ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የግእዝ ጽሑፎች (ግንቦት 2006 ዓም አኩስም ትግራይ)

ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የግእዝ ጽሑፎች (ግንቦት 2006 ዓም አኩስም ትግራይ)
 ክፍል አንድ
1.1 አጠቃላይ የግእዝ ሥነ ጽሑፋዊ ሀብት
የግእዝ ቋንቋ ከሁለት ሺ ዓመታት በላይ ጊዜ ያስቆጠረ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ያለው ቋንቋ ነው፡፡ እስካሁን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የግእዝ ሥነ ጽሑፍ በተጻፉበት ቁስ በሦስት መልኮች ቀርበዋል፡፡ በድንጋይ ላይ፣ በብራና ላይና በወረቀት ላይ፡፡
  1. የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፡- በድንጋይ ላይ የተጻፉት የግእዝ ሥነ ጽሑፎች በአኩስም አካባቢ የተገኙትንና የነገሥታቱን የጦርነት ታሪኮችንና ሌሎች ዘገባዎችን የያዙትን ጽሑፎች ይመለከታል፡፡  የተገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ከአራተኛው መክዘ(ቅልክ) እስከ 8ኛው መክዘ(ድልክ) የሚደርሱ ናቸው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ጥንታዊው የሚባለው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ በመጣራ ኤርትራ በሐውልቲ የተገኘው(5ኛው መክዘ ቅልክ) ጽሑፍ ነው፡፡
‹ዝ ሐውልት ዘአገበረ
አገዘ ለአበዊሁ ወሰ
ሐበ ሙሓዛተ አውዐ
አለፈነ ወጸበለነ›› የሚለው ነው፡፡
እነዚህ የድንጋይ ላይ ጽሑፎች አብዛኞቹ ዘገባዎችና ታሪኮች ሃይማኖታውያን አይደሉም፡፡

