በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ቤተሰብ

  • ሕፃኑም ዮሐንስ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል። (ሉቃ ፩፥፲፭)
  • ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት። (ሉቃ ፩፥፵፩)
  • አባቱ ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ። (ሉቃ ፩፥፷፯)  

ጽሐፍ ቅዱስ የዚህን ታላቅ ቤተሰብ ታሪክ በሉቃስ ወንጌል ላይ ካህኑ ዘካርያስ እና ከካህኑ ከአሮን ወገን የሆነች ኤልሳቤጥ ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለ ነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ በማለት ይገልፃል። የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የልደት ታሪክም እንዲህ በሚለው በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ይጀምራል፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። (ሉቃ ፩፥፲፭-፲፯)

የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሕግጋት እየጠበቀ በቅድስና ይኖር የነበረው ካህኑ ዘካርያስ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣውን የቅዱስ ገብርኤል ቃል ባለመስማቱ ሕፃኑ እስከሚወለድ ድረስ ድዳ እንደሚሆን በአብሳሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ተነገረው። ይወለዳል የተባለው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን የኤልሳቤጥ መፅነስ በቤተሰቡ መካከል ለረጅም ጊዜ ይፈለግ የነበረ ስለነበር ደስታ ሲፈጥር የካህኑ ዘካርያስ ድዳ መሆን ደግሞ ቤተሰቡን የሚያስጨንቅ ሌላ ክስተት ሆነ። ቅድስት ኤልሳቤጥም ባለመውለዷ ምክንያት በአካባቢው ሰዎች ግን እግዚአብሔር እንዳዘነባትና ልጅ እንደከለከላት ይነገርባት ስለነበር የልምላሜዋ ዘመን ካለፈ በኋላ መፅነስ በመቻሏ ነቀፌታዬን ከሰው መካከል ያስወግድልኝ ዘንድ ጌታ በተመለከተበት ወራት እንዲህ አድርጎልኛል (ሉቃ ፩፥፳፭) በማለት ደስታዋን ገልፃለች።

አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ተብሎ እንደተነገረው የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካክሉ በማለት ፊት አውራሪ ሆኖ የሚላከውን ቅዱስ ዮሐንስን የፀነሰችው ቅድስት ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ልትጠይቃት ወደ እርሷ በሔደች ጊዜ እጅግ የሚያስገርም ሁኔታ ተፈጠረ። ይኸውም  ቅዱስ ዮሐንስ በማኅፀን ውስጥ ኾኖ ለቅድስት ድንግል ማርያም እና በማኅፀኗ ላለው ለዓለም መድኃኒት ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰግዷል (ሉቃ. ፩፥፳፮-፵፩)

 

ሕፃኑም ከተወለደ በኋላ አባቱ ካህኑ ዘካርያስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እንደዚህ አለ፦ ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። (ሉቃ ፩፥፸፮-፸፱)

በዚያም ዘመን ሄሮድስ የአምላካችን፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ ከሰብአ ሰገል ሲሰማ መንግሥቴን ይወስድብኛል ብሎ በመፍራቱ የቤተልሔም ሕፃናትን መግደል የመጀመርያ ውሳኔው ሆነ። (ማቴ. ፪፥፩-፲፮) ቅድስት ኤልሳቤጥም ልጇን ዮሐንስን ይዛ ወደ ምድረ በዳ ተሰደደች። የአዋጅ ነጋሪው ቃል ተብሎ የተነገረለት ቅዱስ ዮሐንስ ጊዜው ሲደርስ ከነበረበት በረሐ ድምፁን እያሰማ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ! እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ሁሉ ወጣ። (ሉቃ. ፫፥፫-፮) ።

በስብከቱም እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፤ ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ፤ ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ፤ በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፤ ይል ነበር። (ሉቃ. ፫፥፯-፲፬) ።

የትሕትና አባት የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ ሊጠመቅ ወደ እርሱ ሲመጣ እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? በማለት የጌታችንን አምላክነት ፍጹም በሆነ ትሕትና ተናግሯል (ማቴ. ፫፥፲፬) ። ብዙ ተከታይ የነበረውና በስብከቱ የብዙ ሰዎችን ቀልብ የገዛው ቅዱስ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር ሙሽራይቱ ያለችው እርሱ ሙሽራ ነው፤ ቆሞ የሚሰማው ሚዜው ግን በሙሽራው ድምጽ እጅግ ደስ ይለዋል። እንግዲህ ይህ ደስታዬ ተፈጸመ። እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል። (ዮሐ ፫፥፳-፱-፴) በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር የሚገባውና ከሁሉ የበለጠ ሙሽራ መሆኑን ተናግሯል። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ካህን፣ መምህር፣ ሐዋርያ፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ እና ሰማዕት ነው። ሊቁም ከሰማይ መላእክት ወገንም ሆነ በምድር ካሉ ቅዱሳን፣ ነቢያት፣ ካህናት፣ መምህራንና ሐዋርያት መካከል ማንም እንደ ቅዱስ ዮሐንስ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ ዮሐንስ ሆይ ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ሆነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም ሲል ተናግሮለታል። (መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ) ።


ሰኔ ፴ ቅዱስ ዮሐንስ የተወለደበትን ቀን ቤተ ክርስቲያን በቅዳሴ  እና ታቦት በማውጣት ታከብራለች። በጌታ የተወደደ እና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ሆኖ አምላክን ለማጥመቅ የታደለው የቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት አይለየን፣ መንፈስ ቅዱስን ተሞልተው ድንቅ ያደረጉና ሕያው ምስክርነትን የሰጡት የመላው ቤተሰብ በረከትም ከሁላችን ጋር ይሁን።

ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር፤

ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ።

ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