(ክፍል 1)

ይህን ቃል የጻፈልን ቅዱስ ሉቃስ ሲሆን ተናጋሪው ደግሞ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ነው።

የበራክዩ ልጅ ከሆነው ከካህኑ ዘካርያስና ከእናቱ ከቅድስት ኤልሳቤጥ የተገኘው ዮሐንስ መጥምቅ ካህኑ ዘካርያስ በእርጅና ሳለ፤ ቅድስት ኤላሳቤጥ ልምላሜ ጠፍቶባት በእርጅና ሳለች በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት እግዚአብሔርን በማምለክና በመፍራት ይኖሩ የነበሩ ካህኑ ዘካርያስ እና ኤልሳቤጥ እግዚአብሔርን እያገለገሉ ለዘመናት በኖሩበት መቅደስ የመልአኩን ብሥራት ካህኑ ዘካርያስ ሰማ "ልጅ ትወልዳለህ" የሚለውን የምሥራች ዜና።

      "ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ፃድቃን ነበሩ" /ሉቃ፣ ፩፥፱/

ዮሐንስ ማለት ፍስሐ ወሐሴት ማለት ነው "በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል" ሉቃ፣ ፩፥፲፬

ዮሐንስ መጥምቅ ክርስቶስን በ6 ወር በመወለድ ይቀድመዋል "እነሆ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እርሷ ደግሞ በእርጅናዋ ወንድ ልጅ ፀንሳለች ለእርሷም መካን ትባል ለነበረችው ይህ ስድስተኛ ወር ነው" ሉቃ፣ ፩፥፴፮  የጌታችንን መወለድ ንጉሡ ሄሮድስ በሰማበት ሰአት ክርስቶስን አገኛለሁ ብሎ ንጉሡ ከሁለት ዓመት በታች የሆኑትን ህፃናት አርዶ ደማቸው እንደ ውሃ በፈሰሰ ጊዜ /የህፃናቱ ብዛት 14እልፍ ከአራት ሺህ ናቸው/ የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥም ልጇን ይዛ በበረሃ ተሰዳ ነበረ እርሷም መስከረም ፯ ቀን በበረሃ አርፋለች። አባቱ ካህኑ ዘካርያስንም በቤተ መቅደስ ሄሮድስ ሰውቶታል። ዮሐንስም ለእስራኤል እስከሚገለጥ ድረስ ኑሮውን በብሕትውና፣ በትህርምት፣ በበረሃ በማድረግ ኖሯል። ጊዜው በደረሰ ጊዜ ግን ባማረና በተዋበ አለባበስ ሳይሆን የግመል ፀጉር ለብሶ፣ ወገቡን በጠፍር ታጥቆ፣ አንበጣና፣ የበረሃ ማር እየበላ በዮርዳኖስ ወንዝ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ ብርታትና ተግሳፅ በሞላበት አንደበት ማስተማር ጀመረ። ዮሐንስ ከልቡ አመንጭቶ የሚናገርበት ድፍረትና ጥብዓት ያገኘው በኖረው ፍፁም ብሕትውና እና የቅድስና  ኑሮ ነው "የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ በምድረ በዳ መጣ"  ሉቃ፣ ፫፥፭ እንዳለ፦

ዮሐንስ ነቢይም፣ ካህንም፣ አጥማቂም፣ መምህርም፣ ጻድቅም፣ ሰማዕትም፣ ሐዋርያም ተብሎ ይጠራል።

 የጌታን መንገድ ለማዘጋጀት የዮሐንስ ትምህርቶች፣

  ፩/ ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት

  "መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ" ማቴ፣ ፫፥ ፩–፪

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የትምህርቱ መጀመሪያ፣ የመንገድ ጥርጊያው መጀመሪያ፣ ወደ እግዚአብሔር መመለሻው ንስሐ መጀመሪያው

ስለሆነ ተመለሱ ንስሐ ግቡ እያለ አስተማረ።

ንስሐ ማለት፦ መጸጸት፣ ማዘን፣ ማልቀስ፣ ክፉ ዐመልን መተው፣ መጥፎ ጠባይን መቀየር ማለት ነው። የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ሰፊውን ስፍራ የንስሐ ጥሪን መልእክት ይዞ እናገኛለን። በተለይ የነቢያት ጩኸት ወደ እግዚአብሔር ሕዝቡ እንዲመለስ፣ ከጣዖት አምልኮ እንዲርቅ፣ከዝሙት እንዲርቅ፣ ከሟርተኝነት እንዲርቅ፣ የሚያደርግ ድምጽ ነበር። እግዚአብሔርም ሰዎች ሲመለሱ የሚኖራቸው የሕይወት ለውጥ እንዲህ ብሎላቸዋል፦ "ኃጢአተኛውም ከሰራው ኃጢአት ሲመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል አስቦ ከሰራው በደል ሁሉ ተመልሶአልና ፈጽሞ በህይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም" ት/ሕዝ፣ ፲፰፥ ፳፯–፳፱

