም በማታለል ይወስዷቸዋል፡፡ በኛ በኩል ደግሞ ምእመናኑ በመናፍቃኑ የቅሰጣ ትምህርት እንዳይወሰዱና ትክክለኛውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ወንጌል በስፋትና በጥልቀት መስጠት ይቀረናል፡፡ ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ ሰፋፊ የዐውደ ምሕረት ስብከቶችን መስጠት አለብን፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮቶችን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ እኛ ግን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ወደ ፊት የሚጠበቅብንን ከሠራን ለውጥ እናመጣለን ብየ አምናለሁ፡፡

 

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተጀመረው የአንድነት ጉባኤ ምን ይመስላል?

 

በጥሩ ሁኔታ ከያዝነውና ከመራነው ውጤታማ መሆን ይችላል፡፡ ጅምሩ ጥሩ ነው፡፡ ከላይ ላነሣናቸው ተግዳሮቶች መፍትሔ ማምጣት የምንችለው እንዲህ ዓይነት ሰፋፊ ጉባኤዎችን ማድረግ ስንችል ነው፡፡ ወደ ፊት አዲስ አበባ ላይ ያለውን ውጤት ገምግመን ወደ ሌሎች አህጉረ ስብከት ተግራባዊ ማድረግ ያስችለናል፡፡ ይህ አሠራር ደካማ ጎናችንን ለማየት ይጠቅመናል፡፡ የሰባክያኑንና የምእመናንን አስተያየት በመሰብሰብ የተሻለ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለማዳረስ ያግዘናል ብዬ አምናለሁ፡፡


በገጠሪቱ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እየተሰጠ ነው ማለት ይቻላል?

 

የገጠሪቱን ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ስንመለከት በርካታ ችግሮች አሉበት፡፡ ትምህርት የሌለበት፣ መምህራንን እንደልብ የማይጎበኙት በመሆኑ በገጠሩ አካባቢ ስብከተ ወንጌል የተጠሙ ምእመናንን እናያለን፡፡ ችግሩ ካህናቶቻችንን በስልጠና አግዘን ወንጌሉ እንዲስፋፋ አላደረግንም፡፡ ምክንያቱም ምእመናን ካህናቱን ይሰማሉ፤ የሚነግሯቸውንም በቀላሉ ይቀበላሉና ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ወደ ገጠር ወንጌል ተደርሷል ለማለት አያስችልም፡፡ ዛሬም ድረስ ወንድም ወንድሙን ይገድላል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ በሀሰት ይመሰክራል፡፡ ጥንቆላው፣ ሟርቱ እዚያ ነው ያለው፡፡ ወንጌል ተሰበከ የሚባለው የሰው ልጅ ተከባብሮ በሰላም መኖር ሲችል ነው፡፡ ስለዚህ በገጠር ያለው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲጠናከር ሰባክያን ወደ ገጠር ወጥተው ማስተማር ይገባቸዋል፡፡

 

እስከ አሁን ብዙ ርእሰ ጉዳዮቸን አንሥተን ተወያይተናል፡፡ መምሪያው በስብከተ ወንጌል በኩል ምን እየሠራ ነው?

 

መምሪያው አርፎ አያውቅም፡፡ በየጊዜው ዕቅድ በማውጣት፣ የወጣውንም ዕቅድ በሥራ ላይ በማዋል በዐውደ ዓመት፣ ወርኃዊና ዓመታዊ በዓላትን በማስመልከት በየሀገረ ስብከቱ የሰባክያን እጥረት ባለበት ሰባክያንን ይመድባል፣ ያሰማራል፡፡ ችግሩ ለውጥ ላይ ነው፡፡ ዛሬ የሰው መንፈስ እየተለወጠ ነው፣ ጥንካሬ ይጐድላል፡፡ መምሪያው ግን ያለ ዕረፍት እየሠራ ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ዘመኑን የዋጀ ትምህርት ለመስጠት በመገናኛ ብዙኀን ጭምር ሰብከተ ወንጌል ለማስፋፋት ዕቅድ አውጥተናል፡፡ ከቀደመው ዘመን የተሻለ ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን፡፡ መመሪያውንና ዕቅዱን ቅዱስ ሲኖዶስ አይቶት አጽድቆ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባት ብቻ ነው የቀረን፡፡

 

ምእመናን ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ፤ ነገር ግን የሚፈልጉትን ለመስማት ዕድሉን አያገኙም፡፡ የሚሰሙት የካህናቱ ጸብ፣ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተፈጠሩ አሉባልታዎች፣ ስለ  ገንዘብ መጉደል፣ ሌሎችም ለእነሱና ለቤተ ክርስቲያናቸው የማይመጥኑ ነገሮችን ይሰማሉ፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሲመጡ ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን በቃልም፣ በሕይወትም የሚለውጥ ቃለ እግዚአብሔር ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ባለማግኘታቸው ያዝናሉ፡፡ የስብከተ ወንጌሉ አገልግሎት አሰጣጣችን በጣም ደካማ ነው፡፡

