በባሕር ዳር ማእከል ለግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ተሰጠ

መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም.

በግዛቸው መንግሥቱ /ከባሕር ዳር ማእከል/

በማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል የግቢ ጉባኤያትን አገልግሎት ለማጠናከርና ጠንካራ አገልጋዮችን ለማፍራት እንዲያስችል የካቲት 21 እና 22 ቀን 2007 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በከተማው ለሚገኙ ለ16 ግቢ ጉባኤያት ተወካዮች ሴሚናር ተሰጠ፡፡

በሴሚናሩም “መንፈሳዊ አገልግሎት “ እና “የስልታዊ ዕቅድ አዘገጃጀትና አተገባበር” የተሰኙ ሁለት ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፤ የግቢ ጉባኤያትን የአገልግሎት ተነሳሽነትና የመፈጸም አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡


በመጀመሪያው ቀን ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ መንፈሳዊ አገልግሎትን በተመለከተ ለግማሽ ቀን ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ለማገልገል በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት የጠቆሙት ዶ/ር አለማሁ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ የሚከተሉትን ነጥቦች ሊያሟላ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ፈቃደኛ መሆን ፣ በሚገባ ተምሮ ማገልገል፣ ምን አስተምራለሁ( አገለግላለሁ) ብሎ አለመጨነቅ፣ አገልግሎት ሁሉ እኩል መሆኑን መረዳት ወይም በአገልግሎት አለመታበይ፣ ለአገልግሎት ግድየለሽ አለመሆን፣ በተሰጠ ጸጋ ማገልገል፣ አገልግሎት ሰውን ማስደሰት ብቻ ሳይሆን ሰውን ማዳን መሆኑን መረዳት፣ በአገልግሎት አለመሰልቸት( አለመታከት)፣ ራስን አለመርሳት፣ በጸሎት መትጋት፣ ሰውን አለማሰናከል፣ ሕይወትን ሁል ጊዜ ማሳደግ፣ ሁልጊዜ ስለ ቤተ ክርስቲያን ማሰብ፣ በኑሮ ጠንቃቃ መሆን ( በአለባበስ፣ በአነጋገር ፣በአመጋገብ..)ና የመሳሰሉት ዶ/ር አለማየሁ ከዘረዘሯቸው ዋና ዋና ነጥቦች ይገኙበታል፡፡


አንድ አገልጋይ ሳይማር ማገልገል ስለማይችል መጀመሪያ ማንበብ፣ ማወቅ፣ መማር፣ መረዳት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ “የማያነብ ሰው የመንፈሳዊና የሥጋዊ ስኬት ሊኖረው አይችልም” የሚሉት ዶ/ር አለማየሁ አባቶቻችን ዐይናቸው እስኪጠፋ ድረስ አንብበው፤ መጻሕፍትን ጽፈው እንዳለፉት ሁሉ እኛም አንብበን የሚገባንን አገልግሎት ለመፈጸም ትኩረት ልንሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡


አንድ አገልጋይ ከተመደበበት ክፍል ከመጸለይ ጀምሮ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በጾም፣ በጸሎት ፣ በክርስቲናዊ ሥነ ምግባር እየበረታ አገልግሎቱን ማጠናከርና ድርሻውን መወጣት እንዳለበት ያሳሰቡት ዶ/ር አለማየሁ “ክርስትና ዘወትር የሚኖሩት የእለት እንጀራ፤ የዘወትር ልብስ ነው” በማለት የሚገጥማቸውን ፈተና በመቋቋም በክርስቲያናዊ ሕወታቸው እንዲበረቱ አሳስበዋል፡፡


በሁለተኛው ቀን በተካሔደው ሴሚናር በአቶ ጌታሁን መኮንን “የስልታዊ ዕቅድ አዘገጃጀትና አተገባበር” የተሰኘ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡


አቶ ጌታሁን በቀረቡት ጽሑፍም የዕቅድ ምንነት፣ የዕቅድ ጠቀሜታ፣ የማበኅረ ቅዱሳን ዕቅድ፣ የግቢ ጉባኤያት ድርሻ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ተንትነዋል፡፡ በቀጣይነትም ምን እናድርግ? በሚል ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ለተጠየቁ ጥያቄዎችም ምላሽ ተሰጥቶባቸው ሴሚናሩ ተጠናቋል፡

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1770-2015-03-10-15-29-54