በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበረው የደብረ ታቦር በዓል  በርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቤዛ-ኩሉ ሰንበት ት/ቤት አዘጋጅነት ነሐሴ ፲፬  እና ፲፭  ቀን ፪ሺህ፰ ዓ/ም በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሰረት የደብረ ታቦር በዓል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ስጋዌው ሲከተሉት ለነበሩትና ለተመረጡት ሐዋርያት በደብረ ታቦር ተራራ ክብሩን የገለጸበትን ቀን  የምናስብበት ታላቅ መንፈሳዊ በዓል ነው፡፡ቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት የቤተ የክርስቲያንን ስርዓትና  ትውፊት መሰረት በማድረግ በዓሉን በቤተ ክርስቲያኗ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከካህናት አባቶችና  ከምዕመናን ጋር ባንድ ላይ በመሆን በታላቅ መንፈሳዊ ስነ ስርዓት አክብሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም  በሁለቱም ቀናት በቁጥር ሃያ የሚሆኑ  የሰንበት ትምህርት ወጣት መዘምራን በዓሉ የሚገለጽበትን የሆያ ሆዬ ዝማሬ በየምዕመናን ቤት እየተዘዋወሩ በማቅረብ ምዕመናን የበዓሉ በረከት ተካፋይ እንዲሆኑ ከማድረጋቸውም በላይ እሁድ ከቅዳሴ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ለምዕመናን የሆያ ሆዬ ዝግጅታቸውን በማቅረብ የበዓሉን መንፈሳዊ መልእክት ለምዕመናን አስተላልፏል፡፡

 

ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተደረገው የበዓል አከባበር መርሀ ግብር ሰንበት ት/ቤቱ የደብረ ያቦር የበዓል አከባበር ትውፊት እንዳይረሳና  ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ህጻናትና አዳጊዎች የበዓሉ ቀጥተኛ  ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ልምድ እንዲቀስሙ አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰንበት ት/ቤቱ በምዕመናን ቤት እየተዘዋወረ ባደረገው የሆያ ሆዬ አገልግሎት ሰላም፣ፍቅርና አንድነትን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ መስበክ የቻለ ሲሆን ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ በተጓዳኝ ከምእመናን የተለገሰለትን የገንዘብ ስጦታ በማሰባሰብ ለቤተ ክርስቲያን ገቢ ማድረግ ችሏል፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ  በቤዛ ኩሉ ሰንበት ት/ቤት በሆያ ሆዬ የተከበረው የደብረ ታቦር በዓል ሁሉንም ምእመናን ያሳተፈና ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው መንፈሳዊ ሀብት እንዲኮሩ ያደረገና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ደስ ያሰኘ በዓል ሆኖ አልፏል፡:

 

ወጣቶቻችን ካዜሙት የደብረ ታቦር (የቡሄ)ግጥሞች

 

ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና

 

ያዕቆብ ዮሃንስ ሆ! እንዲሁም ጴጥሮስ
አምላክን አዩት ሆ! ሙሴ ኤልያስ
አባቱም አለ ሆ! ልጄን ስሙት
ቃሌ ነውና ሆ! የወለለድኩት

 

ድምጽህን ሰማና በብሩህ ደመና
የቡሄው ብርሃን ለኛ መጣና።
መጣና መጣና ደጅ ልንጥና

 

        መጣና ባመቱ እንዴት ሰነበቱ፣
        ክፈት በለዉ በሩን የጌታዪን

 

ወስብሐት ለእግዚኣብሔር

ቤዛ ኩሉ ስራ አመራር ጽ/ቤት