የአገልጋይ መንፈሳዊ ባሕርያት

የካቲት 27ቀን 2007ዓ.ም.

 

ይህ የትምህርት መርሐ ግብር በማኅበረ ቅዱሳን በአዲስ አበባ ማእከል የአባላት ማስተባበሪያ ዋና ክፍል አዘጋጅነት እየተዘጋጀ በየሳምንቱ የሚቀርብ ትምህርት ነው፡፡ በዚህ ትምህርት መርሐ ግብራችን የአገልጋዮችን በሕብረት የመሆን ጥቅምና የአገልጋይን ባሕርያት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ይሆናል ፡፡

 

ክፍለ ትምህርት አንድ

         

ምዕራፍ አንድ:-  አገልጋዮች በሕብረት ሆነው የማገልገላቸው ዓላማ፡-


1. መንፈሳዊ አንድነትን ለማምጣት፡-

መንፈሳዊ አንድነት የአገልግሎት ዓይነተኛ ባሕርይ ነው፡፡ መድኅን ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ሕዝቡን ካስተማረ በኋላ ለብቻቸው ያገኛቸው ነበር፡፡ የመንግሥትንም ምስጢር ይተረጉምላቸው ነበር፡፡ በሐዋርያት ሥራ1፡14 ላይም ደቀመዛሙርቱ በአንድ ልብና አሳብ ሆነው ይጸልዩ እንደነበር ተጽፏል፡፡ አንድነትን በተመለከተ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ቁልፍ አሳብ የተጠቀለለበት አሳብ ነው፡፡

 

በሐዋርያት ሥራ 2፡1 ላይም ያመኑ ክርስቲያኖች በአለ ሀምሳ በተባለው ቀን በዓሉን ለማክበር የተሰበሰቡት በአንድ አሳብ ልብና መንፈስ እንደነበር ተጽፏል፡፡ የቅደስት ቤተ ክርስቲን አካል እንደመሆናችን በአንድ አሳብ፣ ልብ ፣ አላማ እንድንመላለስ ተጥረተናል በዚሁ በተጠራንበት መንፈስ በአንድ አሳብ እናገለግላለን ፤ በአንድ አሳብ እንሰበሰባለን ፤ በአንድ ሀሳብ እንጾማለን፣ እንጸልያለን አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ በጋራ መከራን እንቀበላለን፤ የተጠራነው ለዚሁ ነውና፡፡

 


2. መንፈሳዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ
የአገልገሎት ጠቃሚው ክፍል ሰው እድገትን እንዲያስመዘግብ መርዳቱ ነው፡፡ የአገልጋዮች በሕብረት መሆን በግልም በጋራም እንዲያድጉ ያስችላል፡፡ በጋራ በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ ሲቻለን በአንድ ልብ በአንድ መንፈስ ማገልገል ያስችለናል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገልግሎት ወሳኝ ነው፡፡

 

ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ አስቀምጦታል እንዲህ በማለት፡- « በአንድ አሳብ ፣ ልብ፣ ፍቅር ደስታየን ፈጽሙልኝ´/ፊል 2፡2-3/ የመንፈሳዊ አገልጋይ ደስታ ፍጹም የሚሆነው በፍቅር በሚደረግ የጋራ አገልግሎት ነው፡፡ ክርስቲያናዊ አገልግሎት የፍቅር አገልግሎት ነውና፡፡ በፍቅር የማይገለጥ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ሊኖር አይችልም፤ ቢኖርም እንኳን ውጤታማነቱና ዘለቄታዊነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡

 


