ምኩራብ

 

 የካቲት 20 ቀን 2007.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ    

እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓትና ትውፊት መሠረት በዐቢይ ጾም ስምንቱ ሰንበታት ሊዘመር የተዘጋጀው የጾመ ድጓው መዝሙር ነው፡፡ በየሰንበቱ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት ፣ የሚዘመረው የዳዊት መዝሙር (ምስባክ) ከሰንበቱ ስያሜ ጋር የሚያያዙና የሚዛመዱ ናቸው፡፡ በሰንበታቱ ውስጥ የሚነበበውና የሚዘመረውም ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ ያስተማራቸውን ትምህርቶችና የሠራቸውን ዋና ዋና ተዓምራትና መንክራት የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ጾሙ የጌታ ጾም ስለሆነ ሁሉም መዝሙራትና ምንባባት ከጌታ ትምህርትና ሥራ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት ሦስተኛው ሰንበት ምኩራብ ተብሎ ተሰይሟል፡፡

 

ምኩራብ ማለት ሰቀላ መሰል አዳራሽ ማለት ነው። አይሁድ ስግደትና መሥዋዕታቸውን የሚያቀርቡት በኢየሩሳሌም ባለው መቅደስ ብቻ ነው ብለው ቢያምኑም (ዮሐ 4፥20) ፤በየተበተኑበት ቦታ ምኩራብ እየሠሩ ትምህርተ ኦሪትን በመማር ሃይማኖታቸውን ያፀኑ ነበር። ምኲራብ የአይሁድ የጸሎት ቤት ሲሆን በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚገልጸው ናቡከደነጾር የአይሁዳውያንን ቤተ መቅደሱን አፍርሶ ሕዝቡንም ወደባቢሎን ካፈለሰ ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎትና ለማኅበረተኛነት ልዩ ቤት ሊሠሩ እንደጀመሩ ይገልጻል፡፡

 

አይሁድ በምኲራቦቻቸው የሕግንና የነቢያትን መጻሕፍት /የብራና ጥቅሎች/ በአንድ ሣጥን ውስጥ ያስቀምጣሉ፡፡ በመሆኑ የጸሎት ሥፍራዎቻቸውን ለትምህርትና ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በሕገ ኦሪት የአይሁዳውያን ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ሕግ ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ተግባራት ከሚሄዱበትም ይልቅ በዓመት አንዴ የሚቀርበውን መሥዋዕትና መብዓ ለመስጠት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሕግ ሊፈጽም ወደ ቤተ መቅደስ ይሔድ ነበር፡፡ “ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንዳስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ” እንዲል /ሉቃ.2፥42/ “ዕለት ዕለትም በቤተ መቅደስ /ምኩራብ/ ያስተምር ነበር፡፡” /ሉቃ.19፥47/ ፡፡

 


በዚሁ ዕለት የሚዘመረው ጾመ ድጓ ከዋዜማው ጀምሮ እስከ ሰላሙ ድረስ በዕለተ ሰንበት “ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ” እያለ ኢየሱስ በአይሁድ ምኩራብ ማስተማሩን እያነሳ ስለሚዘምር ይህን ሰንበት ለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ እየገባ ለማስተማሩና በምኩራብ የሚሸጡ የሚለውጡ ነጋዴዎችን ስለማስወጣቱ ቤተ መቅደሱን ስለማስከበሩ መታሰቢያ ሆኖ ነው፡፡ማቴ21፡12

 

 

ጌታችን በምኩራብ እየተገኘ ሲያስተምር ትምህርቱን ሕግን አውቆ እንደሚያሳውቅ ሠራዔ ሕግ ስለሆነ በሙሉ ሥልጣንና ኃይል ያስተምር ነበር፡፡“ቦአ ኢየሱስ ምኩራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕትአነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያውኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምስያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኩራቦሙ ወገሠፆሙያርምሙ አንከሩ ምህሮቶ ሞገስ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዓ አፉሁ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኩራብ ገባ፤ የሃይማኖት ቃልን አስተማረ፤ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅምየሰንበት ጌታዋ ነው ፡፡ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል (እያለየሃይማኖትን ቃል አስተማራቸው) ፤ ወደ ምኩራባቸውም ገብቶ ዝም ይሉ ዘንድ ገሠፃቸው፤እነርሱም ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ። የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

 

 ቅዱስ ዳዊትም አስቀድሞ በተናረው ትንቢት መሠረት ጌታ ለቤተመቅደሱ ቀንቶ አጽድቶት ነበር፡፡

 

መዝ 68፡9
እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ
ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ፡፡

 

ትርጉም፦የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና
ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፡፡

 

 

በነብዩ በኢሳይያስ እንደተጻፈ ጌታ በአይሁድ ምኩራብ ገብቶ መጽሐፍ እንዲሰጡት ጠይቆ የሚሰሙት ቃል ዛሬ በጆሯቸው እንደተፈጸመ እንዲህ ሲል እንደነገራቸው፡፡ “ኢየሱስም በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ፤ ስለ እርሱም በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ዝና ወጣ። እርሱም በምኵራባቸው ያስተምር ሁሉም ያመሰግኑት ነበር። ወዳደገበትም ወደ ናዝሬት መጣ፤ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኵራብ ገባ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ። “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል፡፡” ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።

 

 

መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ በምኵራብም የነበሩት ሁሉ ትኵር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም። “ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ”ይላቸው ጀመር። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር ከአፉም ከሚወጣው ከጸጋው ቃል የተነሣ እየተደነቁ። “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለምን? ”ይሉ ነበር። እርሱም። ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። “ባለ መድኃኒት ሆይ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ” አላቸው። ሉቃ.4፡14

 

 

“ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀመዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፣ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ፡፡ የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ፡፡ ወደ መቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፣ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ፣ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፣ ርግብ ሻጪዎችንም ይህን ከዚህ ውሰዱ፡፡ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ፡፡

 

 

አይሁድ መልሰው ይህን ስለምታደርግ ምን ምልክ ት ታሳየናለህ አሉት፡፡ ኢየሱስም መልሶ ይህን ቤተመቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው ስለዚህ አይሁድ ይህ ቤተ መቅደስ ከአርባ ስድስት ዓመት ጀምሮ ይሠራ ነበር፣ አንተስ በሦስት ቀን ታነሣዋለህን አሉት፡፡ እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተመቅደስ ይል ነበር፡፡”ዮሐ 2፡12-25 ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ይህን እንደተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ፡፡

 

በፋሲካ በዓልም በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ ብዙ ሰዎች በስሙ አመኑ ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፣ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/2012-02-15-14-49-20/1745-2015-02-27-08-19-40