"ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ"   ዮሐ፥ ፩፡፲፬

"የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ"  ገላ፥ ፬፣፬

             ሐዋርያት እንዳስተማሩን በከዊን ሥሙ ቃል የተባለው የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ማርያም ሰው እንደሆነ እናምናለን። ሰው ሆነ ማለትም የሰውን ጠባያት ነፍስን ሥጋን በረቂቅ ባሕርዩ ለበሰ ተዋሐደ ማለት ነው። ዓለም ሳይፈጠር ጥንት ሳይኖረው ከአብ ከአካሉ፣ ባሕርዩ ከባሕርዩ የተገኘ አካላዊ ቃል ዓለም ከተፈጠረ በኋላ ኑሮ ከድንግል ማርያም የተከፈለ /የተገኘ/ ሥጋና ነፍስን ሆነ፤ ከድንግል ማርያም የተከፈለ /የተገኘ/ ሥጋና ነፍስ ዓለም ሳይፈጠር ከአብ የተገኘ አካላዊ ቃል ሆነ። ቃል ሥጋ ሆነ  ዮሐ፥ ፩፡፲፬

   ቃል ሥጋ ሆነ ሲባል መሆን የኹለቱ ነውና ሥጋ ቃልን ሆነ ማለት እንዳለበት ማስተዋል ይገባናል። ቃል የሚባለው መለኮትነቱ ነው፣ ሥጋ የሚባለው ትስብእቱ ነው ትስብእትም ማለት ሰው መሆን ሰውነት ማለት ነው። ምሥጢሩ ሲገለጥ ነፍስና ሥጋ ማለት ነው፤ ቃል ሥጋ ሆነ ማለት በጉልህ ሲነገር ቃል ከሥጋ ጋር ፣ ሥጋ ከቃል ጋር አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሆነ ማለት ነው። ሃይማኖታችንን ተዋሕዶ ማለታችንም ይህን ይዘን ነው።

   ቃል ሥጋ ሆነ ያለው ቃል የሎጥ ሚስት የጨው ድንጋይ ሆነች እንዳለው እና  ውኃ ወይን ሆነ እንዳለው ሁኔታ አይተረጎምም  ዘፍ፥ ፲፱፡፳፮  ዮሐ፡ ፪፡፱  የሎጥ ሚስት ሰው ሳለች ጨውነት አልነበራትም የጨው ድንጋይ ስትሆን ከሰውነት ወደ ጨውነት ተለውጣለች። የቃና ውሃም ከወንዙ ሲቀዱት ወይንነት አልነበረውም ጌታ ወይን ሲያደርገው ከውኃነት ወደ ወይንነት ተለውጧል። አካላዊ ቃል ግን ሥጋ ሆነ ሲባል ከባሕርዩ ማለት ከቃልነቱ፣ ከመለኮትነቱ ሳይለወጥ ነፍስን ሥጋን ተዋሐደ ማለት ነው። መለኮቱ አልተለወጠም እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም!

