“ሰው ማለት ምን ማለት ነው?”

ነሐሴ 26 ቀን 2007ዓ.ም

ሰው ማለት ነፋሳዊነት፣ እሳታዊነት፣ ውኃዊነት፣ መሬታዊነት ባሕርያት ያሉት በነፍስ ተፈጥሮውም ነባቢት ለባዊትና ሕያዊት የሆነች ነፍስ ያለችው ፍጥረት ነው፡፡ እንዲህ ብለን ግን የሰውን ተፈጥሮ ጠቅልለን መናገር አይቻለንም፡፡ ምክንያቱም ሰውን ከሌሎች ፍጥረታት ይልቅ እጅግ ልዩ በሆነ መልኩ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል ተፈጥሮአልና፡፡ ስለዚህም ቅዱሳን አባቶች እንዲህ ብለው ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጓሜ ይሰጡታል፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ዘቄሳርያ €œከትምህርቶች ሁሉ ታላቁ ትምህርት ራሰን ማወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው ራሱን ካወቀ እግዚአብሔርን ያውቀዋል፡፡ እግዚአብሔርን ካወቀ ደግሞ እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡€ ሲል ቅዱስ ይስሐቅም €œአንተ በልብህ ንጹሕ ከሆንህ ሰማይ በውስጥህ ነው፡፡ በውስጥህም መላእክትንና የመላእክትን ጌታ ትመለከታቸዋለህ€ (The Orthodox Church by Timothy Ware) ቅዱስ ይስሐቅ እንዲህ ማለቱ ያለ ምክንያት ሆኖ አይደለም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ቃሉን በተግባር መልሰው ለሚተገብሩ ሰዎች €œየሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ ማደሪያ እናደርጋለን፡፡(ዮሐ.14፡23) የሚለውን ይዞ ነው፡፡ አካላችን በሰማይ የሚኖረው አባታችን ማደሪያ ከሆነ እኛም ሰማይ ሆንን ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በእኛ ሰውነት ውስጥ ካለ ደግሞ ቅዱሳን መላእክትም መገኘታቸው እርግጥ ነው፡፡


ከዚህ ጠንከር ባለ መልኩ ደግሞ የአሌክሳንደሪያው ቅዱስ ቀሌምንጦስ €œወንድምህን አስተውለህ ስትመለከተው እግዚአብሔርን ትመለከተዋለህ€ ይላል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም €œበሰው ላይ በአመፃ የምትነሣሣ ከሆነ በእግዚአብሔር ላይ እንደተነሣሣህ ቁጥር ነው፡፡ ለባልንጀራህ አክብሮትን የቸርከው ከሆነ እነሆ እግዚአብሔርን አከበርኽ፡፡ይላል፡፡


ቅዱስ ሄሬኔዎስ፣ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እንዲሁም ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ በአንድነት ሰው በጸጋ አምላክ ይሆን ዘንድ ከሦስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ€ ብለው ያስተምራሉ፡፡ (The Image and likeness of God by Vladimir Lossky) በእርግጥ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት በሁለተኛ ድርሳኑ ገጽ 9 ላይ€œHe suffered Himself of to be called also the Son of David, that He might make thee Son of God. €œአንተን የእግዚአብሔር ልጅ ያደርግህ ዘንድ የዳዊት ልጅ መባልን መረጠ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም €œሙሴ በነዝር እባብ የተነደፉት እስራኤላውያን ከፍ ተብሎ በተሰቀለው የነሐስ እባብ እንደ ተፈወሱ አስተዋለ፡፡ በእርሱም በጥንቱ እባብ የተነደፉትን የሚያድነውን(ክርስቶስን) ከሩቅ ተመለከተው፡፡ ሙሴ እርሱ ብቻ ከእግዚአብሔር የጸጋው ብርሃን ተካፋይ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ በእርሱም እግዚአብሔር ቃል ወደ እዚህ ዓለም በመምጣት አማልክት ዘበጸጋን በትምህርቱ እንደሚያበዛቸው ተመለከተ፡፡ ይላል፡፡


