የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሥርዓተ ትምህርት ማስተማሪያ መጽሐፍ አሳትሞ በቅዱስ ፓትርያርኩ አስመረቀ

እንደሚታወቀው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ክርስቲያን የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ከተቋቋመ በርካታ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ አሁን ድረስ የሰ/ት/ቤት ተማሪዎች በግል በተዘጋጀ ጽሑፍና አልፎ አልፎ በግል በሚታተሙ መጽሔቶች እየተማሩ አሁን ላሉበት ደረጃ ደርሰዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተመሳሳይ ያልሆነ ግንዛቤ እያደር የዕውቀትና የአመለካከት ልዩነት ከመፍጠሩም ባሻገር ለልዩ ልዩ እንግዳ ትምህርቶች በር የከፈተ በመሆኑ የሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንድ ዓይነት ወይም ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትመህርት በሰ/ት/ቤት ተማሪዎች ለመዘርጋት በማቀድ የማስተማሪያ መጽሐፍ ዘመናትን በመዋጀት የሚዘመር መዝሙረ ማኅሌት በማሳተም ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች የ51 አህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አስመርቋል፡፡ ብዙዎቹ አባቶች እና ሥራአስኪያጅ እንደገለጹት ከሆነ ለዘመናት ስንጠይቀው የነበረው ጥያቄ አሁን ተመልሷል ማለት ይቻላል በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የመምሪያው ዋና ኃላፊ መ/ር ዕንቈባሕርይ ተከስተ እንደገለጹት የእነዚህ መጻሕፍት ሥራ በዚህ የሚያበቃ ሳይሆን በየቋንቋው የመተርጎም ስራም ተያይዞ ይቀጥላል በማለት ወደ ኦሮምኛ እና ወደ ትግርኛ የመተርጎሙ ሥራ በቅርብ ቀን እንደሚጀምር እና ዝግጅቱ ሁሉ ተጠናቅቆ እንዳለቀም ገልጸዋል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያደጉ እና በዚህ የትርጉም ስራ ላይ ለመሳተፍ እንዲሁም ሕያው የሆነ ታሪክ ለትውልድ ሰርቶ ለማለፍ ፍላጎት ያላቸው ወጣት ምሁራን ወደ መምሪያችን ብቅ ብለው እንዲረዱን ጥርዬን አስተላልፋለሁም ብለዋል፡፡ መጻሕፍቱም ከሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በማደራጃ መምሪያው ሱቅ ውስጥ መሸጥ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

Read more http://eotcssd.org/the-news/400-2014-10-20-09-52-38.html