በክቡር መልአከ አርያም ቆሞስ አባ ኃይለሚካኤል ጸሎት የተከፈተው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ቤዛ-ኵሉ ሰንበት ት/ቤት የተመሠረተበት ፳ኛ ዓመታዊ በዓል ከሐምሌ ፲፭-፲፯/፳፻፰ ዓ.ም. ድረስ በደማቅ ሁኔታ ከደብሩ ካህናት፣ ጥሪ ከተደረገላቸው መምህራንና ዲያቆናት ጋር እንዲሁም ይቺን ቀን በታላቅ ጉጉት ሲጠባበቁ ከነበሩት የሰንበት ት/ቤቱ አባላት እና ከመላው ምእመናን ጋር ተከብሮ ውሏል። ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ይኽ ፳ኛ ዓመታዊ በዓል ከወትሮው ለየት የሚያደርገው ዐቢይ ነገር ቢኖር ቤተ ክርስቲያናችን በተመረቀ በመጀመርያው ዓመት የተከበረ ከመሆኑም በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተተኪ መዘምራን በተለይም ሕፃናት እውነትም የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ መሆናቸውን ያረጋገጡበት ልዩ ዝግጅት አዘጋጅተው በማቅረባቸው ነው። በበዓሉ መጀመርያ ቀን "እንኳን ደህና መጣችሁ" በማለት ዝማሬ ያቀረቡ ሕፃናት በተከታዩ ቀናትም ውዳሴ ማርያምን በቃላቸው ለምእመናን አሰምተዋል። በሦስቱም ቀናት ምእመናንን የሚያንጽ ወንጌል ተሰብኳል።

 

የቤዛ-ኵሉ ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በሰንበት ት/ቤቱ የተደረሱትንና ዜማ የተዘጋጀላቸውን ዝማሬዎች "በጽርሐ አርያም በቅዱሱ ቦታ" የሚለውንና "ሰላም ለእምነ ጽዮን" የተሰኙትን ዝማሬዎች አቅርበዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የቤዛ-ኵሉ ሰንበት ት/ቤት ከምሥረታው ጀምሮ የተጓዘባቸው ሒደቶች በዐውደ ርእይ መልኩ ለምእመናን ቀርቧል።

በመጨረሻም "የጨለማው ብርሃን" የተሰኘ ድራማ በሰንበት ት/ቤቱ አገልጋዮች የበዓሉ መጠናቀቂያ ዕለት እሑድ ሐምሌ ፲፯/፳፻፰ ዓ.ም. በታላቅ ተመስጦ ቀርቧል። ባለ ፵፰ ገጽ መጽሔትና በዓሉን የሚመለከት ቲ-ሸርት ተዘጋጅቷል።

 

 

ሰንበት ት/ቤቱ በዚህ በዓሉ ላይ መሪ ጥቅስ አድርጎ የተመራበት የእግዚአብሔር ቃል ከይሁዳ መልዕክት ላይ የተወሰደው "ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ..." (ይሁዳ ፩፡፫) የሚለው ሲሆን የቤዛ-ኵሉ ሰንበት ት/ቤትም የአባቶቹን ትክክለኛ ሃይማኖት በመጠበቅ ተተኪ ወጣቶችና ሕፃናትን በማስተማር በኩል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከአሁኑ በበለጠ እንደሚሠራ ይተማመናል። በዚሁ አጋጣሚም ሰንበት ት/ቤቱን ለማገልገል እና በቅድመ እግዚአብሔር ቆማችሁ መዘመር ለምትፈልጉ ሁሉ በራችን የተከፈተ መሆኑን እንድታውቁልን እንፈልጋለን። ልዑል እግዚአብሔር ሰንበት ት/ቤታችንን ይጠብቅልን። አሜን!!!

በአብርሃም ሰሎሞን