ቅዱሳን በገድላቸው በሦስት ይከፈላሉ

) በአላውያን ነገሥታት ፊት ሳይፈሩ እስከ ደም ጠብታ ድረስ ስለ ክርስቶስ የመሰከሩ ሰማዕታት ናቸው። ለምሳሌ፦

             ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰማዕቱ ቅዱስ ቂርቆስ ፣ ቅድስት ኢየሉጣ፣ ቅዱስ መርቆርዮስ እና ሌሎችም።

) በገደል፣ በዱር በዋሻ ሆነው ከጣዕመ ዓለም ተለይተው ክርስቶስ ለሞተለት ለዚህ ዓለም ሲጸልዩ ግርማ ሌሊቱን ድምፀ አራዊቱን ጸብአ አጋንንቱን ታግሠው የሚኖሩ ጻድቃን ናቸው። ለምሳሌ፦

ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት፣ ቅድስት አርሴማ፣ ጻድቁ አቡነ አረጋዊ  እና ሌሎችም።

ሐ፦ መጽሐፍ አውጥተው፤ አንቀጽ ጠቅሰው፤ መናፍቃንን ተከራክረው፤ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ያስከበሩ የቤተ ክርስቲያን ጠበቆች አፖሎጂስቶች/ ተብለው የሚጠሩ ናቸው። ለምሳሌ፦

ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፣ ቅዱስ ቄርሎስ፣ ቅዱስ ባስልዮስ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ።

እነዚህ ከላይ በግብራቸው የገለጽናቸው ቅዱሳን አክባሪያቸው ባለቤቱ እራሱ አምላክ ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ቃሉ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል። በማለት የገለጸው (፩ቆሮ. ፰፡፲፫) ምክንያቱም የቅድስና ሰጪው እርሱ ነውና:: ከነቢያትም ነቢዩ ኢሳይያስ በምዕራፍ ፶፰፡፲፫ “እግዚአብሔር የቀደሰውን ክቡር ብትለው" በማለት የምናገኘውን በረከት ይገልጻል። በነገረ ቅዱሳን ትምህርታችን ዘወትር ሰዎች ሊያስተውሉት የሚገባ ነገር ቢኖር ለቅዱሳን ክብር የሰጠ እግዚአብሔር ዘወትር የማይጠፋ ስም በቤቱና በቅጥሩ ውስጥ እንዲህ ሲል መስጠቱን ነው፦ ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለመረጡ ጃንደረቦች ዘወትር የማይጠፋ ከወንዶችና ሴቶች ልጆች ይልቅ የበለጠ ስም በቤቴና በቅጥሬ ዉስጥ እሰጣቸዋለሁ። ብሎ ቃል ገብቶላቸዋል። (ኢሳ. ፶፮፡፬)

 

የቅዱሳን አማላጅነት

ምልጃ በቁሙ ስንፈታው “መለመን፤ ስለሌላው መጸለይ” የሚል ፍቺ ይሰጠናል። አማላጅነት ስንል ደግሞ አድራጊው ያለውን የባለቤትነት ሥልጣን ወይም ችሎታ የተሰጠውን የሚያሳይ ነው። ቅዱሳን የአማላጅነት ጸጋ ተሰጥቷቸዋል፤ ለማማለድም ሥልጣን አላቸው። አማላጅነታቸው ከሰው ወይም ከባለሥልጣን የተሰጠ ሳይሆን ከኃያሉ እግዚአብሔር ነው። ቅዱሳን የተሰጣቸው የማማለድና የመለመን ጸጋ በማንም አለማመን ምክንያት አይነጠቅባቸውም፤ የምልጃ ሥራቸውም የሚቀር አይደለም። ፈርዖን እግዚአብሔርን ሥራውን በሙሴ አማካኝነት በማድረጉ አልተቀበለውም። ምክንያቱም ፈርዖን አለማመኑ ብቻ ሳይሆን እንደርሱ  በፈርዖን ቤት ያደገውና የሚያውቀው ሙሴ ከእርሱ ጋር ልዑል ተብሎ በፈርዖን ቤት ሲጠራ ማየት በእርሱ አመለካከት ውስጥ “ከኔ በምን ይለያል፣ እኔ የማመልከውን ጣዖት አብሮ ሲያመልክ የነበረ ዛሬ እግዚአብሔር የሚለኝ እርሱ ማነው? ባንተ እጅ የምትደረገዋ ተአምር አታስደንቀኝም ምክንያቱም እጅህ ብዙ የፈርዖን ቤት ጥበብና የምትሐት ሥራ ያውቃል” ብሎ ስለናቀው እግዚአብሔር ተአምራቱን ከእርሱ ጋር ባላደገውና በአይሁዳዊው ዮካብድ ቤት ባደገው አሮን በበትሩ እንዲሠራ አድርጎታል። ሙሴን ፈርዖን መስማት ያቃተው “እንደኔው ነው” በማለትና በማቃለል ነበር። ሆኖም ግን እግዚአብሔርን ባያምን  የእግዚአብሔር ሥራ አልተቋረጠም። ዛሬም የማያምኑ እንደኛው ሰው ናቸው በማለት ለሰውነት የተሰጠውን ክብርና እግዚአብሔር በጸጋ በበረከት ታላላቅ ያደረጋቸውን ቅዱሳን አማላጅነት የማይቀበሉ ቢኖሩም አምኖ አማላጅነታቸውን ለጠየቀ ግን የአማላጅነታቸው በረከት ይደርሰዋል፤ ጸጋውም ይበዛለታል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በሁለተኛው የቆሮንቶስ መልእክቱ በእኛ የማስታረቅ ቃል አኖረ። (፪ቆሮ. ፭፡፳) ይለናል። "ወንህነሰ ንተነብል በአምሳለ ክርስቶስ ወይሁበክሙ እግዚአብሔር ፍሥሐ በላዕሌነ" ይኽም በክርስቶስ ማላጅ አደረገን፤ እንማልዳችኋለን በማለት ገልጾታል። በእንግሊዝኛውም God were pleading through us, we implore you on Christ's behalf, be reconciled to God. እነዚህ ሁሉ የምናያቸው መረጃዎች እራሱ ክርስቶስ የማስታረቅንና የማማለድን ሥልጣን ለቅዱሳን መስጠቱን የሚገልጽ ነው።