  1. የብራና ላይ ጽሑፎች፡- ሁለተኛው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ የብራና ሥነ ጽሑፎች መልክ ነው፡፡ የብራና ላይ የግእዝ ጽሑፍ ከ6ኛው መክዘ እስከ አሁን ዘመን የቀጠለ ሲሆን በማይክሮፊልም በተነሡት የብራና መጻሕፍት ቁጥር የሄድን እንደሆነ ቁጥራቸው እስከ 12,000 ይደርሳል፡፡ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጠፍተው የቀሩትን፣ በየቦታው ተደብቀውም አድራሻቸው ያልታወቁትን ሳይጨምር ማለት ነው፡፡ እስካሁን በተገኘው መረጃ ጥንታዊው የሚባለው የብራና የግእዝ መጽሐፍ በእንዳ አባ ገሪማ የሚገኘው ወንጌል ሲሆን የተጻፈውም በ6ኛው መክዘ ነው፡፡
  2. የወረቀት ላይ ጽሑፎች፡- ሦስተኛው የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መልክ በወረቀት የታተሙ መጻሕፍት ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በብራና የሚገኙትን የግእዝ መጻሕፍት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የቀረቡ እንጂ አዳዲስ ድርሰቶች አይደሉም፡፡ የግእዝ የታተሙ መጻሕፍት ታሪክ ጉተንበርግ የግእዙን ዳዊት ጀርመን ላይ ካሳተመበት ጊዜ ይጀምራል፡፡ ይህም የአራት መቶ ዓመታት ታሪክ ይኖረዋል፡፡
 1.2 የሦስቱ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ መልኮች ልዩ ባሕርይ
የድንጋይ ላይ ጽሑፎች
የድንጋይ ላይ ጽሑፎቹ የዘገባ መልክ ያላቸው፣ ታሪካዊ መረጃ የሚሰጡና በአብዛኛውም ሃይማኖታዊ ይዘት የሌላቸው ናቸው፡፡ ሃይማኖታዊ መረጃ ቢሰጡንም ነገሥታቱ ፈጣሪያቸውን ሲያመሰግኑ፣ ለፈጣሪያቸው የሰጡትን መሥዋዕት ሲገልጡ፣ ወይም የሙታን መታሰቢያ ሐውልቶቹ ደግሞ እግረ መንገዳቸውን በሚሰጡን መረጃ አማካኝነት ነው፡፡ የድንጋይ ላይ ጹሑፎቹ በሁለት ዓይነት አጻጻፍ የተጻፉ ናቸው፡፡ በጥንታዊና አናባቢ በሌለው ግእዝ ‹‹ሐወለተ፣ አከሰመ›› በሚለው መንገድና አናባቢ በተፈጠረለት ዘመናዊው ግእዝ የተጻፉ ናቸው፡፡ የድንጋይ ላይ ጽሑፎቹ በቅድመ አኩስምና በአኩስም ዘመን የተሠሩ ሲሆኑ የሚያንጸባርቁትም ያንኑ ዘመን ነው፡፡
የብራና ጽሑፎች
የብራና የግእዝ መጻሕፍት ከ6ኛው መክዘ ጀምረው እስካሁን የዘለቁና በሀገራችን የሥነ ጽሑፍ ዘመን በጥንታዊነትም ሆነ ለረዥም ዘመን በመዝለቅ ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው፡፡ የብራና የግእዝ የጽሑፍ ሀብቶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡
  1. ሃይማኖታውያን፣
  2. በዋናነት ሃይማኖታውያን ያልሆኑ ጉዳዮችን የያዙና
  3. ደብዳቤዎች
ሃይማኖታውያንየምንላቸው የተጻፉበት ዓላማ ሃይማኖትን ለማስተማር(ዶግማን፣ ቀኖናን፣ ትውፊትን፣ ታሪክን) ወይም ለአምልኮ ሥርዓት መፈጸሚያነት(ለጸሎት፣ ቅዳሴ፣ ውዳሴ፣ ዝማሬ፣ ሃይማኖታዊ ክዋኔ) የሆኑ ጽሑፎች ናቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ አብዛኞቹ የግእዝ የብራና ጽሑፎች ሃይማኖታውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ሃይማኖታውያን የግእዝ ጽሑፎች ሦስት እምነቶችን የያዙ ናቸው፡፡ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክና የይሁዲነት፡፡ የኦርቶዶክስ እምነትን የሚገልጡ መጻሕፍት በብዛትም ሆነ በቀደምትነት የግእዝን ጽሑፎች ይይዛሉ፡፡ ከ16ኛው መክዘ በኋላ ደግሞ የካቶሊክ እምነትን የሚገልጡ የግእዝ የብራና መጻሕፍትን እናገኛለን፡፡ የይሁዲነትን እምነት የሚገልጡት ጽሑፎች በኢትዮጵያ ከሚገኙ የቤተ እሥራኤል ወገኖች ጋር የተያያዙ ሲሆኑ እስካሁን ባሉን መረጃዎች ከመካከለኛው ዘመን ወደ ኋላ የዘለሉ አላገኘንም፡፡
የታተሙ የግእዝ የጽሑፍ ሀብቶች
የታተሙት የግእዝ ጽሑፎች የብራና ጽሑፎች ቅጅዎች ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በግእዝ የተጻፉ ኣዳዲስ ድርሰቶችን በኅትመት አላገኘንም፡፡ አብዛኞቹ የታተሙ የግእዝ ጽሑፎች ግእዝና አማርኛን፣ ግእዝና ትግርኛን፣ ግእዝና እንግሊዝኛን፣ ግእዝና ጀርመንኛን፣ ግእዝና ስፓኒሽን፣ ግእዝና ፈረንሳይኛን፣ ግእዝና ፖርቹጊዝን ጎን ለጎን ያደረጉ ሲሆኑ ለሁለት ዓይነት ተግባራት የታተሙ ናቸው፡፡ ለሃይማኖታዊ አገልግሎትና ለምርምር አገልግሎት፡፡ ለሃይማኖታዊ አገልግሎት የሚውሉት የግእዝ ኅትመቶች የሚታተሙት በአብዛኛው በኢትዮጵያና በኤርትራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ትንሣኤ ዘጉባኤ አሳታሚ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ፣ አኩስም ማተሚያ ቤት፣ ማኅበረ ቅዱሳንና የየአጥቢያው አብያተ ክርስቲያናት ሲያሳትሟቸው፤ በኤርትራ ዋናው አሳታሚ ማኅበረ ሐዋርያት ፍሬ ሃይማኖት ነው፡፡