3. መንፈሳዊ ዕውቀት
አገልጋዮች በጋራ የሚሰባሰቡበት ዓላማ መንፈሳዊ ዕውቀታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጨምሩ ዘንድ ነው፡፡ስለ ቤተክርስቲያናቸው ያላቸው መረዳትም ከፍ ይል ዘንድ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይሄንን ነጥብ የሚያብራራ አሳብ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእከቱ /5፤12-14/ ባለው ኃይለ ቃል ውስጥ የተቀመጠ ነው፡፡ ሐዋርያው በዚህ ጊዜ መምህራን መሆን በተገባችሁ ነበር ስለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ማንም እንዲያስተምራችሁ ባለስፈለጋችሁም ነበር፡፡

 

ጠንካራ ምግብን መመገብ ሲገባችሁ ወተትን የምትፈልጉ ሆናችኋል ይላል፡፡ ከወተቱ የሚካፈል ሁሉ ጠንካራ ሰዎች ሊመገቡት ከሚችሉት ምግብ ያልደረሰ ሰው ነው፡፤ በጽድቅ ባለው መንገድም ያደገ አይደለም ፡፡ ገና እንደሕፃን ወተትን የሚፈልግ ነው፡፡

 

4. ችግርን ለመፍታት

ችግሮቻችን በጋራ መወያየት ለመፍትሔወቻቸውም የጋራ አስተሳሰብን እንድንጋራ ያስችለናል፡፡ የጋራ ጸሎት እጅግ ኃይል ያለው ምስጢር ነው፡፡ ሰይጣንም በአገልግሎታችን ጣልቃ እንዳይገባ ማድረግ ያስችላል፡፡

 

ቅዱስ ጳውሎስ ይሄንን ሁኔታ በፊልጵስዩስ መልእክቱ በምዕራፍ/ 4፡6-7/ ባለው ኃይለ ቃል ውስጥ ጠቅልሎ አስቀምጦታል፡፡ በአንዳች ነገር አትጨነቁ በማንኛውም ነገር በጸሎትና በምልጃ በምስጋናም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር አስታውቁ መረዳትን ሁሉ ያለፈ የሰላም አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በመድኃኒታችን ልባችሁንና አሳባችሁን ይጠብቃል ይላል፡፡


የአገልጋይ ባሕርያት

 

1. ፍቅረ እግዚአብሔር

የአገልጋይ እጅግ አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ፍቅረ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርን የምንወደው ከሆነ ፈተናው፣ ችግሩ ፣ ተግዳሮቱ፣ ማስፈራራቱ፣ ራቡ፣ ጥሙ፣ ስደቱ መከራው አይከብደንም፡፡ አገልጋይ ከሚመራቸው ሰዎች በላይ የሆነ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆን ይገባዋል፡፡ ጹሞ ጹሙ የሚል፣ ጸልዮ ስለጸሎት ጠቃሚነት የሚያስረዳ፣ የፍቅር ሰው ሆኖ ፍቅርን የሚሰበክ፣ አትዋሹ ብሎ የማይዋሽ ሰው መሆን አለበት፡፡

 

2. በድርጊት እንጂ በቃል የማይገለጥ
አገልጋይ በአገልግሎቱ አብነት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ተግባርን የሚያስቀድም ነው፡፡በተግባር የሚገለጽ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች ላይ ተግባራዊ ሥራን የመፍጠር ታላቅ ኃይል አለው፡፡ስለዚህ ቃልን እየቀነስን ድርጊትን እያበዛን በሥራና በእምነት የምንገለጥ መሆን ይጠበቅብናል፡፡መድኃኒታችን የአገልጋይን/ደቀመዝሙርን /ዋጋ በተናገረበት አንቀጽ አገልጋይ መክፈል የሚገባውን ዋጋ እንዲህ በማለት ገልጧል፡፡ “ ለሰማይ ወፎች ለምድር ቀበሮዎች መጠጊያ አላቸው፡፡ የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም፡፡ማቴ 8፡20ሐዋርያው ያዕቆብም ሥራ የተለየው እምነት የሞተ ነው፡፡”ያዕ2፡17

