ኅዳር ፳፬ ቀን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ነውና የሰማይን ሥርዓት በምድር ያለማቋረጥ ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እግዚአብሔር በማለት ለሚያመሰግኑት ካህናት የተጻፈ ሥነ-ግጥም፦

 

ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ አምላክ ነህ እያሉ፣

መላእክት በሰማይ ያመሰግናሉ።

ግብራቸው ነውና እግዚአብሔርን ጠርተው፣

ቅዱስ ቅዱስ ማለት በምስጋና ቆመው።

የሰማይ ሥርዓት ሲፈጸም በምድር፣

ከእግዚአብሔር ተሰጥቷል ለካህናት ክብር።

እንደ መላእክቱ እነርሱም ተመርጠው፣

በምድር ይኖራሉ ስመ እግዚአብሔር ጠርተው

ዘወትር በአምላክ ፊት ለማቅረብ ምስጋና፣

ማልደው ይነሣሉ ግብራቸው ነውና።

 

ለፈጠረው አምላክ ሕይወትን ለሰጠው፣

ከባርነት ወጥመድ ከእስር ላላቀቀው፣

ተመስገን እያለ በአምላክ ፊት ይቆማል፣

ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት ምስጋና ያቀርባል።

 

መጸለዩንማ ማንም ይጸልያል፣

ቃል ኪዳን ነውና የካህን ይለያል።

የምእመናን ጸሎት ዋጋ አለው ይሰማል፣

የካህን ጸሎት ግን መሥዋዕት ያሳርጋል።

 

ምሥጢረ ጥምቀትን ምሥጢረ ሜሮንን፣

ምሥጢረ ንስሐ ምሥጢረ ቁርባንን፣

ምሥጢረ ጋብቻ ምሥጢረ ቀንዲልን፣

ታላቁን ስጦታ ምሥጢረ ክህነትን፣

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያሏትን ምሥጢራት፣

ፈጻሚዎች ናቸው የእግዚአብሔር ካህናት።

 

በማቴዎስ ወንጌል ባስተማረው ትምህርት፣

ምዕራፍ አሥራ-ስምንት ቁጥር አሥራ-ስምንት፣

የክህነትን ሥልጣን ሲሰጣቸው ሀብቱን፣

እንዲህ ብሏቸዋል ደቀ መዛሙርቱን፣

 

በምድር የምታስሩት በሰማይም ታስርዋል፣

በምድር የምትፈቱት በሰማይ ተፈትዋል፣

መፍታት ይችሉ ዘንድ የበደል ማሰሪያን፣

ኢየሱስ ክርስቶስ ሰጥቷቸዋል ሥልጣን።

ለእነማን ተሰጥቷል እንዲህ ያለው ሥልጣን፣

ለካህናት እንጂ ለእግዚአብሔር ቅዱሳን።

 

ቀድሶ አቁራቢ ነው ንስሐ ተቀባይ፣

ቅዱስ ቅዱስ የሚል በምድር እንደ ሰማይ።

ክብሩ የሚስተዋል በገሐድ የሚታይ፣

ምስጋና ነው ሥራው የእግዚአብሔር አገልጋይ።

 

በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ተሰጥቶታል፣

ሰውና እግዚአብሔርን ካህን ያገናኛል።

እንዲህ ብሏል ጳውሎስ መልዕክቱን ሲናገር፣

የአምላክን ስጦታ የክህነትን ነገር።

ማንም ካህን አይሆን በእርሱ ቃል እንዳሻው፣

እግዚአብሔር እንደ አሮን አክብሮ ካልጠራው።

 

የት እንደደረሱ ማን እንደቀጣቸው፣

ቆሬ አቤሮን ዳታን ምስክሮች ናቸው።

ሳይጠሩ ቆመው በክህነቱ ቦታ፣

ውጣ አስቀረቻቸው ምድሪቱ ተከፍታ።

ሁለት መቶ ሃምሳ ተከታዮቻቸው፣

ከነቆሬ ጋራ ምድር ተጫናቸው።

 

የእግዚአብሔርን ምሥጢር ክህነትን የናቀ፣

አሥራ አራት ሺህ ሕዝብ በመቅሰፍት አለቀ።

የተፈቀደለት አሮን ቢይዝ ጥና፣

መቅሰፍቱ ቀጥ አለ ክህነት አለውና።

አስቀድሞ እግዚአብሔር ትዕዛዝን አዝዞታል፣

እንደዚህ በማለት ለአሮን ተናግሮታል፦

 

አንተና ልጆችህ ወደ መቅደስ ግቡ፣

ከመሠዊያው ስፍራ ሌሎቹ እንዳይቀርቡ።

ክህነት የሌለው ሰው ክህነት ያልተሰጠው፣

በቤተ መቅደሴ አይገባም ክልክል ነው።

ሥርዓት ነውና ጠብቀው ብያለሁ፣

ስለዚህም አሮን አንተን መርጫለሁ።

 