ለምርምር የሚውሉት የግእዝ ኅትመቶች በአብዛኛው የሚታተሙት በውጭ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች በኩል ነው፡፡ እነዚህ ኅትመቶች በጥናታዊ መጽሔቶች ውስጥና ራሳቸውን ችለው በመጽሐፍ መልክ የሚወጡ ሲሆኑ ከግእዙ በተጨማሪ የመቅረቢያ ቋንቋውን ትርጉም፣ ስለ ጽሑፉ ዳራና የጽሑፉ ምሁራዊ ሐተታ ይቀርቡባቸዋል፡፡ አብዛኞቹም የተለያዩ ቅጅዎች ንጽጽር አሏቸው፡፡ በዚህ ረገድ የጣልያን፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የፈረንሳይና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለጥናት የሚታተሙ የግእዝ ጽሑፎችን በማተም ቤልጅየም የሚገኘውን ፒተርስ አሳታሚ የሚያህለው የለም፡፡
በግለሰብ ደረጃ ከጥንቶቹ እንግሊዛዊው ዋሊስ በጅ፣ ጀርመናዊው ኤድዋርድ ኡልንዶርፍና ኢዮብ ሉዶልፍ፣ ጣልያናዊዎቹ ኮንቲ ሮሲኒ፣ ኤንሪኮ ቼሩሊና ጉይዲ፤ ፈረንሳዊዎቹ ሬኔ ባሴ፣ ዣን ፕሩሶ፤ ራሺያዊውቢ ቱራየቭ ይጠቀሳሉ፡፡ ከዘመናችን ደግሞ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌን የሚስተካከል የለም፡፡
ክፍል ሁለት
ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች
ስለ ግእዝ ሥነ ጽሑፍ ብዙ ጊዜ ሲነገር ከሃይማኖታውያን የጽሑፍ ሀብቶቹ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለውም በሦስት ምክንያቶች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
  1. የግእዝ ቋንቋ በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መገልገያ ቋንቋ በመሆኑ
  2. አብዛኞቹ የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሃይማኖታውያን በመሆናቸው እና/ወይም
  3. ሃይማኖታውያን ስላልሆኑት የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች በብዛት ባለመነገሩና ባለመታተማቸው
ምንም እንኳን ከላይ የተገለጠው ግእዝን ከሃይማኖታዊ ድርሰቶች ጋር የማያያዝ ትርክት ጊዜ ጠገብ ቢሆንም በግእዝ ቋንቋ ተጽፈው የምናገኛቸው አያሌ ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ግን አሉ፡፡ እነዚህ ሃይማኖታውያን ያልሆኑት የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ከሁለት ምንጮች የተገኙ ናቸው፡፡
  1. ከሀገር ውጭ
  2. ከሀገር ውስጥ
ከሀገር ውጭ የምንላቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ተደርሰው ወደ ግእዝ ቋንቋ የተተረጎሙ ሲሆኑ እነርሱም ከግሪክ፣ ላቲን፣ ዓረብና ቅብጥ የተተረጎሙ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን መገኛ ቋንቋዎቻቸው እነዚህ ቢሆኑም በእነርሱ በኩል ግን ከምሥራቅ ሕንድ እስከ ምዕራብ ሮም የሚደርሱ ድርሰቶችን አግኝተናል፡፡
ከሀገር ውስጥ የምንላቸው ደግሞ በኢትዮጵያውያን ደራስያን የተደረሱና በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ናቸው፡፡ እነዚህም በተለይ በመካከለኛው ዘመን ተጀምረው እስከ 18ኛው መክዘ የዘለቁ የግእዝ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ናቸው፡፡ የዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ይህ በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ ላይ የተወሰኑትን እናያቸዋለን፡፡
  1. ፊሳሎጎስ፡- ፊሳሎጎስ ከግሪክ ወደ ግእዝ በ6ኛው መክዘ የተተረጎመ መጽሐፍ ነው፡፡ ፊሳሎጎስ በብዙ ቋንቋዎች የታወቀ መጽሐፍ ሲሆን የስሙ መጠሪያ ‹ፊዚዮሎጎስ› ከሚለው የግሪኩ ስም የመጣ ሆኖ በ200 ዓም አካባቢ በእስክንድርያ ውስጥ በግሪክ ቋንቋ የተጻፈ ነው፡፡ መጽሐፉ 48 ምእራፎች ሲኖሩት 42ቱ በእንስሳት፣ 2ቱ በዕጽዋት፣ 4ቱ ደግሞ በማዕድናት ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ምእራፍ አንድ እንስሳ፣ ዕጽ ወይም ማዕድንን በማንሳት፣ ጠባዩንም በመተንተን ከመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጋር አጣምሮ የሚያቀርብ ነው፡፡
ይህ መጽሐፍ በትውፊታዊው የኢትዮጵያ ትምህርት ውስጥ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ማስተማሪያ ዋና ምንጭ ሆኖ ያገለገለ ነው፡፡
  1. ፈውስ ሥጋዊ፡- ይህ መጽሐፍ በአብዛኛው የሚታወቀው ፈውስ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ በሚል ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱ መጻሕፍት የተለያዩ ናቸው፡፡ ፈውስ መንፈሳዊ ምናልባት ከ13-16ኛው መክዘ ባለው ጊዜ ወደ ግእዝ የተተረጎመ መንፈሳዊ መጽሐፍ ነው፡፡ ዓላማውም በኃጢአት የቆሰለችን ነፍስ በመንፈሳዊ ሕክምና ማከም ነው፡፡ ፈውስ ሥጋዊ ግን በትክክል እስካሁን ያልተጠና ምናልባት ግን ከ17ኛው መክዘ በፊት የተደረሰ(ከሀገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች) መጽሐፍ ይመስለኛል፡፡ በውስጡ ለሥጋዊ ሕመም ፈውስ ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የዕጽዋትንና የእንስሳትን ውጤቶች የያዘ ነው፡፡
