"ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ" ሉቃ፣ ፪ ፥ ፲፬

ሥርዓተ ቅዳሴ የሚለውን ቃል ስንመለከት "ሥርዓት" ማለት አሠራር፣ አፈፃጸም ተብሎ የሚተረጎም ሲሆን "ቅዳሴ" ደግሞ ምሥጋና ማለት ነው፤ ይኸውም ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር ለእግዚአብሔር የሚቀርብምሥጋና ማለታችን ነው። እንግዲህ ቅዳሴ በሐዲስ ኪዳን የተጀመረው በቤተ ልሔም ሲሆን የጀመሩትም ሰማያውያን መላእክት ናቸው፤ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአባታችን ለአዳም በ፭ሺ ፭መቶ ዘመን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ያለው አምላካዊ የተስፋ ቃል ሲፈጸም ቤተ ልሔም በምትባል የዳዊት ከተማ "ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ" ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ እያሉ ሰማያውያን መላእክት እንዳመሰገኑ በሉቃስ ወንጌል ምዕ. ፪ ቁ፥፲፬ ተጽፎ እናገኛለን።

የቅዳሴ አገልግሎት ማከናወኛ/መፈጸሚያ/ የሆነው ሥርዓታችን የተጀመረው ለስም አጠራሩ ክብር ምሥጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ለደቀ መዛሙርቱ ኅብስቱን አንሥቶ ባርኮ ቆርሶ  “እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ጽዋውንም ይዞ አክብሮ አመስግኖ ሁላችሁም ከእርሱ ጠጡ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” በማለት የቅዱስ ቁርባንን ሥርዓት ሲሰጠን ነው።  ማቴ. ፳፮፣ ፳፮፥፳፱  ማር፥ ፲፬፣ ፳፪፥፳፭

ሥርዓተ ቅዳሴ /የቅዳሴ ሥርዓት/ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጸሎት ሁሉ በላይ የሆነ፤ ምስጋናውን ከሰማያውያን መላእክት፣ ሥርዓቱን በአባቶቻችን ሐዋርያት አማካኝነት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነው ታላቅ ጸሎትና በሀገራችን በኢትዮጵያ እንዲሁም አመቺ በሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን በተስፋፋችባቸው የውጪ ሀገራት ሳይቋረጥ ዕለት ዕለት የሚፈጸም ሥርዓት ነው። የቅዳሴ ሥርዓት አገልግሎት በሚፈጸምበት ቦታ ቅዱሳን መላእክት እንደ ቅጠል ረግፈው፣ እንደ ሻሽ ተነጥፈው የሚያከብሩት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ኅብስቱን በጻሕል፣ ወይኑን በጽዋ በማቅረብ ኅብስቱ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር፤ ወይኑ ደመ ወልደ እግዚአብሔር ሆኖ የሚለወጥበትን ሥርዓት የምታከናውንበት ጸሎት ነው።

የቅዳሴ ሥርዓት ካህናትና ምእመናን በአንድነት በመሆን ለአምላካችን ምስጋና የምናቀርብበት፣ ለበደላችን ይቅርታና ምሕረት የምንጠይቅበት፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ኅብስቱና ወይኑ የሚለወጥበት የጋራ የጸሎት ክፍለ ጊዜ ነው፤ በቅዳሴ ጸሎት "እግዚኦ ተሣሃለነ" አቤቱ ይቅር በለን "ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ…" አቤቱ በመንግሥትህ አስበን "ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ…" አቤቱ ሞትህንና ልዩ የሚሆን ትንሣኤህን እንናገራለን በማለት "እኔ" ብለን ሳይሆን "እኛ" እያልን ከፈጣሪያችን ጋር የምንገናኝበት የጸሎት ሰዓት በመሆኑ በቅዳሴ ጊዜ የግል ጸሎት የተከለከለ ነው። ከሁሉም በላይ ልናስተውለው የሚገባን በቅዳሴው አገልግሎት ከግል ጸሎት ተቆጥበን ኅሊናችንን በመሰብሰብ ስንሣተፍ /ስንቀድስም ሆነ ስናስቀድስ/ የጸሎቱ/የሥርዓቱ/ ተካፋዮች መሆናችንን ነው።

በቅዳሴ ጸሎት በመሳተፋችን የኃጢአት ስርየት እናገኛለን፤ በረከተ ሥጋም በረከተ ነፍስም እንታደላለን፤ ከሁሉም በላይ የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን በልተን ክቡር ደሙን ጠጥተን የዘለዓለም ሕይወትን እናገኛለን።

ሌላው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢቱ ምዕራፍ ፮ ቁጥር ፫ ላይ "አንዱም ለአንዱ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኸ ነበረ" ያለውን ቃል መሠረት አድርገን የሰማያውያን መላእክት ምግብ የሆነውንና እነርሱ ፳፬ ሰዓት ያለማቋረጥ "ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር" እያሉ የሚያመሰግኑትን ምስጋና በሥርዓተ ቅዳሴ ውስጥ ስለምናገኘው እኛም በፍፁም መንፈሳዊነትና፣ በንፁሕ ኅሊና ከቤተ ልሔም /ከጌታ መወለድ/ ተጀምሮ እስከ ቢታንያ /የጌታ ዕርገት/ ድረስ ያለውን ነገረ ክርስቶስ እያሰብንና ሥርዓቱን እየፈፀምን/በካህናት አባቶችና በዲያቆናት ሲፈጸም/ እያየን ሥርዓቱን በማክበርና የቅዳሴውን ጸሎት በመጸለይ የመላእክትን ሕይወት የምንኖርበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን

ሥርዓትና፣ የሃይማኖታችን ምሰሶ ነው።

የተወደዳችሁ የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች ከብዙ በጥቂቱ ስለ ሥርዓተ ቅዳሴ ይህን ካልን በልማድ ከመመላለስ፣ የቅዳሴውን አገልግሎት እንደ ሥራ ከመቁጠርና፣ ይህን ከመሳሰሉ ደካማና፣ በክርስትና ሕይወት ከሚታዩ የስንፍና አስተሳሰቦች በመራቅ የቅዳሴውን ጸሎት ጥቅሙን በመረዳት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንምጣ። ወደ ቅዳሴውም ስንመጣ የሚጠበቅብንን የነፍስ፣ የኅሊናና፣ የዕውቀት፣ ዝግጁነታችንን በመፈተሽ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት የማክበር መንፈሳዊ ግዴታችንን በሚገባ ተገንዝበን በሥርዓተ ቅዳሴው በመሳተፍ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እንድናገኝ፤ በንስሐ ሕይወት እየተመላለስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙንም ተቀብለን የዘለዓለም ሕይወት ርስተ መንግሥተ ሰማያትን እንወርስ ዘንድ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን።                                                                                  

            ሊ/ብ ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