 

የቅዱሳን ጸሎት እጅግ ኃይል እንደምታደርግም "ብዙኅ ትረድእ ለጻድቅ ትክል ወታሰልጥ" የጻድቅ ሰው ጸሎትዋ በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። (ያዕ. ፭፡፲፮) በማለት ቅዱስ ያዕቆብ የገለጸው በጸሎት ያለው ዋጋና በረከት የበዛ መሆኑን ለማመልከት ነው። ማንም ከሚጸልየው ጸሎት ይልቅ የጻድቁ ልመና በባለሟልነቱ ኃይል አላትና። ልመናን ማንም ሊለምን እንዲችል የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ነገር ግን ግዳጅ ያላት ግዳጅዋን የምትፈጽም ጸሎት ከእኛ ካለው ንጽሕና ጋርና ለእግዚአብሔር ካለን ቅርበት የሚከናወን ነው። ግብራችን እግዚአብሔርን የማይመስል ሆኖ በሥጋዊ ስሜትና ፍላጎት ታጥረን ሌትና ቀኑን ነፍሳችንን ስለ ሥጋዋ እንጂ አምላክዋን ስለማሰብ እድል ካልሰጠናት ጸሎታችን ለመሰማት ኃይል አይኖራትም። እራሳችንንና ጸጋችንን ማስተዋል ይገባል፤ ደፋር እንዳንሆንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

 

በነቢዩ በኢሳይያስ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም፤ በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፥ ልባቸውን አደንድን፥ ጆሮአቸውንም አደንቍር፥ ዓይናቸውንም ጨፍን። (ኢሳ. ፮፡፱-፲) እንደተባለ ዛሬም በብዙዎች ሕይወት ባለማስተዋላቸው ምክንያት እግዚአብሔር ያከበራቸውን ክቡር ብሎ ጠርቶ እግዚአብሔርን ለማመስገን ተቸግረዋል። ቅዱስ ዳዊት ከድፍረት ኃጢአት ጠብቀኝ ያለውን እውነት እናስተውላለን።

 

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተመዘገበው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብቻ በአማላጅነት አሥራ አምስት ሰዎች ተመዝግበዋል። ከዚህ በታች ያሉትን ጥቅሶች በማንበብ ቅዱሳን በመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸውን ድርሻና ተሰሚነት ልብ እንበል።

ማቴ. ፪፡፳ ማቴ.፯፡፳፭ ማቴ. ፰፡፭  

ማቴ. ፰፡፳፪  ማቴ. ፱፡፪ ማቴ. ፱፡፲፰

ማቴ. ፲፭፡፳፪ ማቴ. ፲፯፡፲፬ ማር. ፱፡፲፯

ሉቃ. ፭፡፲፰ ሉቃ. ፯፡፪ ሉቃ. ፱፡፴፭

ዮሐ. ፬፡፵፮ ሐዋ. ፲፩፡፫ ሐዋ. ፱፡፴፮

ቅዱሳን በሕይወተ ሥጋም ሆነ ከሞቱ በኋላ ያማልዳሉ።

 

መጋቤ ሃይማኖት ቀሲስ አሐዱ አስረስ