ዐብይ ፆም በመባል ስያሜ ወጥቶለት የሚታወቀው ይኽ ፆም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ደንግጋ ከምትፆማቸው አፅዋማት መካከል ለ፶፭ ቀናት ያህል የሚፆም ነው። ይኽንን ፆም ልዩ የሚያደርገው የቁጥሩ ብዛት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ይልቅ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ይበልጣል ብለው አበው እንደተናገሩት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ያዳነን ወልደ አብ ወልደ ማርያም አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለፆመው ነው። 

 

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፬፡፩-፲፬ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት እንደ ጦመ በዚያም በዲያብሎስ እንደተፈተነና ዲያብሎስን ድል እንዳደረገው ተዘግቦ ማንበባችን ፆም ዲያብሎስን ድል መንሻ መሆኑን እንድናረጋግጥበት ያደርገናል። የመጀመርያው ሰው አዳም በሰይጣን ዲያብሎስ ተፈትኖ የወደቀበትን ፈተና መፆም የማይገባው ጌታችን ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ፆሞ ሰይጣንን ድል የነሳበት በመሆኑ እኛም የተለያየ ፈተናን በፆም አሸንፈን በረከት የምናገኝበት ፆም እንዲሆን በየዓመቱ እንጾመዋለን።

 

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ መልእክት ላይ «የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና» የተሰኘውን አምላካዊ ቃል (ሉቃ. ፲፱፡፲) አስፍሮልን ስንመለከት አምላካችን ወድ ምድር መምጣቱ የሰውን ልጅ ከውድቀቱ ሊያነሣው መሆኑን ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ሳያስፈልግ በቀላሉ ለመረዳት ያስችለናል። ዲያብሎስም በበኩሉ ባለው የማጥመጃ መሣሪያና የማሰሪያ ሰንሰለት ተጠቅሞ የሰውን ልጅ ከአምላክ አለያይቶ፣ ከተድላው አርቆ፣ ከገነት አውጥቶ፣ የመንግሥተ ሰማያትን መንገድ አዘግቶ እና ዘላለማዊ ሕይወትን አሳጥቶ መኖርን ስለሚፈልገው በተቻለው ሁሉ ይህንን ግብሩን ሲያደላድል ይኖራል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወት እንድንደርስ ሳያሸልብ እንደሚጠብቀን ሁሉ ከሳሽ ዲያብሎስም ሳያሸልብ መውደቂያችንን ሲያመቻች ይኖራል። 

/፩ኛ ሳምንት ዘወረደ/

በዚህ ዕለት ነቢያት የሰበኩት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ስለ መውረዱና የማዳን ሥራው ስለመጀመሩ ይሰበካል። ቅዱስ ዮሐንስ በአንደኛ መልዕክቱ ምዕራፍ ፫፡፰ ላይ «የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ» እንዳለው ጠፍቶ የነበረውን ሰው ወደ ቀደመ ክብሩ በእንዴት ያለ ሁኔታ እንደተመለሰ በሰፊው ይነገራል። አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና» (ሉቃ. ፲፱፡፲) በማለት የተናገረው ቃል በትምህርትና በዝማሬ ይነሣል። የሰው ልጆችም ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም በትኅትናና በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር እንደሚገባን ከቅዱስ ዳዊት ቃል የመዝሙሩ ምስባክ ይደመጣል። እግዚአብሔር በፍርሓት እንድንገዛለትና እንድናከብረው ይሻልና የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛን በማስተዋል መኖር እንደሚገባን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ «ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ? (ሚልክያስ ፩፥፮) ብሎ እንዳስተማረን

በዚህ በመጀመርያው ሳምንት ከመዝሙረ ዳዊት ላይ የሚሰበከው ምስባክ፦

ጸሎት፤ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት፣ ምህረት እና ቸርነቱን የሚለምንበት፣ የሚማለድበት እና የሚማፀንበት እንዲሁም እግዚአብሔር የሰውን ልመና ተቀብሎ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ረቂቅ ምስጢር ነው። የጸሎት መሠረቱ “ዕሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁን ምቱ ይከፈትላችኋል” (ማቴ. ፯፡፯) የሚለው የጌታችን ትምህርት ነው።

በቤተ ክርስቲያናችን ከሚጸለዩ ጸሎቶች የሚዘወተረው አጭር ጸሎት “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ፤ አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ማረን” የሚለው ሲሆን ካህኑ ሲናዝዙ አሥራ ሁለት ጊዜ “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ካዘዙ በኋላ “በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ፤ አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ማረን” በሉ ይሉናል፡፡ አባቶች እንደሚያስተምሩን ይህ ጸሎት ፍጹም ኃይል ያለዉና ከጽድቅ ጎዳና ሊያወጡን የሚራወጡ አጋንንትን የምንመክትበት ጋሻችን ነዉ።  ስንጸልይም በዘልማድ የሚሆን ማነብነብ ሳይሆን ሕዋሳትን በመሰብሰብ በሰቂለ ሕሊና በነቂሐ ልቡና መሆን አለበት፡፡ ልባችን ከአፋችን: አፋችን ከልባችን አንድ ሳይሆን፥ ከመንፈስ የተራቆተ ስሜት የማይሰጥ ትርጉም የለሽ ዝብዘባ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