Print

ዐብይ ፆም በመባል ስያሜ ወጥቶለት የሚታወቀው ይኽ ፆም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ደንግጋ ከምትፆማቸው አፅዋማት መካከል ለ፶፭ ቀናት ያህል የሚፆም ነው። ይኽንን ፆም ልዩ የሚያደርገው የቁጥሩ ብዛት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ይልቅ ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ይበልጣል ብለው አበው እንደተናገሩት በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ያዳነን ወልደ አብ ወልደ ማርያም አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለፆመው ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፬፡፩-፲፬ አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ከተጠመቀ በኋላ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት እንደ ጦመ በዚያም በዲያብሎስ እንደተፈተነና ዲያብሎስን ድል እንዳደረገው ተዘግቦ ማንበባችን ፆም ዲያብሎስን ድል መንሻ መሆኑን እንድናረጋግጥበት ያደርገናል። የመጀመርያው ሰው አዳም በሰይጣን ዲያብሎስ ተፈትኖ የወደቀበትን ፈተና መፆም የማይገባው ጌታችን ለእኛ አርአያና ምሳሌ ለመሆን በገዳመ ቆሮንቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ፆሞ ሰይጣንን ድል የነሳበት በመሆኑ እኛም የተለያየ ፈተናን በፆም አሸንፈን በረከት የምናገኝበት ፆም እንዲሆን በየዓመቱ እንጾመዋለን።

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ መልእክት ላይ «የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና» የተሰኘውን አምላካዊ ቃል (ሉቃ. ፲፱፡፲) አስፍሮልን ስንመለከት አምላካችን ወድ ምድር መምጣቱ የሰውን ልጅ ከውድቀቱ ሊያነሣው መሆኑን ሌላ ተጨማሪ ማስረጃ ሳያስፈልግ በቀላሉ ለመረዳት ያስችለናል። ዲያብሎስም በበኩሉ ባለው የማጥመጃ መሣሪያና የማሰሪያ ሰንሰለት ተጠቅሞ የሰውን ልጅ ከአምላክ አለያይቶ፣ ከተድላው አርቆ፣ ከገነት አውጥቶ፣ የመንግሥተ ሰማያትን መንገድ አዘግቶ እና ዘላለማዊ ሕይወትን አሳጥቶ መኖርን ስለሚፈልገው በተቻለው ሁሉ ይህንን ግብሩን ሲያደላድል ይኖራል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሕይወት እንድንደርስ ሳያሸልብ እንደሚጠብቀን ሁሉ ከሳሽ ዲያብሎስም ሳያሸልብ መውደቂያችንን ሲያመቻች ይኖራል። 

ፆም ማለት ሥጋንና ነፍስን ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ማስገዛት በመሆኑ ፆምን በፆምን ቁጥር  ከእግዚአብሔር በረከትን እናገኛለን፤ ከሰይጣን ምክርና እስራት ነፃ እንወጣለን። የዲያብሎስ ሥራው  በ፵ ቀንና በ፵ ሌሊት ፆም ሲፈራርስ አይተናልና። አዳምን በመብል ያሳተ የቀደመው እባብ ሰይጣን ዲያብሎስ ዳግም በመብል ፈትኖ ገነት እንደተዘጋች እንድትኖር ቢያልምም ኅልሙ እውን፣ ሙከራው አዎንታዊ፣ ጥረቱ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። እንግዲህ በእንዲህ ያለ ሁኔታ የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በፆም ድል ማድረግን ለእኛ ካስተማረን እኛም በዚህ በዐብይ ፆም የለመንነውና የጠየቅነው ነገር ሁሉ ከኃጢአት በስተቀር እንዲከናወንልን ፆምን ገንዘባችን እናድርግ።

በዐብይ ፆም ውስጥ ያሉት ስምንት ሳምንታት ዘወረደ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መፃጉዕ፣ ደብረዘይት፣ ገብርኄር፣ ኒቆዲሞስና ሆሣዕና የሚል የየራሳቸው ስያሜ ያላቸው ሲሆን በተከታዩ ገጽ የሦስቱን ሳምንታት ስያሜ እና ትምህርት በአጭሩ እናቀርባለን። 

 

በአቶ አብርሃም ሰሎሞን