እኚሁ አባቶች ሰው ገና ሲፈጠር በጸጋ አምላክ እንዲሆን ተደርጎ መፈጠሩንም ያስረዳሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም ጌታ ሆይ ሠዓሊ ቀለማትን አዋሕዶ ሥዕሉን እንዲሥል አንተም አርአያህንና አምሳልህን እንዲመስሉ ሁለቱን አካላት አዋሕደህ አንድ አካል በማድረግ በራስህ መልክ ፈጠርካቸው፡፡ ወደ ራስህ አርአያ ተመለከትኽ የራስህን አርአያና አምሳል በእጆችህ ሣልኸው፡፡ ጌታ ሆይ እነሆ የሣልኸውን ሥዕል አንተው ሰው በመሆን ገለጥኸልን፡፡ሲል ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ሰው ገና ከአፈጣጠሩ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለመፈጠሩ ሲያስረዳ €œበአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም ቤተክርስቲያን በፈሰሰው ደሙ መሠረታት(በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን አንዲል የሐዋ.20፡28)፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርዓያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡ብሎ ጽፎልን እናገኛለን ፡፡ (Spirituality in Syrian Tradition by Sebastian brock) ስለዚህም ወደ ድምዳሜው ስንመጣ ሰው ማለት በጸጋ አምላክ ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት መሆኑን በእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን አባቶች አስተምህሮ መረዳት እንችላለን፡፡ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጠረም ስንል የጸጋ እውቀት የተሰጠው ክፉውን ከበጎ መለየት የሚችል ፍጡር መሆኑን ያስረዳናል፡፡ ከላይ ከሰጠናቸው ትንታኔዎች ተነሥተን ሰው ለሚለው ስያሜ ትርጉም ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ተፈጠረ ብለን ብቻ የምንቋጨው እንዳልሆነ መረዳት እንችላለን፤ እጅግ ሰፊ ትርጉም ያለውና በውስጡም ታላቅ የሆነ መልእክትን እንደያዘ እንገነዘባለን፡፡ ይህን እጅግ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ትርጉም የያዘው €œሰው€ የሚለው ስያሜ ለመረዳት መልክና ምሳሌ ወይም አርአያና አምሳል የሚሉትን ቃላት አስቀድሞ መረዳት ይገባናል፡፡


መልክ (አርአያ) ማለት ምን ማለት ነው?


መልክ (አርአያ) ማለት ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስል ዘንድ በተፈጥሮ የተሰጡት ባሕርያት ናቸው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ከሰው ፈጽሞ የሚወሰዱ አይደሉም፡፡ ብዙ ቅዱሳን አባቶች መልክ (አርአያ) ለሚለው ቃል ትርጉም ሲሰጡ ሲለያዩ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘፍጥረትን በተረጎመበት ድርሳኑ ላይ መልክ (አርአያ) ማለት ለሰው በተፈጥሮ ፍጥረታትን ለሚገዛበት ባሕርይው የተሰጠው ስያሜ ነው ይላል እርሱ (ሙሴ) በእግዚአብሔር መልክ ሲል በምድር ያሉትን ሁሉ ሰው የሚገዛቸው መሆኑን የሚያመለክተን ነው፡፡ በምድር ላይ ከሰው በላይ የሆነ ፍጥረት የለውም€ ይላል፡፡ እንዲሁም ይህ ቅዱስ ስለ ሰው ተፈጥሮ ሲያስተምር€œ ሰው ከሚታዩት ፍጥረታት በላይ የሆነ ፍጥረት ሲሆን ለዚህ ፍጥረት ሲባል ሁሉም ፍጥረታት ተፈጠሩ€ ይላል፡፡ ያም ማለት ሰማይ፣ ምድር፣ ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት፣ ተሳቢና ተራማጅ እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ ለእርሱ ተፈጠሩ


አንዳንድ ቅዱሳን ሰው በእግዚአብሔር መልክ መፈጠሩን መንፈሳዊ ከሆነው ተፈጥሮው ጋር አገናኝተው ያስተምራሉ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም በእግዚአብሐር መልክ የተፈጠረችው ነፍሳችን ናት ብሎ ሲያስተምር አንተ መንፈሳዊ ተፈጥሮ አለህ፤ ነፍስ የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ናት ይላል፡፡ ሰው በነፍስ ተፈጥሮው ነጻ ፈቃድ፣ ነገሮችን የማገናዘብ ችሎታ እንዲሁም ሓላፊነት የሚሰማው ሆኖ የተፈጠረ ፍጥረት ነው፡፡ በእነዚህ ሰው እግዚአብሔር አምላኩን ይመስላል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ግን ነፍሳችንም ሥጋችንም በእግዚአብሔር አርዓያ እንደተፈጠሩ ግልጽ በሆነ መልኩ ሲያስረዳ €œበአዳምና በሔዋን አስቀድሞ ያሳየን ምሳሌ ይፈጸም ዘንድ የሙሽራው ጎን በጦር ተወጋ፤ ከጎኑም (በፈሰሰው ደሙ) ቤተክርስቲያን ተመሠረተች፤ እግዚአብሔር ይህን ባወቀ አዳምንና ሔዋንን በብቸኛ ልጁ አርአያና አምሳል ፈጠራቸው፡፡ይለናል፡፡


