ሰነቦ

ሰነቦ
ነሐሴ 23 ቀን 2006 ዓም ማለዳ 10 ሰዓት ነው ከዕንቅልፌ የነቃሁት፡፡ ዲያቆን  ሙሉቀን ብርሃን ከጎንደር፣ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ ከፍኖተ ሰላም መንገድ ላይ ይጠብቁኛል፡፡ ለመንገዱ የሚሆነውን የቱሪስት መኪና ያዘጋጀልኝ የኦሪጂንስ ኢትዮጵያ አስጎብኝ ድርጅትባለቤት ሳምሶን ተሾመ ነው፡፡ ክብር ይስጥልኝ ብያለሁ፡፡ የምተርክላችሁን ታሪክ ስትጨርሱ ትመርቁታላችሁ ብየ አምናለሁ፡፡ የምጓዘው አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ለማደርገው ጥናት ተጨማሪ መረጃዎችን ፍለጋ ነው፡፡
ሾፌራችን ደምስ ይባላል፡፡ ዝምታና ትኩረት ገንዘቦቹ የሆኑ፣ በሁሉም ነገር ለመንገድ የተዘጋጀ፡፡ ለተራራ ቢሉ ለቁልቁለት፣ ለበረሐ ቢባል ለደጋ የሚሆኑ መሣሪያዎችን ሸክፎ የያዘ ልምድ ያለው ሾፌር ነው፡፡

ሰነቦ
ዓባይ በረሐ መግቢያ ላይ
የምንጓዘው ከምድር ሥር ከሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎቻችን ወደ አንዱ ነው፡፡ በጎጃም በር በኩል ወጥተን ፍቼና ጎሐ ጽዮንን አቋርጠን በክረምት ውበቱ እጥፍ ድርብ ወደሚሆነው ዓባይ በረሐ መንደርደር ቀጥለናል፡፡ ዓባይ በረሐ የሚባል ቦታ መቼም አያልፍለት፡፡ አበሻ ቢሠራው፣ ጣልያን ቢሠራው፣ ጃፓን ቢሠራው መሬቱ እንደሆነ ድንጋይ ላይ እንዳስቀመጡት ሰው ሲንቀሳቀስ ይኖራል፡፡
ሰነቦ
ይንሸራተታል ተጠንቀቁ
ተሻገርንና ደጀንን አለፍናት፡፡ ከደጀን እስከ ደብረ ማርቆስ ያለው መንገድ በመሠራት ላይ ስለሆነ መኪኖቹን ሁሉ ለአካባቢው መንደሮች እጅ ሲያስነሣቸው ይውላል፡፡ አንዳንዱን መንገድ እንኳን መኪና ዝንጀሮም ያለ ስዕለት የሚወጣው አይመስልም፡፡ በግራ በቀኝ ሽው እልም እያሉ የሚከንፉት መኪኖች ሁሉ መዘጋጃ ቤት እንደ ረሳው ጎዳና በተቆፋፈረው መንገድ ላይ ሲደርሱ ለቆጠራ እንደወጣ እሥረኛ ሰልፍ ይይዛሉ፡፡ 
እኛም ስንችል ስንበር፣ ሳንችል ስንሰለፍ ደብረ ማርቆስን አልፈን ወደ ደምበጫ ማቅናቱን ተያያዝነው፡፡ ሙሉቀንና ስምዐ ኮነ ከአዲስ አበባ 360 ኪሎ ሜትር ርቀት ደምበጫ ላይ ነው የሚጠብቁን፡፡ እነርሱን ከምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የቅርሳ ቅርስ ክፍል ኃላፊና ከደጋ ዳሞት ወረዳ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ጋር አሳፍረን የባሕርዳርን መንገድ ትተን ወደ ቀኝ በመታጠፍ የፈረስ ቤትን መንገድ ተያያዝነው፡፡
ሰነቦ
ሰቀላ ማርያም ደን
