መፃጉዕ ( የዐቢይ ጾም ዐራተኛ ሳምንት)

የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም.

ምንባባት

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዓ፤ ወይቤልዎ አይሁድ በዓይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ፤ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚኦ ለሰንበት እግዚኦ ውእቱ ለሰንበት ወልድ ዋሕድ ወይቤሎሙ ብውህ ሊተ፤ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስበክ ግዕዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ፡፡


ትርጉም: “የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ፤ አይሁድም በማን ሥልጣን ይህን ታደርጋለህ አሉት፤ እርሱም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ አላቸው፡፡ የሰንበት ጌታው እኔ ነኝ፤ የሰንበት ጌታው/የአብ/ አንድያ ልጁ ነው፡፡ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር እል ዘንድ ፣ ነፃነትን እሰብክ ዘንድ ተሰጥቶኛል ፣ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ልኮኛል አላቸው፡፡” ማለት ነው፡፡


መልእክታት

(ገላ. 5÷1-ፍጻሜ ምዕ.)፡- እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡ እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም፡፡” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም አንደሚገባው እመሰክራለሁ፡፡ በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል፡፡ እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ÷ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ አናደርጋለን፡፡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና፡፡ ቀድሞስ በመልካም ተፋጠናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና፡፡ ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል፡፡ ወንድሞቼ ሆይ÷ እኔ ግዝረትን ገና የምስብክ ከሆነ÷ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል፡፡ የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል፡፡

ወንድሞቼ ሆይ÷ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ፡፡ “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና፡፡ እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትንካከሱ ከሆነ ግን÷ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ፡፡ እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ፡፡ ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና÷ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ፡፡ የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ÷ ከኦሪት ወጥታችኋል፡፡ የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት÷ ርኲሰት÷ መዳራት÷ ጣዖት ማምለክ÷ ሥራይ ማድረግ÷ መጣላት÷ ኲራት÷ የምንዝር ጌጥ÷ ቅናት÷ቊጣ÷ ጥርጥር÷ ፉክክር ÷ምቀኝነት መጋደል÷ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው፡፡ አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም፡፡ የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር÷ ደስታ ÷ሰላም÷ ትዕግሥት÷ ምጽዋት÷ ቸርነት÷ እምነት÷ ገርነት÷ ንጽሕና ነው፡ ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ፡፡ አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ፡፡ ኩሩዎች አንሁን፤ እርስ በርሳችን አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና፡፡ 

(ያዕ.5÷14- ፍጻሜ ምዕ.)፡- ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡ የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል፡፡ እርስ በርሳችሁ ኀጢአታችሁን ተናዘዙ፤ እንድትድኑም ለወንድሞቻችሁ ጸልዩ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎቱ ብዙ ትረዳለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች፡፡ ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር፤ እንደምንታመምም ይታመም ነበር፤ ዝናም እንዳይዘንም ጸሎትን ጸለየ፤ ሦስት ዓመት ከስድስት ወርም በምድር ላይ አልዘነመም፡፡ ዳግመኛም ጸለየ፤ ሰማይም ዝናሙን ሰጠ፤ ምድርም ፍሬዋን አበቀለች፡፡ ወንድሞቻችን ሆይ÷ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር÷ ከኀጢአቱ የመለሰውም ቢኖር÷ ኀጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንደ አዳነ÷ ብዙ ኀጢአቱንም እንዳስተሰረየ ይወቅ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድም የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ተፈጸመች፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

ግብረ ሐዋርያት

(የሐዋ.3÷1-11)፡- ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚልዋት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ወደ እኛ ተመልከት” አለው፤ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጴጥሮስም÷ “ወርቅና ብር የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ÷ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ አጁም ይዞ አስነሣው፤ ያን ጊዜም እግሩና ቊርጭምጭምቱ ጸና፡፡ ዘሎም ቆመ፤ እየሮጠና እየተራመደም ሄደ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ከእነርሱ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፡፡ ሕዝቡም ሁሉ እግዝአብሔርን እያመሰገነ ሲመላለስ አዩት፡፡ እርሱም መልካም በምትባለው በመቅደስ ደጃፍ ተቀምጦ ምጽዋት ይለምን የነበረው እንደ ሆነ ዐወቁት፤ በእርሱም ከሆነው የተነሣ መገረምና መደነቅ ሞላባቸው፡፡

ምስባክ

መዝ.40÷3 “እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፡፡ ወይመይጥ ሎቱ ኩሎ ምስካቢ /ቤ/ሁ እምደዌሁ አንሰ እቤ እግዝኦ ተሣሃለኒ

ትርጉም፦ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው የተነሣ ይለውጥለታል፡፡

ወንጌል

(ዮሐ. 5÷1-24)፡- ከዚህም በኋላ በአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፤ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች÷ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃዉን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ይህን ሰው በአልጋዉ ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደ ቆየ ዐውቆ÷ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ÷ “አዎን ጌታዬ ሆይ÷ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያዉ የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ ጌታችን ኢየስስም÷ “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡ አይሁድም የዳነውን ሰው÷ “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ እርሱም መልሶ÷ “ያዳነኝ እርሱ፡- አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም÷ “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” ብለው ጠየቁት፡፡ ያ የተፈወሰው ግን ያዳነው ማን እንደ ሆነ አላወቀም፤ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ቦታ በነበሩት ብዙ ሰዎች መካከል ተሰውሮ ነበርና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ያን የዳነውን ሰው በቤተ መቅደስ አገኘውና÷ “እነሆ÷ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” አለው፡፡ ያም ሰው ሄዶ ያዳነው ጌታችን ኢየሱስ እንደ ሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ጌታችን ኢየሱስን ያሳድዱትና ሊገድሉትም ይሹ ነበር፤ በሰንበት እንዲህ ያደርግ ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፤ እኔም እሠራለሁ” አላቸው፡፡ ስለዚህም አይሁድ ሊገድሉት በጣም ይፈልጉ ነበር፤ “ሰንበትን የሚሽር ነው” በማለት ብቻ አይደለም፤ ደግሞም እግዚአብሔርን “አባቴ ነው ይላል፤ ራሱንም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተካክላል” በማለት ነው እንጂ፡፡

ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ወልድ ከራሱ ብቻ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ፤ ወልድም አብ የሚሠራውን ያንኑ እንዲሁ ይሠራል፡፡ አብ ልጁን ይወዳልና የሚሠራውንም ሥራ ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ታደንቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራን ያሳየዋል፡፡ አብ ሙታንን እንደሚያስነሳቸው÷ ሕይወትንም እንደሚሰጣቸው እንዲሁ ወልድም ለሚወድዳቸው ሕይወትን ይሰጣል፡፡ አብ ከቶ በማንም አይፈርድም፤ ፍርዱን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ፡፡ ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩ ወልድን ያከብሩ ዘንድ፤ ወልድን የማያከብር ግን የላከውን አብን አያከብርም፡፡

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/2012-02-15-14-49-20/1768-2015-03-10-12-16-58