ላስቬጋስ - ጎንደር


ላስቬጋስ - ጎንደር
አሜሪካ ስመጣ ሦስት ቦታ ያለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይማርከኛል፡፡ ላስቬጋስ  ኪዳነ ምሕረትና ቅዱስ ሚካኤል፣ ዴንቨር መድኃኔዓለምና ሚነሶታ ቅድስት ሥላሴ፡፡ ሃይማኖታቸውን የተረዱ፣ ለአገልግሎት የተጉና ምራቃቸውን የዋጡ ክርስቲያኖች ያሉበት ቦታ፡፡ ወደነዚህ ቦታዎች ስመጣ ከማስተምረው የምማረው ይበልጣል፡፡ በአስቸጋሪው የአሜሪካ ኑሮና ፈተና ውስጥ የቤተ ክርስቲያን እምነትን፣ ሥርዓትና ትውፊትን ጠብቆ፣ ጊዜንና ገንዘብን ሠውቶ፣ የቤተ ክርስቲያንንም አንድነት ጠብቆ ለማገልገል የሚደረገው ተጋድሎ እንኳን የኔ ቢጤውን ሊቃውንቱንም የሚያስደምም ነው፡፡ በተለይ የወጣቶቹ አገልግሎት ጎላ ሚካኤል፣ ተምሮ ማስተማር፣ መርካቶ ተክለ ሃይማኖት ወይም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ያላችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡


ላስቬጋስ - ጎንደር
ላለፉት አምስት ሳምንታት ላስቬጋስ ነበርኩ፡፡ ‹‹የኃጢአት ከተማ›› እያሉ አሜሪካኖች የሚጠሯት የቁማር ከተማ ውስጥ፡፡ ከቅዳሜና እሑድ ይልቅ ረቡዕና ኀሙስ የዕረፍት ቀን በሆነባት ከተማ፡፡ ከሚፈቀደው ይልቅ የማይፈቀደውን ኃጢአት መዘርዘር በሚቀልባት ከተማ፡፡ ክረምቱ ሲመጣ ሙቀቷ እንደ ገሃነም በሚያቃጥልባት ከተማ፤ ዙሪያዋን በተራራ ታጥራ መሐሏ እንደ ድስት ጎድጉዶ፣ ቁማር ላይ የተጣደች ድስት በምትመስለው ከተማ፡፡ በታዋቂው የኔቫዳ በረሃ ውስጥ በምትገኘው ከተማ፡፡ ከተመሠረተች 110 ዓመት በሆናት ጎልማሳዋ ከተማ፡፡ የመጀመሪያዋን ባለቁማር ሆቴል (ጎልደን ጌት ሆቴልን) እኤአ በ1906 በተከለች ከተማ፡፡ በዓመት ከ41ሚሊዮን በላይ ጎብኝ በምታስተናግደዋ ጭንቅንቅ ከተማ፡፡ በየዓመቱ ከ22ሺ በላይ ስብሰባና ትርዒት በምታስተናግደው ውክቢያም ከተማ፡፡ 

ላስቬጋስ - ጎንደር

ቅዱስ ጳውሎስና አባ ኤፍሬም አንድ ሆነው ‹ኀጢአት በበዛችበት የእግዚአብሔር ጸጋ ትበዛለች› እንዳሉት ሆነና ብርቱዎቹ ክርስቲያኖች መሬት ገዝተው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ሠርተዋል፡፡ ላስቬጋስ ኪዳነ ምሕረት ወቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፡፡ ያውም ወጭው ሙሉ በሙሉ ከፍለው ያለ ዕዳ፡፡
እዚህ የመጣሁት ለአንድ ወር የሚቆይ ሥልጠና ተዘጋጅቶ ነው፡፡ መታዘዝ ከመሥዋዕትነት ይበልጣል ብዬ እንጂ በቀለጠቺው የላስቬጋስ ከተማ፣ ዕረፍት በሚነሣው የአሜሪካ ሩጫና ጊዜ ጠየቅ በሆነው ልጆችን የማሳደር ኃላፊነት ውስጥ ያንን ያህል ቁጥር ያለው ሰው ሥልጠናውን ይወስዳል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ 
ላስቬጋስ - ጎንደር

ሥልጠናው ሲጀመር ግን የኔን ፍርሃት የሚንድ፣ የላስቬጋሶችን ቆራጥነት የሚያሳይ ነገር መከሰት ጀመረ፡፡ ረቡዕ ከምሽቱ 12 ሰዓት(6 pmበምዕራብ አሜሪካ ሰዓት) እስከ 2 ሰዓት(8 ሰዓት)፣ ኀሙስ ደግሞ ከምሽቱ 11 (5 pm በምዕራብ አሜሪካ ሰዓት) እስከ 1(7pm  በምዕራብ አሜሪካ ሰዓት) ነበር ሥልጠናው የሚሰጠው፡፡ ከእነዚህ ጊዜያት በተጨማሪ ኀሙስ ጠዋትና እሑድ ጠዋት ቅዳሴ አለ፡፡ እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው የልጆች መርሐ ግብር ይካሄዳል፡፡
ሥልጠናው ሦስት ክፍሎች ነበሩት፡፡ ትምህርት፣ የቤት ሥራና አቅርቦት፡፡ ከአንድ ተኩል እስከ ሁለት ሰዓታት የሚፈጅ ትምህርት አለ፡፡ ትምህርቱን መሠረት ያደረገ የቤት ሥራ ይሰጣል፡፡ የቤት ሥራው ቅዱሳት መጻሕፍትን ማገላበጥና አባቶችን መጠየቅን የግድ ይላል፡፡ የተሠራው የቤት ሥራ በቀጣዩ ቀን በድንገት በተመረጡ ሠልጣኞች ለሕዝብ ይቀርባል፡፡ ይሄ ራሱ ጊዜ ጠየቅ ነው፡፡ ከሥራ፣ ከልጆች፣ ከምግብ ማብሰልና ከቤት ጽዳት በሚተርፍ፣ ከዕንቅልፍ በሚቀማ ጊዜ የሚከናወን፡፡  
ላስቬጋስ - ጎንደር

