በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።አሜን።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያትን ከተለያየ የኑሮ ጠባይና የሥራ መስኮቻቸው ላይ ሲጠራቸውና የተአምራቱ ተቋዳሽ፣ የምሥጢሩ ተካፋይ አድርጎ ሲያከብራቸው ወደፊት ስለሚሸከሙት ታላቅ አደራ እሱ ባወቀ እያዘጋጃቸው ነበረ። የጥሪውን ነገር በዕለተ አርብ በድንግዝግዝ ቢረዱትም ከትንሣኤው በኋላ ግን ከዛ በፊት ያልተረዱትን የአገልግሎት ጥሪ ታላቅነት በግልፅ እያዩት መጡ። ከእግሩ ሥር ተቀምጠው የተማሩትን ትምህርት በሥራ ላይ የሚያውሉበት ዘመን መቅረቡን ተረዱ። ከማረጉም በፊት አፅናኝ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚልክላቸው እና ወላጅ እንደሌላቸው ልጆች እንደማይተዋቸው ቃል ገብቶ ሲለያቸው የዛ ሁሉ ዘመን ዝግጅት እስከሞት ድረስ የሚደርስ ቆራጥነት የሚጠይቅ ኃላፊነት መሆኑን ተረድተውና ከመንፈስቅዱስ አጋዥነት ጋር የሚገጥማቸውን ፈተና እንደሚያልፉት አምነው ነው ሊያገለግሉት የተነሱት። ወደየሀገረ ስብከታቸው ከመሰማራታቸው በፊት ግን በፆም እና በጸሎት ለታመነ አምላክ ራሳቸውን አደራ ሰጡና ይኸው ከምዕተ ዓመታት ብዛት ነዶ የማያልቅ የአገልግሎት ጧፍ ሆነውና ለኩሰው ተጠሩ። በሐዋርያት እግር የተተኩ አባቶቻችንም ፆመ ሐዋርያት ብለን የምንፆመውን ፆም ከአዋጅ አፅዋማት አንዱ አድርገው ልጆቻቸው እንፆመው ዘንድ ሥርዓት ሠሩልን። ፆመ ሐዋርያት ከበዓለ ጰራቅሊጦስ እሑድ ማግስት ጀምሮ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ የተሰዉበትን ዕለት እስከምናከብርበት ሐምሌ ፭ ድረስ የሚፆም ሲሆን ለመፆም ዕድሜያቸው የደረሱ በሙሉ ይፆሙት ዘንድ የታዘዘ ነው። ሐዋርያት ይኼን ዓለም ከመጋፈጣቸው በፊት በፆም እንደተዘጋጁ እኛም ሥራችንን ሁሉ በፆም በፀሎት እንጀምረው ዘንድ ይገባል። ቀሪዎቹን የፆመ ሐዋርያት ሳምንታት በትጋት ሆነን እንድንፈፅም እና ከቅዱሳን ሐዋርያት ረድኤት በረከት እንዲከፍለን የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር። አሜን!

በሰብለወንጌል ደምሴ