  2. መጽሐፈ አዕባን፡- እስካሁን ባለኝ መረጃ መሠረት ስለዚህ መጽሐፍ ጥናት አልተደረገም፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ በዚሁ ስም አንዲት አነስተኛ መጽሐፍ አሳትሟል፡ የተጠቀመው ይህንን ምንጭ ይሁን ወይም ሌላ አልተገለጠም፡፡ መጽሐፉ ለልዩ ልዩ ተግባር ሊውሉ የሚችሉ ድንጋዮችን በተመለከተ የተጻፈ የጂኦሎጂ መጽሐፍ ነው፡፡ አልፎ አልፎም ድንጋዮቹ በምን ዓይነት አካባቢ እንደሚገኙ ይናገራል፡፡ በኋላ ዘመን የድንጋይ ትርጉምና ጥቅም ተብሎ የተተረጎመውና በEMML 6815 የምናገኘው ከዚህ የተወሰደ ሳይሆን አይቀርም፡፡
  3. ዜና እስክንድር፡- ይህ መጽሐፍ በጥንታዊው ዓለም ታሪክ የተጻፈውን የታላቁን የግሪክ ንጉሥ የእስክንድርን ታሪክ በግእዝ የሚያቀርብ ነው፡፡ መጽሐፉ ምንጩ ግሪክ ሲሆን ከግሪክ ወደ ሶርያ፣ ከሶርያ ወደ ዓረብኛ፣ ከዓረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመ ነው፡፡ የተተረጎመውም በ16ኛው መክዘ ምናልባት በ11ኛው የደብረ ሊባኖስ አበ ምኔት በዕጨጌ ዕንባቆም የመናዊ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ መጽሐፉ ሲተረጎም ርእሱ ‹‹ሑረቱ ለእስክንድር›› የሚል ነበር፡፡
እስክንድርን በተመለከተ በ14ኛው መክዘ እንደዚሁ አንድ ትርጉም ተከናውኖ ነበር፡፡ ‹‹ዜና እስክንድር›› የተባለው ይህኛው መጽሐፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ መጽሐፍ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው በትግራይ አካባቢ በሚገኙ ገዳማት ውስጥ ነው፡፡ ዜና እስክንድርየእስክንድርን የጀግንነት ታሪክ በክርስትና የሞራል ትምህርት ውስጥ ለማሳየት የሚሞክር ሲሆን ዋናው ዓላማውም ነገሥታቱን፣ መኳንንቱንና ወታደሮችን ማጀገን ነው፡፡
5.       ፍትሐ ነገሥት፡- ፍትሐ ነገሥት ሁለት ክፍል አለው፡፤ ፍትሕ ሥጋዊና ፍትሕ መንፈሳዊ፡፤ ትኩረታችን በፍትሕ ሥጋዊ ላይ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥትን ያዘጋጀው በ13ኛው መክዘ ግብጽ ውስጥ የነበረው እብን- እል አሳል የተባለ ባለሞያ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕግጋቱን ከተለያዩ የቀኖና መጻሕፍት ሲወስድ ሥጋዊ ሕግጋቱን ደግሞ ከሮም፣ ከባዛንታይምና ከሌሎች ሀገሮች ሕግጋት ወስዷቸዋል፡፡
መጽሐፉ ወደ ግእዝ የተተረጎመው በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሀገሪቱ እስከዚያ ድረስ ትጠቀም የነበረው የኦሪቱን የሕግ መንገድ በመሆኑ ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ይህንን ሕግ ለመቀየር በማሰቡ ነው፡፡ ይህንን ሃሳቡን የነገረውና በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጴጥሮስ አብደል ሰይድ የተባለ ግብጻዊ ፍትሐ ነገሥትን ንጉሡ ከግብጽ እንዲያስመጣ መከረው፡፡ ጴጥሮስ አብደል ሰይድም በንጉሡ ተልኮ መጽሐፉን ካመጣው በኋላ ወደ ግእዝ ተረጎመው፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ ግን ፍትሐ ነገሥት በሥራ ላይ ለመዋሉ ምንጭ የተገኘለት በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥት ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሕግ እስክትቀርጽ ድረስ የተጠቀመችበት ለ600 ዓመታት ያህል ያገለገለ የሕግ ምንጭ ነው፡፡
6.       ዜና ስክንድስ፡- ስክንድስ በክርስትና የመጀመሪያዎቹ ዘመን የነበረ የግሪክ ፈላስፋ ነው፡፡ እናትና አባቱ የፍልስፍናን ነገር እንዲያጠና ወደ አቴንስ ልከውት የተመራመረውን ነገር ነው መጽሐፉ የሚገልጥልን፡፡ ይህ መጽሐፍ በሁለት የምዕራብ ቋንቋዎች(ላቲንና ግሪክ)ና በሦስት የምሥራቅ ቋንቋዎች(ሲርያክ፣ዓረብኛና ግእዝ) ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያው መጽሐፍ ከዐረብኛ የተተረጎመ ይመስላል፡፡ ወደ ግእዝ የተመለሰውም በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን መሆኑን ይገልጣል፡፡
ግእዙ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ የመጀመርያው ክፍል የስክንድስን ሕይወት ይይዛል፣ ሁለተኛው ደግሞ የ55 ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችንና መልሶችን የያዘ ሲሆን ሦስተኛው ክፍል 108 ጥያቄዎችን እያነሣ ያትታል፡፡
ሃይማኖታውያን ያልሆኑ የግእዝ ጽሑፎች (ግንቦት 2006 ዓም አኩስም ትግራይ)

7. መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን፡- ይህ ከ1503 - 1515 ዓም ባለው ዘመን የተተረጎመው መጽሐፍ በግእዝ ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የታወቀ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የግሪክና የሌሎች ሀገሮች ፈላስፎችን አባባሎችና ትምህርቶች የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡

8.በርለዓም ወየወሴፍ፡- በርለዓም ወየወሴፍ የተለያዩ ምሳሌዎችንና ተረቶችን የያዘ የሕንድ መጽሐፍ ነው፡፡ የተወሰደውም ከትውፊታዊው የጉተማ ቡድሐ የሕይወት ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ የፍቅር ታሪክ ነው፡፡ የዚህ መጽሐፍ ቅጅዎች በአይሁድ፣ በማኒያውያን፣ በሙስሊሞችና በክርስቲያኖች ዘንድ ይገኛሉ፡፡

ዋዳጎስ የተባለ እጅግ ባዕለ ጸጋ የሆነ ኃይለኛ የሕንድ ንጉሥ በሕንድ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ጨፈጨፈ፡፡ አንድ ቀን ዋዳጎስ የወሴፍ የሚባል ወንድ ልጅ ወለደ፡፡ ኮከብ ቆጠሪዎችና ጠንቋዮች ስለ ልጁ ዕጣ ፈንታ ሲጠየቁ ልጁ ወደፊት ክርስቲያን እንደሚሆንና የክርስቶስን ሃይማኖትንም ከፍ ከፍ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ይህንን በመፍራት ንጉሡ ልጁን በአንድ ቤተ መንግሥት ውስጥ ወስኖ አስቀመጠው፡፡ ኀዘን፣ ድክመት፣ ሞት የሚባሉትን ነገሮች እንዳያውቅ እርሱንም ከደስታ የሚያወጣውን ነገር እንዳያጋጥመው አደረገው፡፡

እያደገ ሲሄድ ግን መስፍኑ ከዚያ ቤተ መንግሥት ውጭ ያለውን ዓለምም ለማወቅ ፈለገ፡፡ ከቤተ መንግሥቱ ውጭም ኀዘን፣ በሽታ፣ ልቅሶ፣ ረሃብና ሞት መኖራቸውን ዐወቀ፡፡ ታዋቂው መናኝ መምህር በርለዓምም መስፍኑን አገኘው፡፡ ስለ እግዚአብሔርና ስለ ክርስትናም አስተማረው፡፡ ይህንንም ያስተማረው የተለያዩ ታሪኮችንና አባባሎችን በመጠቀም ነበር፡፡

መስፍኑ የወሴፍ ዓለምን ለመካድ ከበርለዓም ጋር ያለውንም ግንኙነት አባቱ ሳይሰማ ለማቆም ፈለገ፡፡ አባቱ ነገሩን ከመስማቱ በፊትም በርለዓም ከእርሱ ተለየ፡፡ ንጉሡም ነገሩን ሲሰማ እጅግ ተበሳጨ፡፡ የወሴፍን ወደ ጥንት እምነቱ ለመመለስም የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡ የመንግሥቱን አንድ ሦስተኛ ለመስጠት ቃል እስከ መግባትም ደረሰ፡፡ የወሴፍ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በመጨረሻም ንጉሡ ራሱ ስሕተቱ ገባው፡፡ አማካሪዎቹ ሁሉ ክርስቲያን ከሆኑ በኋላም ንጉሡም ክርስትናን ተቀበለ፡፡

አባቱ ከሞተ በኋላ የወሴፍ መንግሥቱን ተወ፡፡ እጅግ ለሚያምነው ተከታዩ ዙፋኑን በመስጠትም መምህሩ በርለዓም ለመፈለግ ወደ በረሃ ሄደ፡፡ እዚያ በርለዓምን ሲያገኘውም ሁለቱም የምናኔ ሕይወታቸውን እስከ ዕለተ ሞታቸው ቀጠሉ፡፡

መጽሐፉን ያስተረጎመው ዐፄ ገላውዴዎስ ሲሆን የተረጎመው ደግሞ እጨጌ ዕንባቆም ነው፡፡ ትርጉሙም የተከናወነው በ1546 ዓም ነው፡፡ በርለዓም ወየወሴፍ ከሕንድ ተወስዶ በክርስቲያናዊ መንገድ የቀረበ የሥነ ምግባር ማስተማሪያ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በሦስቱ ዋና ዋና እምነቶች (አይሁድ፣ ክርስትናና እስልምና) ተቀባይነት ያገኘ መጽሐፍ ነው፡፡

9. አቡሻክር
አቡ ሻክር ቢን አቢ ኤል ከሪም ቡጥሮስ ቢን አል ሙሐዲብ ያዘጋጀው የዓለምን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ፡፡ የኖረው ከ1200/ 10 እስከ 1295 እኤአ  ካይሮ ውስጥ ነው፡፡ አቡሻክር የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆንና የቅዱሳት መጻሕፍት ደራሲ ነበር፡፡ ከእርሱ መጻሕፍት መካከል በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የታወቀው ‹‹ኪታብ - አት - ታዋሪህ›› የተባለውና የዓለምን ታሪክ በአጭር በአጭሩ የሚገልጠው ‹አቡሻክር፣ ሐሳበ አቡሻክር›› እየተባለ የሚጠራው መጽሐፍ ነው፡፡

ከ1626 እስከ 1630 ዓም ባለው ዘመን መካከል የተጻፈ አንድ አቡሻክር እንዲህ ይላል ‹‹ዝንቱ መጽሐፍ ብሩክ ዘደረሰ እግዚእ ትሩፈ ምግባር ማእምረ መጻሕፍት አቡሻክር ወልደ አቡእልከረም ጴጥሮስ መነኮስ እብንልመሐድብ ዘበትርጓሜሁ ወልደ ግሡጽ ወእመአኮ ወልደ ምሁር ዘእሙር በሪሺ ዘተሠይመ ዲያቆነ በቤተ ክርስቲያን ዘመዐልቃ፡፡ እንዘ ይነግር በእንተ ሐሳበ ዐለም፡፡››
የዐረብኛው መጽሐፍ የተጻፈው በ1250 ዓም ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድ የብራና መጽፈፍ ላይ መጽሐፉ የተጻፈው በ6750 ዓመተ ዓለም፣ በ655 ዓመተ ተንባላት (በእስልምና አቆጣጠር) መሆኑን ይገልጣል፡፡ ይህም በ1250 ዓም መሆኑን ያመለክታል፡፡

