በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፥ አሜን

ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን።”

ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ።” ፩ኛ ዮሐ ፫፥፰

ይህን ቃል የተናገረው ‘ጌታ ይወደው የነበረው’ ተብሎ በወንጌል የተጻፈለት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ፍቁረ እግዚእ እያለች የምትጠራው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉም ሆነ በመልእክታቱ የአምላክን ሰው መሆን እጅግ በሚደንቅ ኹኔታ ገልጦታል። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷም ነፍስን ነሥቶ የዲያብሎስን ሥራ በማፍረስ እኛን ቀድመን ወደነበርንበት ክብር እንደመለሰን ወንጌላዊው አስተምሮናል።

ይህን የጌታችንን የማዳን ሂደት ስንመረምር የመገለጡን ኹኔታም አብረን ማጤን ያስፈልጋል፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ዘመነ አስተርእዮ (የመገለጥ ዘመን) የምንለው ከጌታችን ልደት አንሥቶ እስከ እመቤታችን ዕረፍት ድረስ (ጥር ፳፩) ያለውን ጊዜ ነው። በዚህ ዘመን ከጌታችን ዐበይት በዓላት ልደቱና ጥምቀቱ፣ ከንዑሳን በዓላት ደግሞ ግዝረትና ቃና ዘገሊላ ይታሰባሉ። ከእነዚህ በዓላት በተጨማሪ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሰማያት ላሉ ነፍሳት መገለጧም ይታሰባል።

ጌታችን፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የጀመረው ሥጋን በመዋሐድ ነው። ለዚሁም መጽሐፍ “ቃልም ሥጋ ሆነ” ይለናል። (ዮሐ ፩፥፲፬) በእባብ ተሰውሮ የሰውን ልጅ ያሳተውን የሰይጣንን ሥራ ለማፍረስና የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ አምላካችንም የሰውን ሥጋ በመዋሐድ ዛሬውኑ ልደግ ሳይል ሕግ ጠባይዓዊን በመከተል ተወለደ። በመወለዱም ለሚወዱትና ለሚከተሉት የምሥራችና ክብር፣ ለሰይጣንና ለወዳጆቹ ደግሞ ውርደት ሆነ። ለሁሉ መሠረቱ መወለድ ነውና ይህን የሥራው መጀመሪያ አደረገው። ይህም ደግሞ የመገለጡ የመጀመሪያ ነበር። በተወለደ በስምንተኛው ቀን የመገረዝን ሥርዓት ለመፈጽም ሲል በተአምራት ምላጭ ሳይነካው እንደተገረዘ ሆኖ ተገኘ። ይህም ለኀጢአት ሥርየት በዕለተ ዓርብ ካልሆነ በስተቀር ደም መፍሰስ ስለሌለበት ነው።

ጌታችን በመጠመቁ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ለማወቅ ችለናል። አብ በደመና፣ ወልድ ውኃ ውስጥ፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በርግብ አምሳል በመሆን ምሥጢር ገልጸውልናል። ቀድሞ አምላኬ፥ አምላካችን ብቻ ይል የነበረውን የሰው ዘር አባታችን ማለት የሚችልበትን የልጅነት ጸጋ አልብሶታል።  በጥምቀቱ ጥምቀታችንን ባርኮታል፣ ኃይልም አጎናጽፎናል።

ጌታችን የመጀመሪያ ክብሩን የገለጠው በቃና ዘገሊላ በሠርግ ቤት ነው፤ ”ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” (ዮሐ ፪፥፲፩) ይህ ሠርግ ጌታችን በዶኪማስ ቤት በመገኘት ውኃን ወደ ወይን የቀየረበት ሠርግ ነው። ምንም እንኳን ተሰቅሎ ዓለምን የሚያድንበት ጊዜ ገና መሆኑን ቢገልጽም የእናት ልመና አንገት የማያስደፋ ፊት የማያስቀልስ መሆንን ሲያስረዳ እናቱ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጠየቀችውን ሁሉ እንደፈጸመላት እንመለከታለን። እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን የጌታችን በዓላት ልደቱን ታኅሣሥ ፳፱፣ ግዝረቱን ጥር ፮፣ ጥምቀቱን ጥር ፲፩፣ ቃና ዘገሊላን ጥር ፲፪ በማክበር እናስባቸዋለን።

ከእነዚህ በዓላት በተጨማሪ አስተርእዮን ስናንሣ እመቤታችንን አብረን የምናነሣበት ምሥጢር አለ ይኸውም እመቤታችን በስድሳ አራት ዘመኗ ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለማዊው መንግሥት የምትሄድበት ሰዓት ደርሶ ክብርት ነፍሷ ከክብርት ሥጋዋ ተለይታ በነበረችበት ሰዓት ሐዋርያት ለመቅበር ተሰብስበው እያዘኑ በመንገድ ሲሄዱ ትእቢተኞች አይሁድ ከመንገድ ጠብቀው እነዚህ ክርስቲያኖች “ልጇ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል” ብለው ሕዝቡን እንዳወኩ እሷም ትነሣለች ሊሉንም አይደል በማለት በምቀኝነት መንፈስ ተነሣስተው መቃብሩን ከሐዋርያት እጅ ለመንጠቅ በሚያሞክሩበት ሰዓት እግዚአብሔር አምላክ እመቤታችንንና ቅዱስ ዮሐንስን ነጥቆ ወደ ገነት ወስዷቸዋል። በዚህም ምክንያት እመቤታችን በሰማይ ላሉ ነፍሳት ተገለጠችላቸው፤ ነፍሳትም የአምላክን እናት በማየታቸው ሐሴት አደረጉ። ይህም ክንውን በቤተ ክርስቲያናችን ‘አስተርእዮ ማርያም’ በመባል ይታወቃል የእመቤታችን መገለጥ ማለት ነው።

ክርስቲያኖች፤ እግዚአብሔር አምላክ የቸርነቱ መጠን ወሰን የሌለው በመሆኑ ሁልጊዜም ቢሆን እኛን ለማዳን እጁ ያጠረበት ጊዜ የለም። ከእኛ የሚጠበቀው ህጉን ትእዛዛቱን መከተልና መጠበቅ፣ እርስ በእርሳችን መዋደድ ያስፈልገናል። እንዲህ ካደረግን የዲያብሎስ ዓላማም ሆነ ሥራ ይፈርሳል፤ የእግዚአብሔር መንግስት ወራሾችም እንሆናለን።

የእግዚአብሔር ቸርነት፣

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣

የቅዱሳን በረከት አይለየን፥ አሜን

ወይትባረክ አምላከ አበዊነ

ቤካ መገርሳ