ቃሉ አይታጠፍም ዛሬም ይናገራል፣

የቀባኋቸውን አትዳስሷቸው ይላል።

ከእኛ ይጠበቃል ቸል አትበሉ ሰዎች፣

ካህናትን ማክበር የእግዚአብሔርን ዓይኖች።

 

ጽኑ ቃል ኪዳን ነው ሊከበር ይገባል፣

ካህኑ ለእግዚአብሔር ጸሎት ያሳርጋል።

ከሁሉ እበልጣለሁ ንጉሥ ነኝ በማለት፣

ሳኦል ክህነት ቢያምረው ሳይፈቀድለት፣

እንኳን ያልተሰጠው  የተመኘው  ክህነት፣

ንግሥናው ቀረበት የተፈቀደለት።

 

ንጉሥ ዖዝያንም ቤተ መቅደስ ገብቶ፣

መሠዊያው ላይ ቢያጥን እጆቹን አንሥቶ፣

ወዲያው ከመቅጽበት ፊቱ ላይ ለምጽ ወጣ፣

እንደ ሮጠ ገብቶ እንደ ሮጠ ወጣ።

 

እንዲህ እናምናለን የክህነትን ነገር፣

አምላክን ማክበር ነው ካህናትን ማከበር።

ታላቅ ሰው አብርሃም በዚያ ሁሉ ክብሩ፣

በመልከ ጼዴቅ ፊት ገሐድ ታየ ግብሩ።

 

በታላቅ መባረክ ግድ በመሆኑ፣

አብርሃም ሰገደ ለሊቀ ካህኑ።

አሥራትን አውጥቶ ለታላቁ ካህን፣

አብርሃም ተሰጠው ኅብስትና ወይን።

 

የክህነቱ ምሥጢር አብሮ በመምጣቱ፣

ለአዲስ ኪዳን ቁርባን ቅዱስ መሥዋዕቱ፣

ለድኅነት ቀረበ ለሰው ልጅ አለኝታ።

ኅብስትና ወይኑ ተባርኮ በጌታ።

 

ዛሬም እንደ ትናንት እንደ ሐዋርያቱ፣

አምላክ የቀባቸው ክቡር ካህናቱ፣

የሕይወትን ኅብስት የሕይወትን ጽዋ፣

በቅዳሴው ጸሎት መሥዋዕቱ ሲሠዋ፣

ለሕዝብ ይሰጣሉ የጌታን ሥጋ ደም፣

ፈቃድ ስላላቸው ከአምላክ መድኃኔዓለም።

ምን ዓይነት አምላክ ነው በምን ቃል ይደነቅ፣

ይኽ ምሥጢር ታላቅ ነው ከሁሉም የሚረቅ።

 

ሥጋውን የበላ ደሙን የጠጣ ሰው፣

በሕይወት ይኖራል መንግሥቱን ወራሽ ነው።

ስለዚህም ደግሞ የእግዚአብሔር ካህናት፣

ተፈቅዶላቸዋል ይኽንን ለመሥራት።

እንድንበት ዘንድ ቁርባን የምንቆርበው፣

በዕደ ካህናት የተዘጋጀው ነው።

 

ዓለምን ያዳነ ማንም ሳያግዘው፣

ምድረ ቀራንዮ ደሙን ያፈሰሰው፣

ለእኛ ሲገልጽልን የምሥጢሩን ብዛት፣

መድኃኒት ላከልን በዕደ ካህናት።

 

ለተልዕኮ ምሥጢር የሚፋጠኑትን፣

የእግዚአብሔርን ምርጦች ክቡር ዲያቆናትን፣

በእስጢፋኖስ እግር ገብተው ለተተኩት፣

ምስጋና ይገባል ዘወትር ለሚተጉት።

ቀድሰው አቁራቢ ሲደርስ ጊዜያቸው፣

የዛሬ ዲያቆናት ነገ ካህናት ናቸው።

 

አምላክ አታሳጣን እንዲህ ያለውን ክብር፣

ካህናት ዲያቆናት ይብዙልን በምድር።

ከርሞም እንደ ዛሬ ምእመናን ይሰጠን፣

አሜን ብሎ ማደር የካህን ቃል ሰምተን።

 

አምላክ ለዚህ ክብር መርጦ ለለያቸው፣

መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ላሰለጠናቸው፣

ምስጋና ለማቅረብ ዛሬም እንቆማለን፣

ክብር ለሚገባው ክብር እንሰጣለን።(፪)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አብርሃም ሰሎሞን

መስከረም ፯/፳፻፱ ዓ.ም.