ሰው ሰማያዊት አካል ስላለችው ረቂቁን ዓለም የመረዳት ችሎታ ሲኖረው ምድራዊውም አካል ስላለው ምድራዊውም እውቀት አለው፡፡ ሰውን ከሰማያውያን መላእክትና ከምድራውያን መላእክት ጋር ስናስተያየው ለሁለቱም ዓለማት እንግዳ እንዳልሆነ በሁለቱም ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮአዊ ባሕርይ እንዳለው፣ የሰማያውያንንም የምድራውያንንም እውቀት ገንዘቡ ያደረገ ፍጥረት መሆኑን ስናስተውል በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መፈጠሩን እንገነዘባለን ፡፡


እግዚአብሔር አምላክ የሰማያውያንም የምድራውያንም ፍጥረታት እውቀት ባለቤት ነው፡፡ ሰውም በጸጋ ለሰማያውያን መላእክት ለምድራውያን ፍጥረታት እውቀት ባይተዋር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በላይ በሰማይ በታች በምድር ከሰማይም በላይ ከሰማይም በታች ይኖራል፡፡ ሰው ሙሉ ለሙሉ አይሁን እንጂ በታች በምድር ግዙፋን ፍጥረታትን ሲገዛ በላይ በሰማይ ደግሞ ከሰማያውያን መላእክት ጋር እኩል በምስጋና ይሳተፋል፡፡ ከዚህም ተነሥተን ሰው በሁለት ዓለማት እኩል የመኖር ተፈጥሮ እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡


ቅዱስ ጎርጎርዮስ ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ስንል  በነፍሱም በሥጋውም እንደሆነ ሲያስረዳ እንዲህ ብሎ ጽፎልን እናገኛለን፡፡ €œሰው ምድራዊና መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጥረት ሆኖ በመፈጠሩ ከመላእክት በተለየ በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ተፈጠረ ተባለለት፡፡ ሰው ምድራዊ ተፈጥሮ ባይኖረው ኖሮ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጠረ ባላልነው ነበር፡፡ ስለዚህም ሰው በምድራዊው ተፈጥሮውም የእግዚአብሔርን መልክ ይዟል፡፡€ ብሎ ያስተምራል፡፡


በእርግጥ ይህ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ ፈጥሮአቸዋል፡፡ ወደ መኖርም ባመጣቸው ፍጥረታትም ሌሎችንም ፍጥረታትን ፈጥሮአል፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ የሰው ተፈጥሮ አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ምድርን ፈጠራት፡፡ ከምድርም አፈር ሰውን አበጀው፡፡ ይህ ዓይነት ባሕርይ እንደ እግዚአብሔር አይሁን እንጂ በሰውም ላይ ይታያል፡፡ ሰው ምንም እንኳ ነገሮችን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ እንደ አምላኩ አይፍጠር አንጂ የተፈጠሩ ፍጥረታትን በመጠቀም ምድራዊው አኗኗሩ ቀላልና ምቹ አንዲሆንለት ሲል ከመላእክት በተለየ እጅግ ድንቅና ሊታመኑ የማይችሉ ተግባራትን ሲከውን ይታያል፡፡ በዚህም አምላኩን ይመስላል፡፡


ምሳሌ(አምሳል) ማለት ምን ማለት ነው ?


ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እኛ የሰው ልጆች በእግዚአብሔር መልክ(አርአያ) የመፈጠራችን ዓለማው እግዚአብሔርን እንደ ችሎታችን መጠን እርሱን መስለን እንመላለስ ዘንድ ነው ይላል፡፡ ከዚህ ተነሥተን ምሳሌ (አምሳል) ስንል በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን በተግባር እርሱን የምንመስልበት ሂደት እርሱ ምሳሌ (አምሳል)ይባላል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርይው ፍቅር ነው፣ ትሑትና የዋህ ነው፣ ቅን ፈራጅ ነው፣ ጻድቅ ነው፣ ርኅሩኅ ነው፣ መሐሪ ነው፣ ታጋሽ ነው፡፡ እነዚህ ባሕርያት ሁሉ በእኛ ተፈጥሮ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባሕርያት ወደ ተግባር መልሰን ስንፈጽማቸው እግዚአብሔርን መስለነዋል ወይም የእግዚአብሔር ምሳሌ ወይም አምሳል በእኛ ላይ ተንጸባርቆ ይታያል፡፡


