ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል በዘመነ ሐዲስ ኪዳን ከእግዚአብሔር ተልእኮ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቅ የብሥራት ዜና ይዞ በመጣ ጊዜ የብሥራቱ መደምደሚያ ያደረገው ዓረፍተ ነገር «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና» የሚለውን ነበር። በስድስት ወራት ልዩነት ወደ ሁለት የተለያዩ ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተላከ እንረዳለን፤ በመጀመሪያ ወደ ጻድቁ ዘካርያስ፣ ቀጥሎም ወደ እመቤታችን።

ወደ ሁለቱም የተላከው ለተመሳሳይ የብሥራት ዜና ነው ፤ ለዘካርያስ ዮሐንስ የሚባል ቅዱስ ልጅ እንደሚወልድ እና የጌታን መንገድ እንደሚያሰናዳ ሲገልጽለት ለእመቤታችን ደግሞ ጌታን እንደምትወልድ አብሥሯታል። ሁለቱም ቅዱስ ገብርኤልን በጥርጣሬ መልክ ጥያቄ ጠይቀውታል።

ጻድቁ ዘካርያስ ሽማግሌ መሆኑን ሲያስረዳ እመቤታችን ደግሞ እንዴት ያለወንድ ልጅ መውለድ ይቻላል? በማለት ጠይቃለች። ለተመሳሳይ ብሥራት የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ግን አመላለሱ በጣም የተለያየ ነበር።  "በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ፣ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ድዳ ትሆናለህ፣ መናገርም አትችልም" ( ሉቃ ፩ ፤፳) በማለት ለጻድቁ ዘካርያስ በአንድ ግዜ ሲመልስለት ለጌታ እናት ግን መጀመሪያ ከሰላምታው ሁኔታ፣ ቀጥሎ ደግሞ ያለ ተፈጥሮ ህግ እንዴት ሰው ይወለዳል? የሚል ጥያቄም ብታስከትልበትም እንደ ትሁትና ቅን አስተማሪ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ እና ምሥጢረ ሥጋዌ ካስረዳት በኋላ በመጨረሻ ላይ " ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና" በማለት የሐሳቡ መቋጫ አድርጎታል።

 

በእውነትም በስሙ ላመኑትና እንደ ፈቃዱም ለሚጓዙት ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም። ሰለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣ እግዚአብሔር ፣ ህፃኑ ቂርቆስን እና እናቱ ኢየሉጣን ያዳነ መድኃኔዓለም ዛሬም የበረከት እጁን እንደዘረጋ ነው። በቤተ ክርስቲያናችን በሀገራችን በአጠቃላይ በዓለማችን ላይ ከተጋረጠው እሳት እግዚአብሔር አምላክ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንዲታደገን የጸሎት ሕይወታችን መበርታት አለበት። የቀደሙት አባቶቻችንንና እናቶቻችንን የተራዳ ቅዱስ ገብርኤል እኛንም በተራዳኢነቱ እንዲጎበኘን የአምላካቸን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን። አሜን።