ከፊት ለፊታችን የሰቀላ ማርያም ደን ጫፍና ጫፉን ገጥሞ በመካከሉ ሲያሳልፈን ሙሽራ ለመቀበል የወጣ የአዲስ አበባ ሚዜ ይመስል ነበር፡፡ በአንጀኒን በኩል አለፍንና ሰነቦ ተራራው ላይ ደረስን፡፡ መቼም የፈረስ ቤት የጠጠር መንገድ ከአንዳንዱ የአዲስ አበባ አስፓልት ይመረጣል፡፡ በስተግራችን ተራራውን ተደግፈን፤ በስተ ቀኛችን በረሐውን እያማተርን መኪናችንን ከአካባቢው ፖሊስ መጠበቂያ ጎን አቆምናት፡፡
ሰነቦ

አሁን ከባዱ መንገድ ሊመጣ ነው፡፡ የምንወርደው ከምድር ሥር ወደ ታች ነው፡፡ በተራራው ወገብ እየታከክን፣ እንደ ዝንጀሮ ተንሸራትተን እንደ ጦጣ እየዘለልን መጓዝ ይጠበቅብናል፡፡ ዕቃዎቻችንን ሁሉ ሸከፍንና የማይቀረውን ቁልቁለት ተያያዝነው፡፡ ለጉልበት ፋታ የማይሰጠው ቁልቁለት መቅኔያችን ያለቀ እስኪመስለን ድረስ ያንተፋትፈናል፡፡ የገበሬዎችን እርሻና መንደር እያቆራረጥን፣ ወንዝና ገደሉን እየተሻገርን የተራራውን ሥር ለማግኘት እንኳትናለን፡፡
ሰነቦ
ውረድ- ወደ ሰነቦ
የተራራውን ወገብ ካለፍን በኋላ ዓለምን ተሰናብተናት ዓለምን ወደረሳና ዓለምም ወደረሳችው ክልል ወረድን፡፡ በጫካ የተሞላ፣ የፏፏቴ ድምጽ ከሩቅ የሚጣራበት፣ ወፎቹ በተሲዓት የሚዘምሩበት፣ የፋርስ ምንጣፍ የተነጠፈበት የሚመስል ሸለቆ ተቀበለን፡፡ እስካሁን ዋሻውን አላገኘነውም፡፡
ወደ ቀኝ ታጥፈን አንዲት ጅረት መሰል ውኃ ከተሻገርን በኋላ የግቢው መግቢያ በር ጋ ደረስን፡፡ ጭንቁ እዚህ ላይ ይጀምራል፡፡ እኔ ለራሴ ቁልቁለቱን ለመውረድ እንደ ቅቤ ቅል ስናጥ ስለቆየሁ ጉልበቴና እግሬ ተለያይተው ለየብቻ የሚሄዱ መምሰል ጀምረዋል፡፡ እዚህ ደግሞ ለከተማ ሰው የከበደ ቀኖና ጠበቀን፡፡ ከገዳሙ ክልል መግቢያ ጀምሮ በባዶ እግር ነው የሚገባው፡፡ ፊት ለፊት የማያቸው ደንጋዮች ሆያ ሆዬ እንደሚሉ ልጆች እጅብ እጅብ ብለው ቆመው፣ እንደ ፋስ መጥረቢያ የተሳሉ ናቸው፡፡ አንድ እግሬን የመግቢያው ርብራብ ላይ አሳርፌ ሁለተኛውን የት ላድርገው፡፡ በግራ በቀኝ የማያቸው ድንጋዮች እንደ ጥሬ ሥጋ ቆራጭ ቢላዋቸውን አሹለው ይጠብቁኛል፡፡ በብኾር ላይ ቆረቆር እንዲሉ ከተራራው ላይ ባለማቋረጥ የሚወርደው ውኃ አካባቢውን ስላራሰው እግሬ በብርዱ ወደ መደንዘዝ ደርሷል፡፡
ሰነቦ

መጨነቄን ያየው የቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪ የሆነው የዐቢ እንደ አቡነ ገሪማ አገልጋይ በግራ ጎኔ በኩል መጥቶ ደገፍ አደረገኝ፡፡ አይቀርምና እግሬን ወደ አንዱ ሹል ባልጩት ሰደድኩት፡፡ የእግሬ ድንዛዜና የባልጩቱ ስለት ተባብረው ዋጋዬን ሰጡኝ፡፡ ድምጽ እንደሰማች ዕንቁራሪት ዘልዬ ወደ ሌላው ድንጋይ ተሻገርኩ፤ እርሱም እንደ ጓደኞቹ በጠረባ አወራረደኝ፡፡ የዐቢ እየደገፈኝ፣ እኔ ጥርሴን ነክሼ እየዘለልኩ የውኃው ድምጽ እንደ ነጎድጓድ ከሚያስገመግምበት ሥፍራ ደረስን፡፡ ሰነቦ ተክለ ሃይማኖት፡፡