10.     በአርመንኛ የሚገኙ ቁጥሮች ትርጉም፡- ይህ መጽሐፍ እስካሁን አልተገኘም፡፡ የተጻፈው በ11ኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ በአቡነ ዕንባቆም የመናዊ ነው፡፡ ከስሙ ለመገመት እንደሚቻለው የአርመንኛ ቁጥሮችን ኮድ የሚተረጉም ይመስላል፡፡ ስለ መጽሐፉ ፍንጭ የሰጠን አልቫሬዝ ነው፡፡

11.       የላቲን ቃላት ዝርዝር፡- ይኼኛውም መጽሐፍ የዕንባቆም መጽሐፍ ነው፡፡ እስካሁን ግን አልተገኘም፡፡ ከስሙ ለመገመት እንደሚቻለው የላቲን ቃላትን የሚዘረዝርና የሚተረጉም ይመስላል፡፡ አልቫሬዝ ዕንባቆም ላቲን እንደሚችል ይነግረናል፡፡ ምናልባትም ጥንታዊ መዝገበ ቃላትም ይሆናል፡፡

12.     በሮማን ዘየ(dialect) የተጻፉ ቁጥሮች ትርጉም፡- ይህ መጽሐፍ የዕጨጌ ዕንባቆም መጽሐፍ ሲሆን የሮምን ቁጥሮችን መንፈሳዊ/ የኮድ ትርጉም የያዘ ይመስላል፡፡ መጽሐፉ እስካሁን አልተገኘም፡፡

13. ዮሐንስ መደብር፡- ይህ መጽሐፍ በግእዝ ሊቃውንት ዘንድ እጅግ የታወቀ የታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ ዲያቆን ቅብርያል በ16ኛው መክዘ የነበረ ግብጻዊ ነው፡፡ ዐረብኛና ግእዝ ይችል ነበር፡፡ በሠራዊቱ አለቃ በአትናቴዎስና በእቴጌ ማርያም ሥና ትእዛዝ ‹‹ዮሐንስ መደብር›› የተሰኘውን የነቅዩስ ጳጳስ የዮሐንስን መጽሐፍ በ1594 ዓም በዐፄ ያዕቆብ ዘመን በአራተኛው ዓመት ተርጉሟል፡፡

በአንድ መጽሐፍ መጨረሻ ላይ እንዲህ ይላል ‹‹ወተርጎምና በአስተሐምሞ ብዙኅ ለዝንቱ መጽሐፍ እም ዓረቢ ለግእዝ አነ ምስኪን ምኑን በኀበ ሰብእ ወትኁት በውስተ ሕዝብ ወዲያቆን ቅብርያል ግብጻዊ ወልደ ሰማዕት ዮሐንስ ዘቀልዩቢ በትእዛዘ አትናቴዎስ ሊቀ ሠራዊት ዘኢትዮጵያ፡፡ ወበትእዛዘ ንግሥት ማርያም ሥና››

14. አንጋረ ፈላስፋ፡- ይህ የተለያዩ ፈላስፎችን አነጋገር የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ የአሪስቶትል(አርስጣጣሊስ)፣ የፕሉቶ (አፍላጦን) የሶቅራጥስ ና የሌሎችንም ፈላስፎች ንግግሮች ይዟል፡፡ መጽሐፈ ፈላስፋ ጠቢባን በመባልም ይታወቃል፡፡

15. ሐተታ ዘርዐ ያዕቆብ አኩስማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራንዛዊ፡- ይህ የ17ኛው መክዘ ኢትዮጵያዊ የፍልስፍና መጽሐፍ ሲሆን በሁለት ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ነው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በተባለ የአኩስም ተወላጅና ወልደ ሕይወት በሚባል የጎንደር (እንፍራንዝ) ተወላጅ፡፡ ሁለቱን ያገናኛቸው አመለካከት ነው፡፡ ዘርዐ ያዕቆብ በወቅቱ ይታሰብ ከነበረው የእምነት፣ የባሕልና የአስተዳደር አስተሳሰብ ወጣ ብሎ ነገሮችን በሰላ ዓይን ይመረምር ነበር፡፡ ደቀ መዝሙሩ ወልደ ሕይወትም ይህንኑ መሥመሩን ተከትሎታል፡፡

16. መጽሐፈ ማስያስ፡- አባ ማስያስ በጣና ገዳማት በ15ኛው መክዘ የነበሩ ኢትዮጵያዊ መነኮስ ናቸው፡፡ ስለ ዓለም ነገር ማወቅ ይፈልጉ ነበር፡፡ ይህንንም በጾምና በጸሎት ከፈጣሪያቸው ጠየቁ፡፡ በመጨረሻም መላእክት እየረዷቸው ዓለምን ዞሩ፡፡ በመጽሐፋቸው እንደሚገልጡት ከሃያ ዓለማት በላይ አሉ፡፡ በስተ ምዕራብ በኩል አዲስ ዓለም እንዳለም ይገልጡታል ‹‹ሐዲሰ ዓለም›› ሲሉ፡፡ ይህም በ16ኛው መክዘ ተአምረ ማርያምም ላይ ተገልጧል፡፡ ከምድራችን ውጭም ሌሎች ሰዎች እንዳሉ ይገልጣሉ፡፡ ‹‹ካልዕ ፍጥረታት›› ይሏቸዋል፡፡ ይህንን ሃሳባቸውን የክብራን ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ የነበረው የ14ኛው መክዘ ሊቅ ርቱዐ ሃይማኖትም ‹‹መጽሐፈ ርቱዐ ሃይማኖት›› በተሰኘው ድርሳኑ ላይ ይገልጠዋል፡፡

