ይህን ቃል ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩት ሐዋርያት ተናግረውታል። ጸሐፊው ደግሞ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ነው። በ64 ዓ.ም. አካባቢ እንደጻፈው ይነገራል። መጽሐፉ ሐዋርያት የክርስቶስን ወንጌል ከይሁዳ ወደ ሰማርያ፤ ከሰማርያ ወደ ሶርያ ከዚያም ወደ እስያ ወደ ግሪክና ወደ ሮሜ እንዴት እንዳስፋፉ ያስረዳል። የመጽሐፉ ዓቢይ ነገር የሚያወሳው የሐዋርያትን ሥራ ሲሆን በይበልጥ አጉልቶ የሚናገረው ግን ሐዋርያት በወንጌል ያደረጉትን ተጋድሎና የተጓዙበትን ውጣ ውረድ፣ ለወንጌል የከፈሉትን መሥዋዕትነትና የፈጸሙትን ተአምራት ነው። ከቃሉ መነሻነት እንደምንመለከተው ሦስት ዋና ዋና ነገሮች እናገኛለን፦

፩) ለአባቶች የተሰጠው ተስፋ

አባታችን አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በተስፋ እና በደስታ ይኖር ነበር። ይህ ተስፋው ለዘለቄታ እንዳይቆይለት አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በበላ ሰዓት ተስፋ-ቢስና መንገዱ ሁሉ የጨለማ እና የሁከት ሆኖበታል። ለዚህ ነው  “ራቁታችውን ሆኑ” የሚል የመጽሐፍ ንባብ የምናነበው። አባታችን አዳም ያጣውንና የተሟጠጠበትን የተስፋ ሕይወት  ከገነት ከመውጣቱ በፊት ፈጣሪ እንዲህ ብሎ የተስፋ ስንቅን ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል።.....አንተም አናቱን ትቀጠቅጣለህ (ዘፍ. ፫፡፲፭)።  አባታችን አዳም ራቁቱን በነበረበትና አትብላ የተባለውን ዕፅ በለሰ በልቶ ከፈጣሪው በተጣላበት ሰዓት ይህን ልዩ የሆነ የተስፋ ቃል ከገነት ይዞ ወጥቷል። ስለሆነም ከገነት ወጥቶና ወድቆ እንደማይቀር ያኔ ከገነት ያባረረው ሰይጣን አናቱን ተመትቶ አዳም ከዘመናት በኋላ  ወደ ገነት እንደሚመለስ የተስፋ ስንቅ ሰንቆ ወጥቷል ።

ይኽ ለአዳም ቃል የተገባለት የተስፋ ስንቅ እውን እንደሚሆን እግዚአብሔር  በብዙ ምሳሌና ትንቢት ሲያሳይና ሲያናግር ቆይቷል።  በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ስለሚሆነው የወደፊት ትንቢት እንደሆነና እንደተደረገ አድርጎ ትንቢት በመናገር የሚታወቀውና ደረቅ አዲስ ኪዳን በመባል የሚታወቀው የኢሳይያስ ትንቢት ዋነኛው ነው። ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች። (ኢሳ. ፯፡፲፬) ይህ የአዳም የተስፋ ቃል ኪዳን በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚፈጸም ሲያስረዳ በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና  እንደሚወለድ ተናግሯል። በመቀጠልም የሚወለደው አምላክ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ እንደሆነ በትንቢቱ ተናግሯል። (ኢሳ. ፱፡፮) እንግዲህ ይህ የሚያሳየን ለአዳም የተሰጠው ብቸኛው ተስፋ የዘላለም አባት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ አዳም ያጣውን የልጅነት ጸጋ በሰላም ሊመልስልት እንደሚመጣ ይኽም የማይጨበጥ የማይሆንና የሚዘገይ ተስፋ ሳይሆን እውነት ያለው መሆኑን ያስረዳል ።

"አበ ብዙኃን" አብርሃም እንደዚህ የሚል የተስፋ ቃል ተነገሮታል፦.

የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ ። ይህቸን  ምድር ለዘርህ እሰጥሃለሁ። (ዘፍ. ፲፪፡፯)  ይኽ ቃል ታላቅ ተስፋው  ከዘሩ ክርስቶስ ተወልዶ የምድርን ነገድ ሁሉ እንዲባረኩ እንደሚያደርግ ነው። በዚህ ደግሞ ከአብርሃም ዘር በሚወለደው በክርስቶስ መሆኑንም ነው።

የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ (ማቴ፩፡፩) እንደተባለ። “እንግዲህ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደሆኑ አወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ “በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንግዲህ እግዚአብሔር የተስፋው ብርሃን በአዳም እና በልጅ ልጆቹ አኑሮ አዳምም በተስፋ ወደወጣበት ገነት እንደሚመለስ ሲጠባበቅ ኖሯል። በዓበይት ነብያትና በደቂቀ ነብያት ሲናገር እና ሲያጽናና ቆይቷል። ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር  በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን ። (ዕብ. ፩፡፩)

፪) የምስራችን እንሰብካለን

ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከና እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። (ገላ. ፬፡፬) ለአበው ተሰጥቶ የነበረው ተስፋ እሙን እንደሆነ የተረጋገጠበት የመጨረሻው መንገድ የምሥራች ተብሏል። ይኽም የሐዲስ ኪዳን ውልና ስምምነት ሊፈጽምለት በመጣው በንግል ማርያም ልጅ ነው። በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ። (ኢሳ.፱፡፩)  የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያውን  የምሥራች በማድመጥ የተመረጠችውና የታደለችው ለድኅነት ምክንያት  የሆነችው  ድንግል ማርያምን  በሚያስደንቅና በሚያስገርም ሁኔታ ብሥራታዊ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል እንዲህ በማለት አበሠራት፦ ጸጋን  የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ከአንቺም የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚብሔር ልጅ ነው። (ሉቃ. ፩፡፳፮-፴፮)  

በቀዳማዊ አዳም የራቀው ሰላምና የአንዣበበው የሞት ጥላ  ጽድቅ ርቆ ኃጢአትና ርኩሰት በዝቶ በፍርሃትና በኀዘን  በሰቆቃው በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ ለአምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን  የተኖረበት ታሪክ ተቀይሮ የደስታ ብሥራት ተሰማ ያ የፍዳ ዘመን ተሽሮ አዲስ ዘመን የምሕረት ዘመን ቀረበ። አዲስ ዜና፣ አዲስ ብሥራት፣ የምሥራች ተሰማ የምሕረት ዓመት ቀረበ ብሎ አበራት። ከዚያም ጌታ የመወለጃው ቀን በደረሰበት ዕለት አሁንም ታላቁን ምሥራች ኖሎት እረኞች አደመጡ። ከብቶቻቸውን እየጠበቁ ባለበት ሰዓት ዛሬ በዳዊት ከተማ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ደስታ ተወልዶላችኋል (ሉቃ. ፪፡፲፩) ተባለ። የሕዝቡ ሁሉ ደስታ በጌታቸን መወለድ ሆነ፤ አረጋዊ ስምኦንም እንዲህ አለ፦ ዓይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና  ባርያህን በሰላም አሰናብተኝ። (ሉቃ. ፪፡ ፳፪-፴፭)

(ይቀጥላል)

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለመስቀሉ ክቡር

መጋቤ አእላፍ ቀሲስ ስንታየሁ ደምስ