የሰበካ ጉባኤ አባላትን አቅም ለማሳደግ ሥልጠና ተሰጠ

መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም.

ከጀርመን ቀጣና ማዕከል

002 german በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ፤ ምሥራቅና ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የሰበካ ጉባኤ አባላትን አቅም ለማሳደግ የታለመ ሥልጠና በጀርመን ፍራንክፈርት ዙሪያ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መቀመጫ በሆነው በሩሰልስሃይም ከተማ የካቲት 28 ቀን 2007 ዓ.ም ተሰጠ::


የሥልጠና መርሐ ግብሩን በጸሎትና በቡራኬ የከፈቱት ብፁዕ አቡኑ ሙሴ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፤ የሥልጠናውን ወቅታዊነትና አስፈላጊነት አበክረው ተናግረዋል::


የሥልጠናው ዋና አስተባባሪ የሆኑት የሀገረ ስብከቱ ጸሐፊ መጋቤ ምሥጢር ኅሩይ ኤርያስ የእለቱን መርሐ ግብር በዝርዝር በማስተዋወቅ እና ጥሪውን አክብረው የመጡ ሠልጣኞችን በማመስገን ሥልጠናው ተጀምሯል::


ሥልጠናው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ አገልጋዮች ሊያውቋቸውና በሥራ ሊተገብሯቸው ከሚገቡ መሠረታዊ የአስተዳደር ተግባራት መካከል የሚመደቡ ሲሆኑ፤ “የሰበካ ጉባኤ አመሠራረትና አጠቃላይ የአስተዳደር መዋቅር”፤ “የሂሳብ አያያዝና የገንዘብ አሰባሰብ ገቢና ወጪ ሥርዓትና ደንብ”፤ “የምእመናን እና ንዋየተ ቅድሳት ምዝገባ፤ ቆጠራና ሪፖርት”፤ “የአገልግሎትና አስተዳደር ሥራ አፈጻጸም” ፤ “ሰንበት ትምህርት ቤቶችና የጽዋ ማኅበራት አደረጃጀት እና ሚና” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡


“የሰበካ ጉባኤ አመሠራረትና አጠቃላይ የአስተዳደር መዋቅር” የሚለውን ሥልጠና የሰጡት ሊቀ ብርሃናት አባ ገብረ ሕይወት ፍስሐ በጀርመን ሙኒክ የደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሲሆኑ፤ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደርና አወቃቀር ሰፋ ባለና አጥጋቢ በሆነ መልኩ አቅርበዋል::


በመቀጠልም ከፈረንሳይ በመጡት በመልአከ ሕይወት አባ ዘድንግል ኑርበገን በፓሪስ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ አማካኝነት “የሂሳብ አያያዝና የገንዘብ አሰባሰብ ገቢና ወጪ ሥርዓትና ደንብ”፤ እንዲሁም በቀሲስ ግሩም ታዬ “የምእመናን እና ንዋየተ ቅድሳት ምዝገባ፤ ቆጠራና ሪፖርት” በቀሲስ ግሩም ታየ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ሰፊ ግንዛቤ ያስጨበጠ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡


ከሰዓት በኋላ በተካሔደው የሥልጠናው ቀጣይ መርሐ ግብር በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ የደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት በመልአከ ሕይወት ፍስሃ ድንበሩ “የአገልግሎትና አስተዳደር ሥራ አፈጻጸም” በሚል ከላይ የተነሱትን ርእሶች በሚያዳብርና በሚያጠናክር መልኩ አቅርበዋል፡፡


የመጨረሻው ርእስ “ሰንበት ትምህርት ቤቶችና የጽዋ ማኅበራት አደረጃጀት እና ሚና” የሚል ሲሆን፤ በዲያቆን ዶክተር ያብባል መሉዓለም በማኅበረ ቅዱሳን የጀርመን ቀጣና ማዕከል ሰብሳቢ ቀርቧል፡፡


በቀረቡት የሥልጠና ርእሰ ጉዳዮችና በተደረጉት ገለጻዎች ላይ በተደረገው ሰፊ የውይይት ጊዜም ተሳታፊዎች ያሏቸውን ጥያቄዎች አቅርበው በብፁዕ አቡኑ ሙሴ እና በሌሎች አባቶች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል::


ተሳታፊዎቹ በሰጡት አስተያየት “ስለ ቤተ ክርስቲያናችን አወቅቀርና አደረጃጀት ያላወቅነውን እንድናውቅ፤ ያላስተዋልነውን እንድናስተውል አድርጎናል፡፡ በተለይም ብፁዕ አባታችን አቡነ ሙሴ በመካከላችን በመገኘት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የጎደለውን በመሙላት፤ የጠመመውን በማቅናትና አባታዊ ምክራቸውን በማስተላለፍ አብረውን በመዋላቸው ፍጹም ደስተኞች ነን” ብለዋል።


001 german ብፁዕ አቡነ ሙሴ በሰጡት ቃለ ምዕዳን "አሐተ ሰአልክዎ ለእግዚአብሔር ወኪያሃ አኀሥሥ ከመ እኅድር ቤቶ ለእግዚአብሔር በኵሉ መዋዕለ ሕይወትየ... እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ" (መዝ 26፡4) እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት መኖር ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡


የቤተ ክርስቲያን ልጆች በአንድ ላይ ተሰባስበው ሲማማሩ እና ሲወያዩ መዋላቸው ለቤተ ክርስቲያን እድገት እና መስፋፋት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ለዚህ ጉባኤ መሳካት አስተዋጽዎ ያደረጉትንና ሥልጠናውን ያስተባበሩትን፣ ያስተማሩትን፣ ጥሪውን አክብረው በሥልጠናው የተሳተፉትን፣ እንዲሁም በመስተንግዶ ያገለገሉትን የሮሰልስሃይምና ራውንሃይም አካባቢ ነዋሪ ምእመናንን አመስግነዋል፡፡

በዚህ ልጠና ላይ ከ 40 በላይ ልጣኞች የተሳተፉ ሲሆን በጀርመን ሀገር ከሚገኙ 12 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የ9ኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ አመራር አባላት እንደተገኙ ታውቋል።

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1772-2015-03-13-13-18-27