17. መጽሐፈ ነደቅት፡- ይህ መጽሐፍ የተገኘው ከጎንደር አካባቢ ነው፡፡ በትክክል ከየት ገዳም እንደተገኘ አልተገለጠም፡፡ ሥራው የ17ኛው መክዘ ይመስላል፡፡ እንደ እኔ ግምት ግን ከጣና ገዳማት የወጣ ይመስላል፡፡ መጽሐፉ ቤት ሲሠራ መከተል ስለሚገባው አሠራር ይገልጣል፡፡ ወራጅና ቋሚ፣ በርና መስኮት፣ ጣራና ድምድማት፣ ክብና አራት መዓዝን እንዴት ማውጣት እንደሚቻል ልኬቱን በክንድ፣ በስንዝርና በርምጃ እየለካ ያስቀምጣል፡፡ መጽሐፉ በዋናነት ለአብያተ መንግሥትና አብያተ ክርስቲያናት መሥሪያ የሚውል ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በሀገራችን ጥንታዊ የሆነ የግንባታ ጥበብ እንደነበርና ይህም በመለኪያዎች ይሠራ እንደነበር ያመለክተናል፡፡

18. ትእይንተ ጎንደር፡- ይህ በ17ኛው መክዘ አዛዥ ሲኖዳ በተባለ የጎንደር ሊቅ የተዘጋጀ መጽሐፍ ነው፡፡ አዛዥ ሲኖዳ በማበብ ላይ ስለነበረችው የጎንደር ከተማ የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ ሲኖዳ የዐፄ በካፋ ጸሐፌ ትእዛዝና ታሪክ ጸሐፊ ሲሆን የአድያም ሰገድ ኢያሱ የልጅ ልጅ ነው፡፡ ደራሲ፣ ፈላስፋና ባለ ራእይ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ሲኖዳ ከዚህም ሌላ እስካሁን ድረስ ያላገኘናቸውንና በለሳ ተክለ ሃይማኖት በሚገኘው መጽሐፈ ቄርሎስ የመጨረሻ ገጽ ላይ የተጻፉትን መርሥኤ ኀዘን፣ ምዝባሬ ቤተ መንግሥት፣ ተፍጻሜተ መንግሥት፣ ምዝባሬ ቤተ መቅደስ፣ ምሳሌ መምህራን፣ መጽሐፈ ሰዋስውና ማኅለቅተ ዘመን የሚሰኙ ድርሰቶችንም ጽፎ ነበር፡፡

19. ዜና መዋዕሎች፡- በግእዝ ከተጻፉት ለሃይማኖት ማስተማሪያነት ከማይውሉት መጻሕፍት መካከል ብዛት ያላቸው ዜና መዋዕሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ዜና መዋዕሎች በየዘመናቱ በቤተ መንግሥት በተደራጁ ጸሐፍት በጸሐፌ ትእዛዙ በኩል የሚዘጋጁ የነገሥታቱ ታሪኮች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከቤተ መንግሥት ወጣ ባሉ ሰዎችም ይዘጋጃሉ፡፡ ጸሐፍቱ የቤተ ክህነት ትምህርት ያላቸው በመሆኑ ታሪኩን በቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶችና ምሳሌዎች ያዋዙታል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃ መሠረት ቀደምት ሆኖ በብራና ተጽፎ የተገኘው የዐፄ ዓምደ ጽዮን ዜና መዋዕል ሲሆን በግእዝ ቋንቋ ለመጨረሻ ጊዜ የተጻፈው ደግሞ የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ዜና መዋዕል ነው፡፡ በርግጥ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን የዓምደ ጽዮንን ዜና መዋዕል አደረጃጀት በመመልከት ከዚያ በፊትም በዛግዌ ሥርወ መንግሥት የዜና መዋዕል አጻጻፍ ሳይኖር አይቀርም ብለው ይገምታሉ፡፡ በኋላ በገድልነት የተቀበልናቸው የላሊበላ፣ የሐርቤ፣ የነአኩቶ ለአብና የይምርሐነ ክርስቶስ ገድላት ዜና መዋዕሎች የነበሩ ይመስላሉ ብለውም ይሞግታሉ፡፡

እስካሁን በታወቀው መሠረት
1.    የንጉሥ ዓምደ ጽዮን
2.    የንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ፣
3.    የንጉሥ በዕደ ማርያም
4.    የንጉሥ እስክንድር፣
5.    የንጉሥ ዓምደ ጽዮን 2ኛ
6.    የንጉሥ ናዖድ
7.    የንጉሥ ልብነ ድንግል
8.    የንጉሥ ገላውዴዎስ
9.    የንጉሥ ሚናስ፣
10.የንጉሥ ሠርፀ ድንግል
11.የንጉሥ ያዕቆብ
12.የንጉሥ ዘድንግል
13.የንጉሥ ሱስንዮስ
14.የንጉሥ ኢያሱ 1ኛ
15.የንጉሥ ዮሐንስ 1ኛ
16.የንጉሥ በካፋ
17.የንጉሥ ኢያሱ 2ኛ
18.የንጉሥ ኢዮአስ
19.የዘመነ መሳፍንት ነገሥታት
20.የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ
ዜና መዋዕሎቻቸው በግእዝ ተገኝተዋል፡፡ እጅግ የሚያስገርመው ግን ታዋቂው የጎንደር ንጉሥ ዐፄ ፋሲለደስ ዜና መዋዕሉ ሊገኝ አልቻለም፡፡ በርግጥ ፈረንሳዊው ዣን ሩሶ (J. Perruchon) Le Regne de Fasiledes Revue Semitique, 1897-99 በግእዝና በፈረንሳይኛ ያሳተመው ዶክመንት አለ፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዜና መዋዕል አይደለም፡፡ ከታሪከ ነገሥት የተወሰደ ነው፡፡  

