Print

እግዚአብሔር አምላክ መላእክትን እና የሰውን ልጆች ስሙን እንዲቀድሱ ክብሩን እንዲወርሱ ፈጥሯቸዋል። ለዚህም ቅዱስ ዳዊት ዘይሬስዮሙ ለመላእክቲሁ መንፈስ ወለክለ ይትለአክዎ ነደ እሳት” እንዲል (ዕብ. ፩፡፯)። ፈጥሯቸውም በሦስት ከተሞች በኢዮር፣ በራማ እና በኤረር አሰፈራቸው።

በኢዮር አርባውን ነገድ በማስፈር ለአራት ከፍሎ አጋእዝትን ኪሩቤልን ሱራፌልንና ኃይላትን አድርጓል፤ የኃይላትን አለቃ ቅዱስ ሚካኤልን ሾሞታል “ሚካኤል ሥዩም በዲበ ኃይላት” እንዲል ኋላም በአጋእዝት ላይ አለቃ የነበረው ሰማልያል ሲወድቅ ቅዱስ ሚካኤል በአጋእዝት ላይ ሥልጣን ተቀዳጅቷል። “አሁን የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ መጥቻለሁ” እንዲል። (ኢያ. ፭፡፲፬)የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ስልጣኑ አለቅነቱ በእግዚ አብሔር ሠራዊት ሁሉ ላይ ታዳጊነቱ እርዳታውም ለሁሉም ፍጡር ነው። ይኸው እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ጎርፍ ፈሳሽ ሳይሆን የሕይወት መመሪያችን በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፍ. ፵፰፡፲፮ ላይ እናገኘዋለን። ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” (ዘፍ. ፳፰፡፲፪) በማለት እንደተጻፈው በምድረ ሎዛ የመላእክትን የሰው ልጅ ልመና ወደ እግዚአብሔር ሲያደርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰው ልጆች ሲያመጡ በመሰላል አምሳል ከፍቶ ትድግናቸውን አስቀምጦልናል። የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን እንዲይዙ የአብርሃምን የይስሐቅን የያዕቆብን የሃይማኖት መሪነት አደራ እንዲሸከሙ ለቀጣዩም ትውልድ እንዲያሸጋግሩ ሁለቱን የልጅ ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ለኔ ይሁኑ ሌሎቹ ግን ላንተ ይሁኑ ካለ በኋላ በአመስቅሎ እድ የአባትነቱን ቡራኬ ከሰጠ በኋላ “ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” በማለት የአባቶችን አደራ ለመረከብ የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ እንደሚያስፈልግና በሕይወታችን በኑሮአችን ውስጥ ዕለት ዕለት መሆናቸውን የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳናል።

ነብየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ሰይጣን እሥራኤልን እንዲቆጥር ባነሳሳው ጊዜ በዐውደ አርና ኢያቡሳዊት ዓይኑን አነሣ የእግዚአብሔር መልአክም በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ  የተመዘዘ ሰይፉንም በእጁ ሆኖ ባየ ጊዜ በፊቱ በመስገድ መቅሰፍቱን እንዲያርቁ ለምኖታል፤ በዚያም መሥዋዕት አቅርቦ ተቀባይነት እንዳገኘ በአንደኛ ዜና ፳፩፡፲፮ ተጽፎ እናገኛለን።

እንዲሁም “በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ በዚህ ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ የለም” (ዳን. ፲፡፳፩)። ታላቁ ነብይ ዳንኤል በእውነት ጽሑፉ የተጻፈውን እነግርሃለሁ በማለት የመጋቤ ብሉይ ተራዳኢ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን በማያሻማ መልኩ አስቀምጦልናል።

ወበእንተ ዝ ተገብረ ሎቱ በዓል ስለክብሩና ስለ አማላጅነቱ ወር በባተ በየአሥራ ሁለት ቀን መታሰቢያውን እንድናደርግ አዘዙን ከምን አግኝተው ቢሉ በመጽሐፈ መሳፍንት ፲፫፡፲፯-፲፱ እንዲህ የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን “ የእግዚአብሔር መልአክም ተአምር አደረገ ማኑሄም መልአኩን የነገረህን በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ይባላል ለምንት ትሴአል ስምየ ወመድምም ውእቱ”  ብሎታል ማኑሄም የፍየል ጠቦት ወስዶ ለመሥዋዕት አቀረበ

የእግዚአብሔር መልአክ ከመሠዊያው ነበልባል ጋር ወደ ሰማይ አረገ። ስሜም ድንቅ ነው “ ሚካኤል ብሂል ዕፁብ ነገር” እንዲል ደራሲ። በመሆኑም ዛሬም ለኛ በሚያደርግልን ተአምራት እናከብረዋለን ስእለታችን ሲደርስ ለቅዱስ ሚካኤል ነግሬው ነበረ ብለን ነገራችን በደረሰልን ጊዜ ስሙን እናነሳለን።

የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያኅዳር 12 እና ሰኔ 12 በታላቅ ድምቀት የሚከበርበት ነው። የሰኔ 12 ቀን የሚከበርበት ምክንያት አባ እለ እስክንድሮስ የተባለ አባት ሊቀ ጳጳሳት በሆነበት ወራት የግብፅ ንጉስ የበጥሊሞስ ልጅ ዙሐል የሚባል የኮከብ ጣዖት ሠራች “ወኮነ በውእቱ ምኩራብ ጣዖት ዘብርት” እንዲል በጣም ታላቅና በአውራጃው የገነነ ከ300 ዓመት በላይ የቆየ ወገብሩ ሎቱ በዓል አመ 12 ለወርኃ ሰኔ በዚያም አባ እለእስክንድሮስ ያንን የጣዖት ምኩራብ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመቀየር ማኑሄ መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር እንዳቀረበ ለጣዖት ይሠዋ የነበረ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር እንዲሆን በማድረግ የሊቀ መልአክት የቅዱስ ሚካኤልን ታቦት አስገብቶ ቅዳሴ ቤቱን አክብረውበታል። ወተሠረዓ ዝንቱ በዓል እስከ ዛቲ ዕለት ይህ በዓል ሆኖ እስከ ዛሬ ተወሰነ።

በዚህች ቤተ ክርስቲያን በየወሩ የቅዱስ ሚካኤል ዝክር የሚያዘክሩ መታሰቢያውን የሚያደርጉ ወፈድፈደሰ በኅዳር ወበሰኔ ባልና ሚስት ነበሩ በጎረቤቱም ይህን ሥራቸውን የማይወድ ሀብታም ይኖር ነበር። ይህም በጎ ሰው ከብዙ ጊዜ በኋላ አረፈ ሚስቱም ፀንሳ ነበር በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት መልኩ በጣም ያማረ ልጅ ወለደች ቅዱስ ሚካኤል ሕፃኑን ባረከው እና የዚህን ንፉግ ባለፀጋ ሀብት እንዲወርስ አዝዟል ብሎ ሲናገር ያደምጥ ነበር። መልአኩን የተናገረውን ሰምቶ ሕፃኑ  አሥር ዓመት ሲሞላው በሳጥን አድርጎ ወደ ባሕር ወርውሮታል በሊቀ መልአኩ ታዳጊነት እሩቅ ሀገር አንድ በግ እረኛ አግኝቶት ስሙን ባሕራን ብሎ አሳድጎታል። ዮናስ በዓሣ ነባሪ ሆድ ሦስት ቀን ያሳደረ አምላክ ይህንንም ባሕራንን ከክፉ ነገር ሁሉ ጠብቆ ከዚያ አድርሶታልና ኋላም ይኸው ባለፀጋ ከነባሕራን ቤት በእንግድነት አድሮ የባሕራንን የስሙን ትርጉም ወራቱን ዓመታቱን ጠይቆ እሱ ወደ ባሕር የወረወረው መሆኑን በመረዳቱ ደብዳቤ በመጻፍ እንዲገድሉት “ቅትሎ ወግድፎ ውስተ ግብ” ብሎ ሰጥቶት ይህቺን የሞት ደብዳቤ ሊቀ መልአክ ለነማኑሄ በሰው አምሳል እንደተገለጠው ለባህራንም በንጉሥ ስፍራ አምሳል ተገልጦ ወደ ሕይወት ቀይሮለታል “እስመ አነ ወሀብክዎ ኮሎ ንዋይየ” በቤት ያለኝን ሁሉ ሰጥቸዋለሁ።

ባሕራንም የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ ሲያደርግ ቀሲስ ሆኖ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያገለግል ኖረ። ያን ጊዜ ማኑሄ የእግዚአብሔርን መልአክ መሆኑን አወቀ መሳ. ፲፫፡፳፩ እንዲል ባሕራን ከመንገድ ላይ የተገለጠለት የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን መሆኑን አወቀ።

በመንገድህ ይጠብቅህ ዘንድ ወደ አዘጋጀሁልህ ስፍራ ያገባህ ዘንድ እነሆ መልአኬን በፊትህ እልካለሁ ስማው እምቢ አትበለው ስሜ በእርሱ ስለሆነ። ሁላችንንም ከክፉ ነገር ሁሉ ያድነን ወደ ተዘጋጀልን ሥፍራ እስክንገባ በክንፈ ረድኤቱ ይጠብቀን በአማላጅነቱና በተራዳኢነቱ እንማፀን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

 ቀሲስ በለጠ ጓሉ