 

ምእመናን እምነት አላቸው፡፡ የሚቸግራቸው መንፈሳዊው ኑሮ ነው፡፡ ዘመኑ ከኑሯቸው ጋር ስለሚፈትናቸው መንፈሳዊውን ምግብ በጣም አጥብቀው ይፈልጉታልም፤ ይፈተኑበታልም፡፡ ስለዚህ እንደዘመኑ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ በርግጥ ከጥንቱ የተሻለ የእምነት ጉዞ አለን ለማለት ይቸግራል፡፡ እንደ አባቶቻችን በሆንን መልካም ነበር፡፡ ድሮ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ሁሉም ነገር ሰላም ነበር፡፡ እንደዘመኑ ሙዳየ ምጽዋት ተሰበረ ሲባል አይሰማም፡፡ አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ዘመኑን አገናዝቦ አገልጋዩም፣ ተገልጋዩም ለእምነቱ የቆመ፣ በታማኝነት ተጋግዘን መሥራት አለብን፡፡ ያኔ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ 

   

የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲጠናከር ከማኅበራት፣ ከወጣቶችና ከምእመናን ምን ይጠበቃል?

 

አንዱም ያልሠራንበትና ኖሮን ያልተጠቀምንበት ጉዳይ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ሁሉም በድርሻው ቢያገለግል መልካም ነው፡፡ በአካላችን ውስጥ የተለያዩ የስሜት ሕዋሳት እንዳሉ ሁሉ በቤተ ክርስቲያናችንም ሁሉ አማኝ ድርሻ አለው፡፡ ይህንን የተበታተነውና ዝርው የሆነውን ማሰባሰብ ይጠይቃል፡፡ ጥሩ የሚሆነው አባቶችም በአባትነታቸው፣ ማኅበራትም ሆኑ ለሃይማኖታቸው ቀናኢ የሆኑ ምእመናንን በአንድነት አሰባስቦ መመካከር፣ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ እቅዳችንን ሥራ ላይ አለማዋላችን ያመጣው ክፍተት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ወደፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንክረን እንሠራለን፡፡ ሁላችንም ተግባብተን ለአንዲት ቤተ ክርስቲያናችን አገልግሎት ተሰባስበናልና ምክክር፣ ውይይት ያስፈልጋል፡፡


ካለወጣቶች አገልግሎት አይታሰብም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን አንድ አካል ናቸው፡፡ በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ እንዳለው ቅዱስ ዳዊት ወጣቶች ጉልህ የሆነ የአገልግሎት ድርሻ አላቸው፤ እነሱ ከሌሉ አባቶቻችንን ማን ይተካቸዋል? ቤተ ክርስቲያን ወጣቱ ላይ ትኩረት አድርጋ ልትሠራ ይገባል፡፡ ወጣትነት የትግል ጊዜ ነው፣ ፍላጎት የሚያይልበት በመሆኑ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጠንክሮ፣ ኮትኩቶ ማስተማር፣ ሳይሰለቹ መምከር ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ የተሰባስበበት መንገድ ወጥ የሆነ አይደለም፡፡ የጉዞ፣ የወንጌል፣ የጽዋ ማኅበር እየተባለ ቅርጽ የለሽ ሆኗል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ውስጡ መፈተሸ አለበት፡፡


የተማረው የቤተ ክርስቲያን አካል በቴክኖሎጂው ረገድ የሚጠበቅበትን በማድረግ የቤተ ክርስቲያንን ክፍተት መሙላት ያስፈልጋል፡፡ እቅድ አቅደን፣ ፕሮጀክት ነድፈን ብንሠራ በርካታ ክፍተቶችን እናስወግዳለን፡፡ እስካሁን የተጓዝንበት መንገድ ስንመዝነው ውጤቱ ዝቅተኛ ነው፡፡ መተማመን፣ መግባባትና ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ መቆም አለብን፡፡ እርስ በርስ እየተጎሻሸሙ መጓዝ የትም አላደረሰንም፤ ጎድቶናል እንጂ፡፡ አሠራራችን ከጊዜውና ከምእመናን ፍላጎት ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ የሃይማኖት ሥልጣኔ የምንለው በሥነ ምግባር ታንጾ፣ መጾም፣ መጸለይ፣ ንስሐ መግባትና የቁርባን ተሳታፊ መሆን ሲቻል ነው፡፡ ወጣቱን በዚህ ዓይነት አሠራር ውስጥ እንዲሳተፍ ማድረግ ላይ የልምድ ማነስ ይታይብናል፡፡


ስለሰጡን ቃለ ምልልስ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡


እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡


ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ከታኅሣሥ 1-15/2007 ዓ.ም.

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-16/1670-2015-01-01-19-04-02