ሰው ሲሆን ከባሕርዩ አለመለወጡንም የራሱ ትምህርት ያስረዳናል፦ "ማንም ወደ ሰማይ የወጣ የለም ከሰማይ ከወረደው በቀር እርሱም የሰው ልጅ በሰማይ የሚኖር" ዮሐ፥ ፫፡፲፫ "እኔና አብ አንድ ነን" ዮሐ፥ ፲፡፴ "እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ" ብሏልና ዮሐ፥ ፲፬፡፲፩ ቃል ሥጋ ሲሆን ከቃልነቱ፣ ከመለኮትነቱ ተለውጦ ሥጋን ቢሆን ኑሮ በሰማይ መኖር አይቻለውም፣ እርሱም በምድር ሳለ እራሱን በሰማይ የሚኖር ባላለም ነበር። እንደ እውነቱ ግን ቃል ሰው ሲሆን ከመለኮትነቱ አልተለወጠምና በሰውነቱ በምድር ሳለ በመለኮትነቱ በሰማይ ነበር። ስለዚህም በምድር እየታየ በሰማይ የሚኖር አለ። ዳግመኛም ከመለኮትነቱ ተለውጦ ቢሆን ከሴቶች ከአንዲቱ ከማርያም የተወለደ አንድ ሰው ሲሆን ከእግዚአብሔር ከአብ ጋር መተካከልና በአብ እንደ እውነቱ ግን ሰው ሲሆን ከቃልነቱ አልተለወጠምና በመለኮትነቱ ከአብ ጋር ትክክል ነው በቃልነቱም በአብ ባሕርይ አለ ከአብ አይለይም። ስለዚህ አንድ ሰው ሁኖ ሲታይ በሰውነቱ ቃል ሲናገር ሲሰማ ከመለኮትነቱ ስላልተለወጠ እኔና አብ አንድ ነን አለ ሥጋም ቃል ሲሆን ከባሕርዩ አልተለወጠም። ቃልን ሆነ ሲባል ከባሕርዩ ተለወጠ ማለት አይደለም። ከባሕርዩ ሳይለወጥ ቃልን ተዋሐደ ማለት ነው። ከሰውነት ባሕርዩ ቃል ወደ መሆን ተለውጦስ ቢሆን ኑሮ ሲወለድ በእጅ ባልተዳሰሰም ነበር በተወለደበትም ቦታ ተኝቶ በጨርቅ ተጠቅልሎ ባልታየም ነበር። ከዚህም በሌላ ሁኔታ እንደ ወተትና እንደ ውኃ፣ እንደ ውኃና እንደ ማር የተበረዘ (የተቀላቀለ) አይደለም። ባሕርይ እና ባሕርይ ሳይጣፋ(ሳይበረዝ) እንደ ነፍስና እንደ ሥጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ተዋሐደ እንጂ በተዋሕዶም መንታነት (ሁለትነት) የለበትም። በተወለደም ጊዜ በሰውነት ጠባይ ሥርዓት ከልደቱ እስከ ሦስት ዓመት የእናቱን ጡት በመጥባት፣ ከሦስት ዓመቱ እስከ ሠላሳ ዓመቱ ድረስ እህል በመብላት በመጠጣት ሰውነቱን አጸና፤ በቁመቱም በየጥቂቱ አደገ። መጽሐፍ ቅዱስ "ኢየሱስም በጥበብና በቁመት ያድግ ነበር"(ሉቃ፥፪፡፶፪)  "በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም፤ ኃጢአትን አልሠራም ሐሰትም በአፉ አልተገኘበትም"  ኢሳ፥ ፴፫፡፱  "ልጅ እንደመሆኑ ለእናቱ ይታዘዝ ነበር" (ሉቃ፥ ፪፡፶፩)

   የአብ ልጅ ፣ የማርያም ልጅ ጌታችን ሰው በሆነ ጊዜ የሰውነትን የጠባዕይ ሥርዓት እንደፈጸመ የመጽሐፍንም ሕግ ፈጽሟል። ሕጉና አፈፃጸሙም እንዲህ ነው፦

፩) ኦሪት በስምንተኛው ቀን ልጆቻችሁን ግዘሩ ትላለች። ዘፍ፥.፲፯፡፲-፲፬ ይህን ሕግ ለመፈጸም ጌታችን በተወለደ በስምንተኛ ቀኑ ተገዝሮአል።  ሉቃ፥ ፪፡፳፩ ነገር ግን ሕጉን ፈጸመ እንጂ የገዛሪ ምላጭ አካሉን አልነካውም፣ ደሙን አላፈሰሰውም። ምላጭ ሳይነካው ደሙ ሳይፈስ በአምላካዊ ሥራ ተገዝሮ ተገኝቷል። 

፪) ኦሪት ለወንድ ልጅ በ፵ ቀኑ፣ ለሴት ልጅ በ፹ ቀኗ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ወስዳችሁ መሥዋዕት ሰዉለት ትላለች፣  ዘሌ፥፲፪፡፮-፯ ይህን ሕግ ለመፈጸም ጌታችን በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ተወስዷል፤ መሥዋዕት ተሰውቶለታል። ሉቃ፥ ፪፡፳፪-፳፬

 ፫) ኦሪት ከእሥራኤል የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ ኢየሩሳሌም እየወጣ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ትላለች። ዘፀ፥፳፫፡፲፩-፲፯ ጌታችንም ይህን ሕግ ለመፈጸም ኢየሩሳሌም እየሄደ በዓል ያከብር ነበር። ሉቃ፡፪፡፵፩

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣

ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

በሊቀ ስዩማን ቀሲስ ዓለማየሁ አሰፋ