በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

እስመ ንጉሥ እግዚአብሔር ለኩሉ ምድር፤ ዘምሩ ልብወ ነግሠ እግዚአብሔር ላዕለ ኩሉ አሕዛብ።... እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና፤ በማስተዋል ዘምሩ። እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ ነገሠ፤... (መዝ ፵፮፥፯-፰)

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ከዘመናት በፊት ምሥጢረ ሥጋዌ በገሐድ ተገልጾለት መጪውንና አላፊውን ዘመን በምሥጢር እያስማማ በመዝሙሩ ያስተምረናል። «እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ነግሦልና በማስተዋል ዘምሩ።» ማለቱም የቅዱስ መጽሐፍን ምሥጢራት በማስተዋል ተገንዝባችሁ አንድነቱን ሦስትነቱን ተረድታችሁ በሥጋ ማርያም የተገለጠው የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በማመን ዘላለማዊነቱን እየመሰከራችሁ ዝማሬአችሁን አቅርቡ ሲል ነው። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል «በያዕቆብ ቤት ለዘላለም ይነግሣል» ብሎ መናገሩ ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ ንጉሥ የሆነ እርሱ እግዚአብሔር የጠፋውን ሊፈልግና ዓለምን ሊያድን «የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤» ገላትያ ፬፥፬ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ዘላለማዊ ንጉሥ መባሉን ሲያስረዳ ነው። ዘላለማዊ ንግሥና ለእግዚአብሔር ገንዘቡ መሆኑን በማስተዋል ዘምሩ ሲል እውነቱን ጠንቅቃችሁ በመረዳት አመስግኑ ማለቱ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም መወለዱን መልአኩ ለእረኞች ነገራቸው ይለንና ዝማሬ ሲያቀርቡ ግን ብዙ የሰማይ ሠራዊት መሆናቸውን ይጠቅሳል። ይኽም ማለት እግዚአብሔርን ለማመስገን የሕብረት ዝማሬ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታል። በሕብረት መዘመር ከመላእክት የተገኘ ምሥጢር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕረ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ በታላቅ ትሕትና መቆሙን ተመልክተን እኛም እርስ በእርሳችን በመከባበር በታላቅ ትሕትና በቤቱ መቆም ይገባናል። ልደቱም ጥምቀቱም ከማዳን ምሥጢሩ ባሻገር ትሕትናን ያስተምረናልና። ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ እኛን ሊፈልግ የመጣውን ጌታችንን እያመለክን እንድንኖር ያስፈልጋል። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ጌታን ያጠምቅ ዘንድ በፈቃደ እግዚአብሔር ተችሎታልና ስለ ጌታችን ጥምቀት ስናስተምር ጻድቅም፣ ካህንም፣ ነቢይም፣ ሰማዕትም ስለሆነው ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ልንናገር ግድ ይለናል። በመልክአ ዮሐንስ ላይም እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦  

ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽእቁ፤

እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤

ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ። ትርጓሜውም፦

ዮሐንስ ሆይ ለአንተ የተሰጠው ክብር ትልቅ ነው። ራጉኤል በትጉህነቱ ኢዮብ በጽድቁ ጥረት ቢያደርጉም እንደ አንተ ነበልባለ እሳትን ማጥመቅ አልተቻላቸውም ማለት ነው። እንግዲህ ለእያንዳንዱ የተሰጠ ጸጋ የተለያየ ነውና ቅን ሥራ በመሥራት እግዚአብሔርን ማገልገል ይኖርብናል። የአጥማቂው የቅዱስ ዮሐንስ በረከት፣ አምላክን በድንግልና የወለደች የእመቤታችን ምልጃ፣ ምስጋና የባሕሪው የሆነ የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ከእናንተ ጋር ይሁን። በዓሉን የሐሴት የፍሥሐ ያድርግልን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

  ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ (ሊቀ ጳጳስ)