«በቃና ዘገሊላ ከብካብ ኮነ፣ ወሰማይኒ ረስዮ ወይነ፤»

(በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር ሰርግ ሆነ፤ ውኃውንም ወደ ወይንነት ለወጠው።) ዮሐ ፪፥፩-፲፩

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገሊላ አውራጃ በዳዊት ከተማ በቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ተወልዶ በሠላሣ ዘመኑ በሠላሣ ዓመተ ምሕረት በፈለገ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ጾመ ጸለየ፤ በጠላት ዲያብሎስ ተፈተነ። ፈተናውን ድል አድርጎ ሱባኤውን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን ከእናቱ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና ከቅዱሳን ሐዋርያቱ ጋር በመሆን በገሊላ አውራጃ በቃና መንደር በሰርግ ቤት ተገኝቶ ቤተ ከብካቡን በትምህርቱ በተአምራቱ ባረከ።