3. ትሕትና
ትሕትና የአገልግሎት መሠረት ነው፡፡ሌሎችን አገልግሎቶች የሚያቃና ትሕትና ነው፡፡ የትሕትና መጉደል አገልግሎትን ያጠፋል፡፡ በአገልገሎት ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ይሆናል፡፡ በአገልግሎት ትሑት ለመሆን ማን እንደሆንን፣ ከየት እንደመጣን ወዴትም እንደምንሄድ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡

 

4. ሓላፊነት የሚሰማው
አገልጋይ የበሰለ መሆን አለበት፡፡ሓላፊነት የሚሰማው የተገባም መሆን አለበት፡፡ለአገልግሎቱ ጥብቅ መሆን አለበት፡፡ ታማኝ አገልጋይ በወንጌል በተሠጠው መክሊት ያተረፈ እንደሆነ ተመስክሮለታል፡፡/ማቴ25፡14-30/

 

5. ብስለት
አገልጋይ በመንፈስም በሥነ ልቡናም የበሰለ መሆን አለበት፡፡ በሥራና በድርጊት የተረጋጋ መሆን አለበት፡፡ ችግርን በመንፈሳዊ ጥንካሬ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ በችግር የሚፈታ መሆን የለበትም፡፡ በሥነ ልቡና የተረጋጋ ፣ያመነውን የሚያውቅ፣ የሚሠራውን የሚያውቅ የሚያገለግለውን የሚያውቅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ራሱን የሚገዛ ይህ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነውና ሓላፊነቱን በትክክለኛ መንገድ የሚወጣ ይሆን ዘንድ ብስለት ያስፈልገዋል፡፡

 

6. መታዘዝ

መታዘዝ ልክ እንደትሕትና ሁሉ የአገልግሎት መሠረት ነው፡፡አገልጋይ ሁልጊዜም ታዛዥ መሆን ይጠበቅበታል፡፡መታዘዝና ትሕትና እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው የአንዳቸው መኖር ለሌላቸው አስፈላጊ ነው፡፡ አብረው የሚሄዱ ናቸው፡፡ትሑት አገልጋይ ታዛዥ ነው፡፡ትሕትና ሲጎድለን መታዘዝም ይጎድለናል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ለመታዘዝ ዓብነት የሆኑ ቅዱሳን አሉ፡፡ ለዓብነትም ያህል፡-

 

 አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል፡፡ ልጁም ይስሐቅ አባቱን ታዟል፡፡
 ፊልሞን ቅዱስ ጳውሎስን ታዟል
 መድኃኒታችን የታዘዘው እስከ ሞት ድረስ ነው፡፡

 

7. ራስን መካድ

ራስን መካድ ልብንና ፈቃድን ለልዑል እግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ጌታም «ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ´ /ምሳ 23፡36/ ልባችን በእግዚአብሔርና በዓለማዊ ጉዳዮች መካከል መከፋፈል አይገባውም፡፡አገልጋይ ዓለምንና በዓለም ያለውን ጣጣ መውደድ የለበትም፡፡ ከወደደ የእግዚአብሔር አገልጋይ መሆን አይቻለውም፡፡ ጌታ ለሁለት ጌታ መገዛት የሚቻለው የለም አንዱን ይወድዳል ሌላውንም ይጠላል/ማቴ 6፡24/ ብሏል፡፡

 

8. ታይታን አለመውደድ
በአገልግሎት ውስጥ ለታይታ የሚሆን ቦታ የለም፡፡ አገልጋይ ታይታ የሚወድድ ከሆነ ወደ ውድቀት ያመራል፡፡ አደገኛ በሽታም ነው፡፡ ታይታ ለውጫዊ እንጂ ለውስጣዊ ማንነት አለመጨነቅ ነው፡፡ በውጭ ሲመለከቱን ጻድቅ በውስጥ ግን ግዴለሽ የመሆን ዝንባሌ ነው፡፡

ይቆየን

 

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/---mainmenu-27/1759-2015-03-06-12-01-21