በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ሐምሌ ፭ ቀን ጴጥሮስ ወጳውሎስ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መልካሙን የክርስትና ገድል ተጋድለው ሰማዕትነት የተቀበሉበትን ቀን በታላቅና በተለየ ሁኔታ ታከብራለች። ክርስትናን በማስፋፋት ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት እነዚህ ቅዱሳን አባቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልእክታትን ጽፈዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምንት ምዕራፎችን የያዘ ሁለት መልእክታትን ሲጽፍ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ አንድ መቶ ምዕራፎችን የያዘ አሥራ-አራት መልእክታትን ጽፏል። ለአግልግሎት የጠራቸውም የክብር ባለቤት የሆነው አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

 

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ ሳለ ለዚህ ታላቅ አገልግሎት ሲጠራ (ማቴ ፬፦፲፰) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ቤተክርስቲያን እና የክርስቶስ ተከታዮችን በማሳደድ ላይ ሳለ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል (ሐዋ. ፱፡፬-፭) በሚል አጠራር የተጠራ ነው።

 

እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ብዙ የሚመሳሰሉበት ነገር ቢኖራቸውም ብዙ የማይመሳሰሉባቸው ነገሮችም አሏቸው። ነገር ግን ሁለቱም በአምላካችን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠርተው ሰማያዊ አገልግሎትን በምድር ሆነው አሳይተውናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ቀድሞ ለአገልግሎት የተጠራው ጌታችን በምድር ላይ ሳለ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ከጌታ ዕርገት በኋላ የተጠራ ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ያገባ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ያላገባ ነው።

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መጽሐፍ የማያውቅና ያልተማረ ነው። መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ይለናል፦ (የካህናት አለቆችና ሹማምንቶች ጴጥሮስና ዮሐንስም በግልጥ እንደ ተናገሩ ባዩ ጊዜ፥ መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውለው አደነቁ።) ሐዋ. ፬፡፲፫ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ፈጽሞ የተማረና ሕግንም ጠንቅቆ ያውቅ የነበረ ሰው ነው። መጽሐፍ ቅዱስም እንዲህ ይለናል፦ (እኔ የኪልቅያ በምትሆን በጠርሴስ የተወለድሁ፥ በዚችም ከተማ በገማልያል እግር አጠገብ ያደግሁ፥ የአባቶችንም ሕግ ጠንቅቄ የተማርሁ፥ ዛሬውንም እናንተ ሁሉ እንድትሆኑ ለእግዚአብሔር ቀናተኛ የሆንሁ አይሁዳዊ ሰው ነኝ።) ሐዋ. ፳፪፡፫

እንግዲህ በእግዚአብሔር ፊት እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ቀድሞ መጠራት፣ በጋብቻ መኖርና፣ መጽሐፍን ጠንቅቆ አለማወቅ መመዘኛ ሊሆን አይችልም። በአንፃሩም በመጨረሻው ሰዓት መጠራት፣ በጋብቻ አለመያዝ እና መጻሕፍትን ጠንቅቆ ማወቅ መመዘኛ ሊሆን አይችልም። በፈቃደ እግዚአብሔር መኖርና የእግዚአብሔርን ሕግ በሚገባው ተከትሎ መገኘት ካለ ያገባም ያላገባም፣ የተማረም ያልተማረም እንዲሁም ቀድሞ የተጠራም አመሻሽቶ የተጠራም ሁሉም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አላቸው።

ሁለቱ ሐዋርያት ከአጠራራቸው ጀምሮ የተለያየ ሁኔታ ቢታይባቸውም ለእግዚአብሔር አገልግሎት ግን በተሰጣቸው የሥራ ድርሻ በታማኝነት ያገለገሉ ናቸው። ከላይ በመግቢያው ላይ እንደገለጽነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የሚመሳሰሉበት ሁኔታ ከዚህ እንደሚከተለው ይሆናል፦

፩- ሁለቱም አይሁዳውያን ናቸው፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁዳዊ ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈውን መልእክት ስንመለከት እንዲህ ይለናል፦ ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። (ገላ. ፪፡፲፬)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አይሁዳዊ ለመሆኑ እንዲህ በማለት ባስተላለፈው መልእክት ለማወቅ ይቻላል፦ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ (ፊልጵ.፫፡፭)

 

፪- ሁለቱም በጌታ የተጠሩ ናቸው፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የተጠራው አሳ ሲያጠምድ ነው። ጌታ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። እርሱም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ወዲያውኑ መረባቸውን ትተው ተከተሉት። (ማቴ. ፬፡ ፲፰-፳)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጌታ የተጠራው ወደ ደማስቆ ይጓዝ በነበረበት ጊዜ ነው። ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ። ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም። አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው። (ሐዋ. ፱፡፩-፭)

፫- ሁለቱንም ጌታ ስማቸውን ለውጦታል፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አስቀድሞ የዮና ልጅ ስምዖን ተብሎ ይጠራ ነበር። (ዮሐ. ፳፩፡፲፭) ጌታም ጴጥሮስ ብሎ ስያሜ አወጣለት። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። (ማቴ. ፲፮፡፲፯-፲፰) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ ለአገልግሎት ሲጠራ ስሙ ሳውል ተብሎ ይጠራ ነበር። በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። (ሐዋ. ፱፡፬) በአገልግሎቱ ጽናት ጳውሎስ የሚል ስያሜ ተሰጠው።

- ሁለቱም ድንቅና ተአምራትን አድርገዋል፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስላደረገው ድንቅ እንዲህ ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፏል፦ ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ። በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ። ጴጥሮስም። ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ አለው። ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ አይተውት ወደ ጌታ ዘወር አሉ። (ሐዋ.፱፡፴፪-፴፭)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ታላላቅ ተአምራቶችና ድንቅ ስለማድረጉ፦ እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። (ሐዋ. ፲፱፡፲፩-፲፪)

- ሁለቱም ሙታንን አሥነስተዋል፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታ የተባለችውን ብላቴና ስለማሥነሳቱ፦ በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች። በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች። እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት። (ሐዋ. ፱፡፴፮-፵፩)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አውጤኪስን ከሞት ስለማሥነሳቱ፦ አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም። ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው። ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ። (ሐዋ. ፳፡፯-፲፪)

፮- ሁለቱም የሰማዕትነት አክሊል አግኝተዋል፦

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በስልሣ ሰባት ዓ.ም. በኔሮን ቄሣር እጅ ቁልቁል ተሰቅሎ ሕይወቱን አጥቷል (ሰማዕትነትን ተቀብሏል)። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በስልሣ ሰባት ዓ.ም. በኔሮን ቄሣር እጅ አንገቱን ተቆርጦ ሕይወቱን አጥቷል (ሰማዕትነትን ተቀብሏል)

 

የቅዱሳኑ በረከት ዘወትር ከእኛ ጋር ይሁን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!

አብርሃም ሰሎሞን

 

ምንጭ፦

መጽሐፍ ቅዱስ

ጥሩ ምንጭ (ኅሩይ ወልደ ሥላሴ) ፲፱፻፺፭

SAINT PETER AND PAUL (POPE SHENOUDA)