ቅዱስ ዮሐንስም ተመለሱና ንስሐ ግቡ የእግዚአብሔር መብግሥት ቀርባለችና እያለ ህዝቡን አስተምሯል። " ያን ጊዜም ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር" ማቴ፣ ፫፥ ፭–፮ እንዳለ።

በዮርዳኖስ ወንዝ የተሰበሰቡት ህዝብ ሁሉ የንስሐን ድምጽ ብቻ በመስማት አልዳኑም "ኃጢአታቸውንም ተናዘዙ" እንዳለ። ዛሬ ብዙዎቻችን የንስሐን ትምህርት የምናውቅ ግን ንስሐ የማንገባ፣ የምናዳምጥና የምንናገር ግን የማንተገብር፣ በከንፈራችን ብቻ የምንጸጸት እንጂ የሕይወት ለውጥ የማናመጣ ሆነናል። ንስሐ ኃጢአተኝነትን ብቻ ማመን አይደለም፣ ንስሐ የንስሐ እውቀትን ብቻ መያዝ አይደለም፣ ንስሐ ወደ እግዚአብሔር ቤት መምጣት ብቻ አይደለም፣ ንስሐ በልዩ ልዩ አገልግሎት ውስጥ መሰማራት ብቻ አይደለም፣ ንስሐ የሌሎችን ኃጢአት እያዩ የራስን አቅልሎ ማየት አይደለም፣ ንስሐ ኃጢአትንና የኃጢአትን ሰንኮፍ ነቅሎ ጥሎ ለአዲስ ሕይወት መኖር እንጂ፣ ንስሐ የእግዚአብሔርን የምሕረት አይን የምናይበት ልዩ መነጽራችን፣ የእግዚአብሔርን ይቅርታ የምናገኝበት ልዩ መንገዳችን፣ የእግዚአብሔርን ርኅራኄ የምናገኝበት ታላቁ ቀቁልፋችን ነው።

ለዚህ ነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ያለው፤ ስለዚህ መልካም ወደ ሆነው ተመልሰን፣ የበደልን መልሰን፣ የተጣላን ታርቀን መኖር ያስፈልገናል።

የእውነት ሐዋርያ፣ የእውነት መስካሪና፣ ለእውነት የቆመ፣ ለእውነት የሄደ፣ መናኙ ካህን፣ የሰባኪው የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን።                                                                                

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር!                                                                                                                  

መ/አ/ቀሲስ ስንታየሁ ደምስ

(- - - ይቀጥላል)

በኦርየንታል ኦርቶዶሳዊያን አብያተ ክርቲያናት ዘንድ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ልዩ የክብር ሥፍራ የሚሰጣት በነገረ ድኅነት ውስጥ ታላቅ የሆነ ድርሻ ስላላት ነው። ስለሆነም የክርስትና ሕይወት በምልጃ አገልግሎት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ኦርቶዶክሳዊያን ምእመናንም እመቤታችን ባሕረምህረት ወደብረ ትዕግሥት ከሆነው አምላክ የተሰጣትን የምሕረት ቃል ኪዳን ፍጹም በማመን በጸሎቷና በምልጃዋ ዘወትር ይማጸናሉ። በዚህም መሠረት እናቱ ድንግል ማርያምን በዚህ ቃልኪዳን ያከበረው አምላክ ከመረጥኋዋቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፤ “... ኪዳኔን አላረክስም፤ ከከንፈሬም የወጣውን አልለውጥም “(መዝ.፹፰፡፴፩-፴፬) ሲል ይጎበኘናል፤ በቸርነቱና በረድኤቱም ይጠብቀናል።

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ሦስት ዓመት ከቤተሰቧ ጋር፤ አሥራ-ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ፤ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት ጌታን ጸንሳ፤ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታችን ጋራ፤ አሥራ አምስት ዓመት በወንጌላዊው በዮሓንስ ቤት ከኖረች በኋላ በስድሳ አራት ዓመቷ ጥር ሃያ አንድ ቀን አርፋለች። ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሣኤ በቅዱስ መጽሓፍ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም” በማለት በምሥጢር ይገልጸዋል። መዝ.፻፴፩፡፰