20.    ታሪከ ነገሥት፡- በኢትዮጵያ የታሪክ አጻጻፍ ስልት ላይ ክብረ ነገሥት የራሱን አሻራ በማሳረፉ በእርሱ መንገድ አያሌ ታሪከ ነገሥቶች ተጽፈዋል፡፡ እነዚህ ታሪከ ነገሥቶች በአብዛኛው ከአዳም ተነሥተው ጸሐፊው እስካለበት ዘመን ድረስ ያሉትን ነገሥታት በመከተል የሀገሪቱን ታሪክ የመዘገቡ ድርሳናት ናቸው፡፡ ከዜና መዋዕሎቹ የሚለዩት በአንድ ንጉሥ ላይ አለማተኮራቸው ነው፡፡ እስካሁን በማይክሮ ፊልም ከተመዘገቡት መካከል መጽሐፈ ታሪክ(EMML 5538)፣ታሪከ ነገሥት(EMML 5731)፣ታሪከ ነገሥት ዘዙር አምባ(EMML 7619)፣ ታሪከ ነገሥት ዘመካነ ሰማዕት(EMML 8962)፣ ታሪከ ነገሥት ዘይጋንዳ(EMML 8186)፣ ታሪከ ነገሥት ዘጎሐ ጽዮን((EMML 8053)፣ ታሪከ ነገሥት (EMML 7954)፣ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ ሬኔ ባሴ ያሳተመውና አጭሩ የፓሪስ ዜና መዋዕል በመባል የሚታወቀው ዜና መዋዕልም ታዋቂ ነው፡፡ ከሁሉም የሚበልጠውና ብዙ የተደከመበት ግን ደጃዝማች ኃይሉ እሸቴ ያዘጋጁትና በ480 የብራና ገጽ የተጠናቀቀው ታላቁ ታሪከ ነገሥት ነው፡፡ ዛሬ ዋናው ቅጅ በፓሪስ የሚገኘው ይህ የሀገሪቱን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ በዘመነ መሳፍንት ከጦርነትና ከቁንጸላ የተረፈውን መዝገብ አሰባስበው በደቡብ ጎንደር ማኅደረ ማርያም በግዞት እያሉ ደጃዝማች ኃይሉ ያስጻፉት ነው፡፡ እርሳቸው ይህንን ታሪካዊ ሥራ ባይሠሩ ኖሮ በኋላ ዘመን በደረሰው የድርቡሾች ጥፋት ተቃጥሎ አናገኘውም ነበር፡፡

21.   መጽሐፈ ፀሐይ፡- ይህ መጽሐፍ የፀሐይን ተፈጥሮ፣ ጠባይና ሁኔታ የሚተነትን መጽሐፍ ነው፡፡ እስካሁን እኔ ያየሁት በማይክሮ ፊልም ቁጥር EMML 7625 ከፍርኩታ ኪዳነ ምሕረት የተነሣውን ቅጅ ነው፡፡

22.    ነገረ ግራኝ፡- ይህ መጽሐፍ በኢብን ኢብራሂም አሕመድ አልጋዚ ጊዜ በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የወደመውን የሀገር ሀብት የሚያሳይ ነው፡፡ ስለ አሕመድ ግራኝ የኢትዮጵያውያንን ምልከታ ያሳየናል፡፡ የግራኝን ታሪክ ከጻፈው ከዐረብ ፋቂህ ‹ፍቱል አል ሐበሽ› ጋር አስተያይቶ ማንበቡ ይጠቅማል፡፡ እኔ ያየሁት በEMML 7538 በማይክሮ ፊልም የተነሣውን ነው፡፡

23.    ነገረ ወግ ወሥርዓተ መንግሥት፡-  ይሄ መጽሐፍ የቤተ መንግሥቱን ወግና ሥርዓት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ የቤተ መንግሥት የፕሮቶኮል መጽሐፍ እንደማለት ነው፡፡ እኔ ያየሁት በEMML 6681 የተነሣውን የኢቲሳውን ቅጅ ነው፡፡ የተጻፈው በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመነ መንግሥት( 1555-88 ዓም) ሲሆን በኋላ በአድያም ሰገድ ኢያሱ ጊዜ (1674-98 ዓም) አዛዥ ወልደ ሥላሴ የተባለ ነገር ዐዋቂ ሰው እንደገና ጽፎታል፡፡

24.   ባሕረ ሐሳብ፡- ባሕረ ሐሳብ የዘመን አቆጣጠር ትምህርት ነው፡፡ ጥንታዊው የቁጥር ትምህርት የሚሰጠውም በባሕረ ