ቅዱስ ቁርባን ከመቀበል አስቀድሞ ከቅዱስ ምሥጢር የሚቀበሉ ሁሉ እንዲህ ይበሉ፤

አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ርኵስት ከሆነች ከቤቴ ጠፈር በታች ትገባ ዘንድ የሚገባኝ አይደለም።

እኔ አሳዝኜሃለሁና  በፊትህም ክፉ ሥራ ሠርቻለሁና በአርኣያህና በአምሳልህ የፈጠርኸው ሥጋዬንና ነፍሴን ትእዛዝህን በማፍረስ አሳድፌአለሁና ሥራም ምንም ምን የለኝምና። ነገር ግን ስለ መፍጠርህና እኔን ለማዳን ሰው ስለ መሆንህ፣ ስለ ክቡር መስቀልህም፣ ማሕየዊት ስለ ምትሆን ስለ ሞትህ፣ በሦስተኛው ቀን ስለ መነሣትህም ጌታዬ ሆይ ከበደልና ከመርገም ሁሉ፣ ከኃጢአትና ከርኵሰትም ሁሉ ታነጻኝ ዘንድ እለምንሃለሁ እማልድሃለሁም።

የቅድስናህንም ምሥጢር በተቀበልኩ ጊዜ ለወቀሳ ለመፈራረጃ አይሁንብኝ ማረኝ ይቅርም በለኝ እንጂ።

 

የዓለም ሕይወት ሆይ! በእርሱ የኃጢአቴን ሥርየት የነፍሴንም ሕይወት ስጠኝ እንጂ። በሁለት ወገን ድንግል በምትሆን    በወለደችህ በእመቤታችን በቅድስት ማርያም፣ በመጥምቁ በዮሐንስም አማላጅነት፣ ክቡራን በሚሆኑ በመላእክትም፣ በሰማዕታትና፣ ለበጎ ነገር በሚጋደሉ በጻድቃንም ሁሉ ጸሎት እስከ ዘላለሙ ድረስ አሜን።    

 

ቅዱስ ቁርባን ከተቀበሉ በኋላ በአፍ ሳለ ሁሉም እያንዳንዱ እንዲህ ይበል፤

ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሥሉስ ዘኢይትነገር ሀበኒ ከመ እንሣእ ለሕይወት ዘንተ ሥጋ ወደመ ዘእንበለ ኲነኔ ሀበኒ እግበር ፍሬ ዘያሠምረከ ከመ አስተርኢ በስብሐቲከ ወእሕየው ለከ እንዘ እገብር ዘዚአከ ፈቃደ በተአምኖ እጼውዐከ አበ ወእጼውዕ መንግሥተከ ይትቀደስ እግዚኦ ስምከ በላዕሌነ፣ እስመ ኃያል አንተ እኵት ወስቡሕ ወለከ ስብሃት ለዓለመ ዓለም”

ትርጉሙ፦ የማይነገር ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ሦስት የምትሆን ይህን ሥጋና ደም ሕይወት ሊሆነኝ ሳይፈረድብኝ እቀበል ዘንድ ስጠኝ። በጌትነትህ እንድገለጽ ደስ የሚያሰኝህን ፍሬ እሰራ ዘንድ ስጠኝ የአንተንም ፈቃድ እየሰራሁ እኖርልህ ዘንድ ስጠኝ። በማመን አባት ብዬ እጠራሃለሁ መንግሥትህንም እጠራለሁ። አቤቱ ስምህ በእኛ ላይ ይመስገን ምስጉን ክቡር የምትሆን ኃያል አንተ ነህና ለአንተ ክብር ይገባሃል ለዘላለሙ!

                                              

ምንጭ፦ መጽሐፈ ቅዳሴ