በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር እምሰማያት (በሰማየ ሰማያት ለዘላለም ፀንቶ የሚኖረውን አመስግኑት።)

ሰብሕዎ ለብሉየ መዋዕል (ዘመናትን የሚያስረጀውን ዘመናት የማያስረጁትን እግዚአብሔርን አመስግኑት)

 

ፍጥረታቱ ሁሉ ይሴብሕዎ በአርያም በጽርሐ አርያም በውዳሴው በግናያቱ በልዕልናው በሕያውነቱ ስቡሕ ወውዱስ ተብሎ በአፈ መላእክት ወሰብእ የሚመሰገነውን እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል።  በእግዚአብሔር በውዳሴው አመስጥሮ ሰሌዳ አጠገብ ጽርሐ አርያምንና ዘመናትን ካነሣን ዘንድ ጽርሐ አርያም የምትለውን በማስታወስ ንጉሠ ሰላም መኮንነ ዘመናት ኢየሱስ ክርስቶስ በርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የምትገኙትን ካህናትና ዲያቆናት ምእመናንንና ምእመናትን መዘምራንንና መዘምራትን እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገራችሁ እላችኋለሁ። የጽርሐ አርያም ምሑራን ልጆቿ፣ የሃይማኖት ጠባቂዎቿ፣ የቀኖና አክባሪዎቿ ካህናት ወምእመናን ከርእሰ መዝሙራት ሊቀ ሊቃናት ቅዱስ ያሬድ ድጓ አብነት በመውሰድ በመጠኑ ላመሰግናችሁ ወደድሁ። ቅዱሱ በመንፈሰ ጸጋ ተመስጦ በመሄድ የናግራንን ቤተ ክርስቲያንና ምእመናኖቿን እንዲህ ሲል አወደሳቸው፦

ኦ ሀገረ ናግራን ቤተ ክርስቲያን ጽፍቅት ከመ ሮማን ምዕዝት ከመ ዕጣን ካህናትኪ ነባብያን፣ ወዲያቆናትኪ ልዑካን፣ ምእመናንኪ ለባውያን ወደቂቅኪ ምሑራን (የናግራን ቤተ ክርስቲያን የምእመናኖችሽ ብዛት እንደ ሮማን ጽፍቀት ነው። ሥነ ምግባራቸው እንደ እጣን መዓዛ የተወደደ ነው። ካህናቶችሽ ነባብያን የወንጌል አስተማሪዎች ናቸው። ዲያቆናቶችሽ የሐዲስ ኪዳን ልዑካን ናቸው። ምእመናኖችሽና ወጣቶች ልጆችሽ አስተዋይና ምሑሮች ናቸው።) እንዳለ እናንተም የጽርሐ አርያም ልጆች ካህናቶቻችሁ ነባብያን የወንጌል አስተማሪዎች፣ ዲያቆናቶቻችሁ የሐዲስ ኪዳን ልዑካን፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቻችሁና መላው ምእመናን ደግም አስተዋይና ምሑሮች ናችሁ።

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ግብረ ሌሊት በተባለው መጽሐፋቸው "ቤተ ክርስቲያን እሰ ትትሜሰል በጽርሐ አርያም ዘላዕሉ።" (ቤተ ክርስቲያን በሰማይ ባለው ጽርሐ አርያም ትመሰላለች) በማለት እንዳስተማሩን እናንተም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ጽርሐ አርያም በተሰኘች ቤተ ክርስቲያናችሁ ውስጥ በቅድስና እና በንጽሕና እግዚአብሔርን እያመለካችሁ መኖራችሁ በየዕለቱ ከምታደርጉት እንቅስቃሴ ለማወቅ ተችሏል። አሁንም ቅድሚያ ለቅድስት ሃይማኖታችሁ በመስጠት ካህናቱና ዲያቆናቱ፣ ሰንበት ት/ቤቱና ወጣቶቹ፣ መላው ምእመናንንና ምእመናቱ እንዲሁም የነገዪቱ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ታዳጊዎቹና ሕፃናቱ በአንድ መንፈስ አብራችሁ እንድትጓዙ በማለት አሳስባችኋለሁ።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለክርስትና ሃይማኖት ተገቢ የሆነውን መልእክት ባስተላለፈበት ምእራፉ የተናገረውን ኃይለ ቃል መመሪያችሁ አድርጋችሁ በዚህ በአዲስ ዓመት ተግባራዊ እንድታደርጉት እጠይቃችኋለሁ፦ ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ሮሜ. ፲፪፡፱-፲፯

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ የሰሜን ምሥራቅ፣ የደቡብ ምሥራቅና የመካከለኛው አሜሪካ

የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