Print

ወላጅነትና ልጅ ማሳደግ ከሁሉም የበለጠ የረጅም ጊዜ ሥራ መሆኑን ብዙ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ብዙ ወላጆችም እራሳቸው እንዳደጉበት  እንደ ባሕላቸውና እንደ ጓደኞቻቸው እንደሚያሳድጉም ይታወቃል። ምንም ዓይነት ዕርዳታ ምክርና ትምህርት አያገኙም፤ እንዳለም አያውቁም። የምንኖርበት አገርም እንዲሁ የተለያየ ዓይነት ባሕልና ልጅ አስተዳደግ ያለው ነው። ብዙ ወላጆችም ልጆቻቸው በጤንነትና ደስተኞች ሆነው እንዲያድጉ ምክሮችንና ትምህርቶችን ይፈልጋሉ፤ ያገኛሉም። የእኛ ቤተ ክርስቲያንም ለአባላቶቿ እንዲሁ የልጅ አስተዳደግ መርሐ ግብር በየሳምንቱ ቅዳሜ ከ 10:00 A.M.—12:00 P.M. ድረስ አዘጋጅታ ላለፉት ስምንት ወራት ብዙ ወላጆች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። በዙሁ አጋጣሚም ይኽን መርሐ ግብር የማያውቁ ወላጆች በተቻለ መጠን እንዲሳተፉም ጥሪዋን ታቀርባለች።

የወላጆች ትምህርት የልጅ ማሳደግ ሥራቸውን በብዙ ሁኔታ ይረዳል።

፩ኛ- ልጆቻቸው ጤነኛና ደስተኛ ሆነው እንዲያድጉ

፪ኛ- ልጆቻቸው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዴት መርዳትና ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንዲያውቁ

፫ኛ- ልጆቻቸው ከመጥፎ ፀባይ ርቀው በራሳቸው የሚኮሩና የሚተማመኑ እንዲሆኑ

፬ኛ- ልጆች እንዴት በሁለት ባሕል (በአሚሪካዊነትና በኢትዮጵያዊነት) ማደግ እንደሚችሉና የዚህንም ጥቅም ማወቅን ይማራሉ።

፭ኛ- ዘመኑ የሚያመጣቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በልጆችና ቤተሰቦች መካከል የሚያመጣውን ጥቅምና ጉዳት ይማራሉ

፮ኛ- የተለያዩ ወላጆች በየግል የሚገጥማቸውን ልምዶች በማምጣት ይነጋገሩበታል

፯ኛ- የታወቁ የወላጆች ትምህርትና የአስተዳደግ መመሪያዎች መርሐ ግብርን በመጠቀም ትምህርት ይሰጣል

እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ያህል ለምሳሌነት የቀረቡ ናቸው እንጂ ከዚህ የበለጠ ሌሎች ሁኔታዎችም እንዳሉ ከተሳታፊዎቹ ለውጥ ማስተዋል ይቻላል። ሕፃናት ልጆቻችንም ሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከተለያዩ ባሕልና ወገን ከመጡ ልጆች ጋር በመኖራቸው ለብዙ ነገር የተጋለጡ ናቸው። የሚያድጉትም ከቲቪና ከኢንተርኔት እንዲሁም ከጓደኞቻቸው በየደቂቃው እየሰሙና እያነበቡ ነው የሚያሳልፉት። ይኽ ሁሉ በትምሕርታቸው፣ በፀባያቸው፣  በቤተሰባቸውና በሥነ ልቦናቸው ላይ ተፅእኖ ያደርጋል። በመሆኑም የቤተሰብና የወላጅ ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋቸዋል። የወላጆች ትምህርት ይኽን የመሳሰሉትን ወቅታዊና አስፈላጊ የወላጆች መማማር ስለሚያደርግ ጠቃሚነቱን ከወዲሁ በመረዳት ወላጆች በሙሉ መጥታችሁ አብረን እንድንማማርና ከልምዳችሁም እንድታካፍሉን እንጠይቃለን።