ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ። (፩ጴጥ. ፪፡፳፬)

 

የበዓላት አከባበር ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። በዓላት የሰው ልጆች እግዚአብሔርን የሚያከብሩበት አንደኛው መገለጫቸው ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ከማመስገን የተቆጠበችበት ጊዜ ባይኖርም በበዓላት ግን በበለጠው ስያሜው በተሰየመላቸው ቅዱሳን አማካኝነት የእግዚአብሔር ሥራው ይነገርበታል። በርካታ በዓላት በቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንደሚከበረው እኛም በደብራችን ቅድስት ሥላሴን መድኃኔዓለምን፣ ቅዱስ ሚካኤልንና ቅዱስ ዮሐንስን እናከብራለን።

 

 

በመሆኑም የዛሬ ወር በደብራችን የጥቅምት መድኃኔዓለም ንግሥ ስለሚኖር ምእመናን ከወዲሁ ጊዜያችሁን አመቻችታችሁ የበዓሉ ተሳታፊ እንድትሆኑ ከወዲሁ እናስታውቃችኋለን።

 

ቅዳሜ በዋዜማው ሰዓት እና እሑድ በንግሡ ሰዓት ተገኝተን ዓለምን በክቡር ደሙ ያዳነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሕሌት፣ በቅዳሴና በዝማሬ እናመስግነው። የጊዜ ባለቤት ሁላችንንም በሰላም በጤና ጠብቆ የቀጠሮ ሰው ይለን ዘንድ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን።

 

 

 

 ከበዓሉ በረከት ተሳታፊ ያደርገን ዘንድ ልዑል እግዚአብሔር በጤና ይጠብቀን፤

 

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት አይለየን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር  ወለመስቀሉ ክብር ወለወላዲቱ ድንግል

 

ወ/ት ዘመናይ ዘሪሁን

 

 

 

 

 

ቅዳሴ፣ ማሕሌት፣ ኪዳን፣ ምህላ እና ንግሥ

* ዓመቱን በሙሉ ኪዳን ይደርሳል (6:00 A.M)

* ዘወትር እሑድ ቅዳሴ ይቀደሳል

* በሥላሴ፣ በመድኃኔዓለም፣ በማርያም፣ በሚካኤል እና በዮሐንስ ወርኃዊ በዓላት ይቀደሳል (የክርስትና ማንሳት አገልግሎት ይሰጣል)

* ጥርና ሐምሌ ሥላሴ፣ ጥቅምት እና መጋቢት መድኃኔዓለም፣

      ኅዳር እና ሰኔ ሚካኤል፣ ሰኔና መስከረም ዮሐንስ ይነግሣል

* በጾመ ፍልሰታ የሱባኤ ወቅት ሰዓታት ይቆማል፣ ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም ይተረጎማል፣ ቅዳሴ እና የሰርክ ጸሎት ይደርሳል

* በአዲስ ዓመት (በዘመን መለወጫ)፣ በልደት  በትንሣኤ እና ቤተ ክርስቲያናችን ባሏት ተጨማሪ ዐበይት በዓላት የተለያዩ መርሐ-ግብሮች ይከናወናሉ።

* በሰሞነ ሕማማት ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሙሉ አገልግሎት ይሰጣል

ክርስትና

* ቤተ ክርስቲያናችን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጀምሮ በርካታ ሕፃናት የጥምቀተ ክርስትና አገልግሎት አግኝተዋል።

ስብከተ ወንጌል እና መንፈሳዊ ትምህርት

* ዘወትር አርብ ስብከተ ወንጌል ይሰጣል

* ዘወትር ቅዳሜ መላ ምእመናንን የሚያሳትፍ የሰንበት ትምህርት ቤት መርሐ-ግብር ይደረጋል

* ዘወትር ቅዳሜ የአብነት ትምህርት እና መሠረታዊ የአማርኛ ቋንቋ ለወጣቶችና ለታዳጊ ሕፃናት ይሰጣል

* ዘወትር እሑድ ሃይማኖታዊና የሥነ-ምግባር ትምህርት ለሕፃናት እና ለወጣቶች ይሰጣል

ዕድር

* የቤተ ክርስቲያናችን አባላት የሆኑ ብቻ በአባልነት ተመዝግበው በኀዘናቸው ጊዜ መርጃ እንዲሆናቸው ታስቦ የተቋቋመው ዕድር ለአባላት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።