ሰነቦ

ጠበሉ ከቤተ ክርስቲያኑ በላይ ካለው ተራራ ላይ ነው የሚወርደው፡፡ በሦስት ቦታ ተጠማቂዎቹ ይገለገላሉ፡፡ ለሴቶች፣ ለወንዶችና ለካህናት የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በሌሎች የመጠመቂያ ቦታዎች ለካህናት የተዘጋጀ የተለየ ቦታ አልገጠመኝም፡፡ በዚህ ሰነቦዎች ይመሰገናሉ፡፡ የቤተ መቅደሱ በር ከተራራው ሥር ይታያል፡፡ ዋሻው ግራና ቀኝ ተገንብቶ በበር ተዘግቷል፡፡ በስተ ግራ በኩል የካህናት መግቢያ ሌላ ሰርጥ አለ፡፡ ዋናው በር ተከፈተልንና ገባን፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ስትገቡ በስተግራ ይገኛል፡፡ መጀመሪያ ቅኔ ማኅሌቱን፣ በእንጨት በተከለለው ሥፍራ ደግሞ መቅደሱን የዋሻው ውስጥ ደግሞ ቅድስቱን ታገኛላችሁ፡፡ 
ሰነቦ
የመቅደሱ ግንብ
ከቤተ ክርስቲያኑ በስተ ቀኝ ማለቂያው የማይታወቅ የዋሻ  ውስጥ መንገድ ይገኛል፡፡ ያውም መንገዱ በውኃ የተሞላ ነው፡፡ አንዳንድ አገልጋዮች የአራት ሰዓት መንገድ ተጉዘው መጨረሻውን ሊያገኙት እንዳልቻሉ ገልጠውልናል፡፡ እንደ አካባቢው ቃላዊ ታሪክ ከሆነ ዋሻው ከደብረ ሊባኖስ ጋር ይገናኛል፡፡ ገዳሙ ‹ሰነቦ ደብረ ሊባኖስ ተክለ ሃይማኖት ገዳም› የተባለውም ለዚህ ነው ይላሉ፡፡
የገዳሙን የምሥረታ ጊዜ በትክክል ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ አገልጋዮቹ ከሚተርኩት ትረካና በትረካቸው ውስጥ ከሚጠሯቸው ሰዎች ስንነሣ ግን ከግራኝ ዘመን ቀደም ብሎ የተተከለ መሆኑን ለመገመት ይቻላል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ የተተከለው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን(1674-1698ዓም) መሆኑን አንዳንድ የገዳሙ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ አድያም ሰገድ ኢያሱ በዚህ ዋሻ ውስጥ አንድ መነኩሴ ጽላት እንደያዙ መስቀል ጨብጠው ዐጽማቸው እንደሚገኝ የሰሙትን ለማረጋገጥ ከጎንደር ተነሥተው መጡ፡፡ ሲመጡም የሰሙት ትክክል መሆኑን አዩ፡፡ ገዳሙን ገድመው፣ ርስት ሰጥተው አከበሩት፡፡ በወቅቱ 500 መነኮሳት ነበሩት(300 ወንዶችና 200 ሴቶች)፡፡
ሰነቦ
ወደ ዋሻው በዐለት ፍላጭ ላይ ጉዞ
