፩) መቋሚያን ለመጀመርያ ጊዜ ለመዝሙር የዜማ መሣሪያነት ያዋለ ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ያሬድ ነበር

፪) መቋሚያ የያዕቆብ በትር ምሳሌ ነው፤ ያዕቆብ የመስቀል ምልክት ያለበትን በትሩን ከፊቱ አቁሞ ይሰግድ፥ይጸልይ ነበር (ዕብ፡፲፩፥፳፩)።

በትረ ያዕቆብም፥መቋሚያም የመስቀል ምሳሌዎች ናቸው። ጌታችን መስቀሉን በትከሻው እንደተሸከመ፥ መቋሚያውን በትከሻችን ተሸክመን እንዘምራለን። መቋሚያውን የምንደገፈው፥ መስቀል ኃይላችን መሆኑን ለመግለጥ ነው።

፫) የመቋሚያ ሥርዓተ ማሕሌት አጠቃቀም ምሳሌያዊ ትርጉም

ሀ)  በሥርዓተ ማሕሌት ጊዜ መዘምራን መቋሚያን በመጀመሪያ ከላይ ወደታች ያደርጉታል። ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስማየ ስማያት መውረዱን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ መወለዱን ያመለክታል። ከዚያም መቋሚያውን ከግራ ወደ ቀኝ ከቀኝ ወደ ግራ የሚያደርጉት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐና ቀያፋ ከጲላጦስ ወደ ሮድስ መመላለሱን መከራ መቀበሉን ለማስብ ነው። መቋሚያን ከግራ ወደ ቀኝ ሲያሽከረክሩትም ዓለምን ዞሮ ማስተማሩን ለማጠየቅ ነው።

ለ) መዘምራን መቋምያን መሬት ላይ የሚደስቁት የማይሞት ጌታ ወደ መቃብር ወረደ ለማለት ሲሆን ወደ መሬት የደሰቁትን መልሰው ወደ ላይ ማንሣታቸው ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን ለመመስከር ነው።

ሐ) መዘምራን ከቀድሞ በበለጠ መቋምያን ከፍ አድርገው ኋላ ረጋ ብለው የሚመልሱት ዕርገቱን እና ዳግም ምጻቱን ለማዘከር ነውሞቶ የተነ ተነቶም ያረገው ዳግመኛ ይመጣ ሲሉ ነው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣

ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

በዶ/ ሰሎሞን ፎሌ