ነቢዩ ዳዊት ይህን ቃለ ትንቢት የተናገረው ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው። ይህም እመቤታችን እንደ ልጇ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው። ታቦት ያላት ማደሪያው ስለሆነች ነው። የወላዲተ አምላክ ዜና እረፍቷን እና ትንሣኤዋን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እንደሚተረከው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት በሆነበት ዕለት፤ ሐዋርያት የእመቤታችንን አስከሬን ለማሳረፍ ወደ ጌቴ ሴማኒ መካነ ዕረፍት  (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዐት መንፈስ ተነሣስተው “ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ በአርባኛውም ቀን ወደ ሰማይ አረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል” እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል። አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፤ ዐረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን? “ኑ! ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት” ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፍንያ የተባለ ጎበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን አስከሬን የተሸከሙበትን አልጋ ሸንኮር ያዘ። የአልጋውን ሸንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጆቹን ስለቆረጣቸው ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ። ነገር ግን ታውፍንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡዕ ተአምር የተቆረጡ እጆቹን እንደቀድሞው አድርጋ ፈውሳዋለች።

በዚያ ጊዜም መልአክ እግዚአብሔር የእመቤታችንን አስከሬን ከሓዋርያው ዮሓንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችን አስከሬን በገነት መኖሩን ነገራቸው። ሐዋርያትም የእመቤታችንን አስከሬን አግኝተው ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት የተነሳ በነሐሴ ፩ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በአሥራ አራተኛው ቀን (በሁለተኛው ሱባኤ መጨረሻ፟) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ አስከሬን አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፤ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት። የእመቤታችን የቀብር ሥነሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል። በዚያ ጊዜም ትንሣኤዋን ሌሎች ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “ፈቀዳ ይደቅ እምደመናሁ” ይለዋል። ማለትም በፊት የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ከማዘኑ የተነሳ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው። በዚህ ጊዜ እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሓዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አፅናናችው። ሄዶም ለወንድሞቹ ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራችው አዝዛው ለምልክት ምስክር ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ፈጽማ ወደ ሰማይ ዐርጋለች።

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወዳሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ “እመቤታችንን እኮ ቀበርናት።” ብለው ነገሩት። እርሱም አውቆ ምሥጢሩን ደብቆ “አይደረግም! ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?” አላቸው። “አንተ እንጂ፤ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ። አሁንም አታምንምን?” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው ሲያሳዩት መቃብር ቢከፍቱ የእመቤታችንን አስከሬን አጡት። ደነገጡም፤ በዚህ ጊዜም ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች” ብሎ የሆነውን ሁሉ ከተረከላቸው በኋላ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው። እነሱም ሰበኗን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል።

በዓመቱ ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቅርብን ብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ሱባኤ ገቡ። በሱባኤው መጨረሻም በነሐሴ በአስራ ስድስተኛው ቀን (ነሐሴ ፲፮) ቀን) ጌታችን የለመኑትን ልመና ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፤ ቅዱስ እስጢፋኖስን፤ ገባሬ-ሠናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን ዕርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሐዋርያዊቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም ትጾማለች።

በጽኑ ለሚፈልጉት ሁሉ የሚሰጠውን ለሚገባቸውም ተትረፍርፎ የሚገኘውን የእግዚአብሔር ጸጋ በረከትን ለማግኘት፤ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕረፍት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ደቂቅየ ልጆቼ” ይላቸው በነበሩት ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፤ ሴቶችና ወንዶች አረጋዊያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል።

በዚህ የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት መታሰቢያ (በጾመ ፍልሰታ) ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው፤ በመቃብር ቤት ዘግተው፤ አልጋና ምንጣፍ ትተው፤ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግኝ ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ።

በአጠቃላይ በሰሙነ ፍልሰታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለው ሁኔታና ሕዝቡ ደግሞ ልጅ አዋቂ ሳይል የሚያሳየው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያረጋግጥ ነው።

ከብርሃነ ትንሣኤዋ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር  ወለመስቀሉ ክቡር ወለወላዲቱ ድንግል

ከቤዛ ኩሉ ሰ/ት/ቤት ትምህርት ክፍል

በአቶ አበጀ ሐደሮ