አድያም ሰገድ ኢያሱ ያሠሩት የቤተ መቅደሱ ግንብ ፍርስራሹ አሁንም ይታያል፡፡ የመንበሩን ሥዕል ያሠሩት ወ/ሮ መለኮታዊት (ያረፉት በ1618 ዓም ነው) መሆናቸውን የገዳሙ ካህናት ይገልጣሉ፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የገዳሙ ትክል ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቀደም ይላል ማለት ነው፡፡ ወ/ሮ መለኮታዊት የነበሩት በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ በዐፄ ቴዎፍሎስ ዘመን የነበሩትና በ1701 ያረፉት መለኮታዊት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአንዳንዱ የገዳሙ መጻሕፍት ላይ ከዐፄ ፋሲል የተሰጠ መሆኑን ስለሚገልጥ ታሪኩ ከአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን ቀደም ያለ መሆኑን ያሳየናል፡፡
ሰነቦ
የዋሻው ውስጥ መንገድ
ምሽቱን የአካባቢው ሕዝብ ከዝናብና ጭቃ ጋር እየታገለ ለክብረ በዓሉ ሲጎርፍ ነው ያመሸው፡፡ ያች ዋሻ ከአፍ እስከ ገደፏ ሞላች፡፡ ማኅሌቱ ሌሊቱን በሙሉ ከዋሻው ሲሰማ አደረ፡፡ ቅዳሴውን ያስቀደስነው ከታች ካለው ቅዝቃዜና ከጎን ከሚመጣው ብርድ ጋር እየታገልን ነው፡፡ ፈውስ ፍለጋ ከየቦታው የመጡት ሕሙማን እንደ ሰሊሆም መጠመቂያ ማለዳውን ይጠብቃሉ፡፡ ቅዳሴው እንዳለቀ የሚጀመረውን የዋሻ ውስጥ ጥምቀት፡፡
ሰነቦ
የሌሊት ማኅሌት
ቅዳሴው አብቅቶ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ ለደመራ የሚበራውን ችቦ የሚያስንቁ አራት አምስት ችቦዎች በርተው መጡ፡፡ ሕዝቡም ወደ ዋሻው መንገድ ተሰባሰበ፡፡ ከግራ ከቀኝ በአገልጋዮች ተደግፌ ከተሳሉት የዋሻ ውስጥ ድንጋዮች ላይ እግሬን እያሳረፍኩ፣ በብርዱ የደነዘዘውን እግሬንም ትቼው የመጣሁ እስኪመስለኝ እየረሳሁ ከካህናቱ ጋር ወደ ዋሻው ውሳጣዊ ክፍል ገባን፡፡ በዐለቶች ላይ እንደ ጦጣ ተንጠላጥለን የጠበሉ ጫፍ ላይ ደረስን፡፡
ሰነቦ
ይህ አሁን ከፊታችን የሚታየው ጠበሉ ነው፡፡ ተጠማቂው ወገቡን በገመድ ይታሠርና ወደ ጠበሉ ይገባል፡፡ ወገቡን የሚታሠረው የዋሻው ጥልቀት ስለማይታወቅ ነው፡፡ አንድ ሰው አራት ሸንበቆ ተቀጣጥሎ ወለሉን እንዳልደረሰበት ነግረውኛል፡፡ በኋላ እንደገመትነው ጥልቀቱ ከ20 ሜትር በላይ ነው ማለት ነው፡፡ ጥልቀቱ ብቻ ሳይሆን የዋሻው መጨረሻም አይታወቅም፡፡ ቆርጦ ከሄደ መመለሻውን እንጃ፡፡ ‹ተክልየ ነው የሚይዙት›› ብለውኛል፡፡ እውነትም፡፡
ሰነቦ
በጨለማው ውስጥ ወደ ጠበሉ ጉዞ
ካህኑ መስቀል ይዘው እያጠኑ መጡ፡፡ ተጠማቂውም እየጮኸ ወገቡን በገመድ ታሥሮ ቀረበ፡፡ እርሳቸው ወደ ጠበሉ ዳር ገቡና ተጠማቂውን ጠሩት፡፡ ገባ፡፡ ታሪክ ተጀመረ፡፡ መስቀል ከመያዝና ጸሎት ከመድገም በቀር ካህኑ ምንም አላደረጉትም፡፡ እርሱ ግን መናገር ጀመረ፡፡ የተደረገበትን፣ ማን መድኃኒት እንዳደረገበት፣ ለምን እንዳደረገበት፣ ይለፈልፍ ጀመር፡፡ በአራት ጎረምሶች ተይዞ የገባው ጎልማሳ ኅሊናው ተመልሶለት ራሱ ከጠበሉ ወጣ፡፡ እንዲህ እያለ አንድ ሦስት ሰው ተጠመቀ፡፡