አንዳንዶች €œእግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ፡፡ €(ዘፍ.2፡7) የሚለውን ቃል ይዘው መንፈስ ቅዱስ ወደ ነፍስነት ተቀይሮ ለሰው ልጅ ተሰጠው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ የአሌክሳንደሪያው ቅዱስ ቄርሎስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ላላቸው ወገኖች አንዲህ በማለት ይመልስላቸዋል፡- €œበአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት ሲል መንፈስ ቅዱስ ለሰው ነፍስ ሆነው ብላችሁ ትተረጉማላችሁን? እንዲህ ብሎ ማሰብ በራሱ በደል መሆኑን አትገነዘቡምን? እንዲህ የምትሉ ከሆነ እንግዲህ ነፍስ የማትለወጥ ናት ማለት ነዋ ! ያም ማለት ለለውጥ አትገዛም፡፡ ሁል ጊዜም ባለመለወጥ ትኖራለች ማለታችሁ ነው፡፡ ነገር ግን ነፍስ ለለውጥ የምትገዛ ናት፡፡ ስለዚህም የማይለወጠውን መንፈስ ቅዱስን ወደ ነፍስ ባሕርይ ተለወጠ በማለት ሳታችሁ፡፡ ስለዚህም እኛ እንዲህ ብለን አናስተምርም፡፡ ነገር ግን ከማይለወጠው መንፈስ ቅዱስ ነፍስ ተሰጠች እርሱዋም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ከበረች እንላለን፡፡


ከዚህ የምንረዳው ፍጥረት የሆነች ሕያዊት ነፍስ ከእግዚአብሔር መሰጠቷን ነው፡፡ እቺን ነፍስ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በጸጋው አምላኳዋን እንድትመስል ያግዛታል፡፡ አዳምና ሔዋን በበደላቸው ምክንያት ያጡት የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ነው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን በንፍሃት መንፈስ ቅዱስን በሐዋርያት ላይ እስኪያሳድር ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ (ዮሐ.21፡22)


እኛ የሰው ልጆች የመንፈስ ቅዱስን እገዛ በኃጢአት ምክንያት ከማጣታችን የተነሣ ምንም እግዚአብሔርን በጸጋ የምንመስልበት ተፈጥሮ ቢኖረንም አልተቻለንም ነበር፡፡ ወደዚህ ወደ ቀደመ ክብራችን ለመመለስ ሰው ግዴታ ሊጠመቅና ሰውነቱን የመንፈስ ቅዱስ ቤተመቅደስ ሊያደርገው ይገባል፡፡ እንዲህ ከሆነ በእርሱ ሰውነት ውስጥ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር አምላክን መስሎ የሚኖርበትን ጸጋ ያገኛል፡፡ በእርሱም በተፈጥሮ ያገኘውን እግዚአብሔርን የመምሰል አቅም ተጠቅሞ በጸጋ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ያድጋል፡፡


ስለዚህ አንድ ሰው በትክክለኛው ተፈጥሮ ለመኖር ከፈቀደ የግድ ተጠምቆ ክርስቲያን በመሆን የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ያለበለዚያ ምኞት ቢኖረው እንኳ በትክክለኛው ተፈጥሮ መኖር ይሳነዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሰውነቱ በኩል ሰው እንደሆነ እንዲሁ እኛም ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች በመሆን እርሱን በጸጋ ወደ መምሰል ልንመጣ ይገባናል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ስለዚህ ሲያስረዳ በሥጋዊ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዘፈ አካል አለው አንደማንለው ሁሉ አንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም ይለናል፡፡


ቅዱስ ጳውሎስም በመንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ጽድቅን መፈጸም እንደሚሳነን ሲያስረዳ €œየማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም፡፡ በውስጥ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፤ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል ይልና በቀጣዩ ምዕራፍ ላይ ለዚህ መልስ ሲሰጥ €œእንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና፡፡€ ይላል (ሮሜ 7፡15-25፣8፡1-2)


እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች እዳ አለብን እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም፡፡ እንደ ሥጋ ፈቃድ ብንኖር እንሞት ዘንድ አለን፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብንገድል በሕይወት እንኖራለን፡፡ (ሮሜ.8፡12-17) አሁን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚያግዘንን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን አግኝተናል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው መልካምን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጥረናል፡፡ (ኤፌ.2፡10) ስለዚህ እንፍራ ከአሁን በኋላ ለምንፈጽማቸው ኃጢአቶች ምንም ምክንያት ማቅረብ አንችልም፡፡ ጽድቅን ከማድረግ ብንመለስ ወይም እያወቅን ከመፈጸም ብንለግም ቅጣቱ በእኛ ላይ ይከፋል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በውስጣችን ያደረውን መንፈስ ቅዱስን ሰምተን ለመታዘዝና እርሱን መስለን ለመመላለስ ያብቃን፡፡ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/768-2011-10-31-14-56-03