የበዓሉ ባለቤትና የዘመኑ አቆጣጠር ቀማሪ የሆነችው ቅድስት ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን አመቱን ሙሉ የተጠራቀመውን ቆሻሻ በክረምቱ ዝናም ታጥቦ ሲጠራ እና ምድር በአደይ አበባ ስትደምቅ ኢትዮጵያም ዘመኗን ትቀይር፣ አዲስ ዘመንም በደስታ ትቀበል ዘንድ ርእሰ ዓውደ ዓመት ብላ መስከረም በባተ በመጀመሪያው ቀን  ታከብራለች። የተስፋ እና የበጎ ውጥን ምልክት የሆኑ ወጣት ልጃገረዶች እንግጫ ጭንቅላታቸው ላይ አስረው፣ አደይ አበባ ታቅፈው በወዳጅ በጎረቤት ቤት እየዞሩ

አበባየሆሽ = አበባ አየሽ ወይ” እያሉ የሚያዜሙበት ፤ የሚሰጣቸውንም የበዓል በረከት ተቀብለው

ከብረው ይቆዩን ከብረው” ብለው ሲመርቁ የሚውሉበት ታላቅ በዓል ነው ዕንቁጣጣሽ።

ዕንቁጣጣሽ የሚለው ቃል የተለያየ መነሻ እና ትርጉም እንዳለው ይነገራል።  ንጉስ ሰለሞን ለንግስት ሳባ በወርኃ መስከረም “ ዕንቁ ለጣትሽ “ ብሎ ስለሰጣት ሲወርድ ሲዋረድ  ቃሉ አጥሮ ዕንቁጣጣሽ ሆኗል የሚል ትርጉም የሚሰጡ ይበዛሉ። የቃሉ መነሻ ከየትም ቢሆን ቤተክርስቲያናችን በታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ደግሞ እንደየባህሉና ወጉ በድምቀት የሚያከብረው ይሄ ቀን ታላቅ ነው።

የር/ አ/ጽ /አ/ቅ/ሥ/ቤ/ክን ምዕመናንም ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ ይሄን በዓል በታላቅ መንፈሳዊና ባህላዊ ሥርዓት እያከበርነው እንገኛለን።

 

 

አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ቀይ የሀገር ባሕል ልብሳቸውን ለብሰው፤ ቢጫ አደይ አበባ በእቅፋቸው ይዘው “አበባየሆሽ” እያሉ የሚዞሩ የቤዛ

ኲሉ ወጣት እህቶች ከምዕመናን እናቶችና ወጣቶች በየሄዱበት የሚያይዋቸው የደስታ ፊቶች ድካማቸውን አስረስቶ  ኃይማኖት እና ባህላቸውን  በተለየ አክብሮት እንዲያዩት የሚያደርግ በዓል ሆኗል። ቢጫ አደይ አበባ በእቅፋቸው ይዘው “አበባየሆሽ” እያሉ የሚዞሩ የቤዛ ኲሉ ወጣት እህቶች ከምዕመናን እናቶችና ወጣቶች በየሄዱበት የሚያይዋቸው የደስታ ፊቶች ድካማቸውን አስረስቶ  ኃይማኖት እና ባህላቸውን  በተለየ አክብሮት እንዲያዩት የሚያደርግ በዓል ሆኗል።

አሁንም በቸርነቱ ሌላ ዘመን የጨመረልን አምላካችን ሀገራችንን እንዲጠብቅልን፣ ወገኖቻችንን ከመከራ እንዲታደግልን እየለመንን የምናከብረው በዓል ሊሆን ይገባል። ይህን መልእክት ለምታነቡ ሁሉ መልካም አዲስ ዓመት እንመኛለን!

የአበባየሆሽ ግጥም

            ብለን መጣን ብለን መጣን (2)

ቸርነቱን አይተን  - - - ብለን መጣን ብለን መጣን

ምህረቱን አይተን - - - ብለን መጣን ብለን መጣን

አበቦችን ይዘን - - - ብለን መጣን ብለን መጣን

ቄጤማዉን ይዘን - - - ብለን መጣን ብለን መጣን

እሜቴ አሉ ብለን- - - ብለን መጣን ብለን መጣን

ጌቶች አሉ ብለን- - - ብለን መጣን ብለን መጣን

            አበባየሆሽ– - - ለምለም (2)

የጥፋት ዉሃ - - ለምለም - - - በጎደለ ቀን - - ለምለም

ለምለሙን አየህ - - ለምለም - - -  እርግቧን ልከህ - - ለምለም

እኛም መጥተናል - - ለምለም - - -  ቄጤማ ይዘን - - ለምለም

ሰላም ለእናንተ - - ለምለም - - -  ይሁን እያልን - - - ለምለም

            አበባየሆሽ– - - ለምለም (2)

ወደ ንሰሃ- - ለምለም - - - የሚጠራን - - ለምለም

በራችን ቆሟል - - ለምለም - - -  አዳኛችን - - ለምለም

እንቀበለዉ - - ለምለም - - -  በእምነት ሆነን - - ለምለም

እንዳይመለስ - - ለምለም - - -  እንዳያልፈን- - - ለምለም 

            ይሸታል የእጣን ጢስ ከቤተ መቅደስ

            ይሸታል ዶሮ ዶሮ ከማሚዬ ጓሮ

            ከብረዉ ይቆዩን ከብረዉ (2)

            ልቦና መንፈስ ገዝተዉ

            ቃሉን በትጋት ሰምተዉ

            ሥጋና ደሙን በልተዉ

            የፍቅር ሸማ ለብሰዉ

            ከብረዉ ይቆዩን ከብረዉ።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣

ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

በሰብለወንጌል ደምሴ