ሰነቦ
ካህኑ ወደ ጠበሉ ሲገቡ
ካህኑ በቃ አሉ፡፡ እንደሰማነው በወር አንድ ወይም ሁለት ቀን ወደ ዋሻው ጠበል ይገባል፡፡ እዚያ ገብቶ ሳይድን የሚወጣ የለም፡፡ ሕሙማኑም እነዚያን ሁለትና ሦስት ቀናት በተስፋ ነው የሚጠብቋቸው፡፡
ሰነቦ
በውኃው ላይ ወደ ጠበሉ ጉዞ
ከአንድ ሰዓት በኋላ ከዋሻው ወጣን፡፡ እኔም ከሹሉ ድንጋይ ላይ ዝናብ፣ ብርድና ጭቃ ተጨምረውበት እየዘለልኩና እየተደገፍኩ የገዳሙን ክልል ለቅቀን ወጣን፡፡ ወደ ማረፊያችን ገብተን ምሳ ከበላን በኋላ ከጫማችን ጋር ተገናኘን፡፡ ለካስ ጫማም ይናፍቃል፡፡

image
ተጠማቂው በገመድ ታሥሮ ወደ ጠበሉ ኩሬ ሲገባ
ስንመጣ ቁልቁል ያየነውን አሁን ቀና ብለን ልናየው ነው፡፡ በትናንቱ መንገድ ላይ ዝናብና ጭቃ ተጨምሮበታል፡፡  የጫማዬ መልክና ቁመና ጠፍቶ ከተራራው ጋር እየታገልኩ መውጣት ቀጠልኩ፡፡ አንድ ጎኔን የዐቢ ደግፎኝ በአንድ እጄ መቋሚያ ይዣለሁ፡፡ የተጎረዱ መሬቶችን መዝለል፣ በጭቃው ተንሸራትቶ ወደ ኋላ መመለስ፣ ከፊት ለፊት እንደ ጅብራ የተገተረ ተራራን ማየት እንዴት አድካሚ መሰላችሁ፡፡ 
ሰነቦ
ተራራውን ከታች ወደ ላይ ሲያዩት
ይባስ ብለው ሙሉቀንና ስምዐ ኮነ እየጣሉኝ ወደ ተራራው ጫፍ መድረሳቸውን ሳይ የምደርስ አልመስልህ አለኝ፡፡ የዐቢ እኔን ደግፎ ተራራውን ለመውጣት ይፈጋል፡፡ የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅና የአካባቢው ካህናት ‹በርታ በርታ› ይላሉ፡፡ አሳብ የለሽ ሀብታሙ ደግሞ ከጎኔ ሆኖ ‹ምክርና ቡጢ ለሰጭው ይቀላል› ይላል፡፡ ልቤ እንደ ጾም ፍርፍር ፍርስ ልትል ነው፡፡

ሰነቦ
በተስፋ፣ ከታች ወደ ላይ
ተመስገን የተራራው መጨረሻ ላይ ደረስኩ፡፡ የቀደሙኝን ሁሉ መንገዱ ዳር መኪናው ጋ አገኘኋቸው፡፡ ጫማየን አውልቄ በፌስታል ጠቅልየ መኪናው ላይ ጣልኩት፡፡ ከዚያም ወደ ኋላ ተመልሼ የመጣነውን ተራራ አየሁት፡፡ 
ሰነቦ
ሸለቆው ከሩቁ
ድካሙ ሲቀነስ ውበቱ አሁንም አለ፡፡ ከእኔ እናንተ ትበረታላችሁና ሰነቦን እዩት፡፡ በተለይ ከአኩስምና ላሊበላ በጎንደርና ባሕርዳር በኩል የምትመጡ ተጓዦች ጎራ ብትሉ ቅርብ ነው፡፡ ሌሎቻችሁም ዛሬ ሄዳችሁ ነገ መምጣት ትችላላችሁና ተነሥታችሁ ሂዱ፡፡ ውጣ ውረዱ ራሱ እንዴት ልዩ ትዝታና በረከት መሰላችሁ፡፡ ደኅና እንሰንብት፡፡
ሰነቦ
ተራራው ላይ ደረስን

Read more http://www.danielkibret.com/2014/09/blog-post_62.html