ክርስቲያናዊ ቤተሰብ›፣ ‹የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት›፣ ‹ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን›ና ‹መንፈሳዊ አገልግሎት› የትምህርቶቻችን ርእሶች ነበሩ፡፡ ትምህርቱን ለመከታተል ከአንድ መቶ ሰው በላይ በሰዓቱ ይገኝ ነበር፡፡ ትምህርቱ ከተጀመረ ከ10 ደቂቃ በኋላ በሩ እንደሚዘጋ ሕግ ስለወጣ ሁሉም ተሯሩጦ በሰዓቱ ነበር የሚገኘው፡፡ ከድካምና ከዕንቅልፍ ጋር እየታገሉ መማር፣ ልጆችን ይዞ መጥቶ እየጠበቁ ሥልጠና መከታተል ከባድ ነበር፡፡ ላስ ቬጋሶች ግን በሚደንቅ ጽንዐት ተወጡት፡፡ በችግር ወይም በሥራ ምክንያት የቀሩትም ስልካቸው ከፍተው ባሉበት ይከታተላሉ፡፡ ያለበለዚያም ጓደኞቻቸው ቀድተው ይወስዱላቸዋል፡፡ የቤት ሥራውን ግን ይሠራሉ፡፡
ብዙዎች የማዕድ ቤት ሥራ እንጂ የቤት ሥራ ረስተዋል፡፡ ምንም እንኳን ትምህርቱ ታትሞ ቢሰጥም ማስተዋሻ መያዝ ግን የግድ ነበር፡፡ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አባቶችና እናቶች በትጋት ትምህርቱን ሲከታተሉ፣ የቤት ሥራቸውን ሲሠሩና የቤተ ክርስቲያንን መጻሕፍት አገላብጠው የተሰጣቸውን ሠርተው ሲመጡ እንደማየት በአሜሪካ ምን ተአምር አለ፡፡ 
ላስቬጋስ - ጎንደር

ሥልጠናው የተጠናቀቀው የእመቤታችንን ስደት በማስመልከት በካሊፎርንያ ግዛት ወደሚገኘው የአባ ሙሴ ጸሊምና አባ እንጦንስ የግብጽ ገዳም በተደረገ ጉዞ ነበር፡፡ ከ300 በላይ ምእመናን በ6 አውቶቡሶች ተሣፍረው መንፈሳዊ ውይይት እያደረጉ ነበር የተመሙት፡፡ የግብጹ ገዳም ጉብኝት ቅዳሴ፣ ትምህርትና የአንድነት ምግብ(አጋፔ) የታከሉበት ነበር፡፡ እጅግ አስደናቂው ነገር ደግሞ በዚህ ጉዞ ለመሳተፍ ከ4 ሰዓት በላይ ተጉዘው የሳንድያጎ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምእመናን አብረውን መኖራቸው ነው፡፡ 
ላስቬጋስ - ጎንደር

ኀሙስ ከቅዳሴ በኋላ ትምህርታቸውን በሚገባ ያለ ቀሪ የተከታተሉ፣ የቤት ሥራቸውን የሠሩና ያላረፈዱ ሠልጣኞች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ነበር፡፡ የብዙዎቹ ምእመናን ጥያቄ ወደፊት ሊቃውንቱን ጋብዘን ጠንከርና ጠለቅ ያለው የቤተ ክርስቲያን ወደ መማር መጓዝ አለብን የሚል ነበር፡፡ በቀጣይም ሊቃውንቱ ተገኝተው ትውፊታዊውን ጉባኤ የሚያስተምሩበትን መንገድ ለማዘጋጀት ነው የወሰኑት፡፡ ይበል ነው፡፡ ድካም፣ የቤት ውስጥ ሥራ፣ ልጆችን መከባከብና የዕንቅልፍ እጦት የማይበግራቸው የላስ ቬጋስ ካህናትና ምእመናን ያደርጉታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ብቻ እድሜ ይስጠን፡፡ እድሜ ለሰጠው ላስቬጋስ ጎንደር ትሆናለች፡፡ ‹ለእመ አእመረ ባቲ፣ ጎንደርሰ ዋልድባ ይእቲ› አይደል የሚባለው፡፡

Read more http://www.danielkibret.com/2015/10/blog-post_31.html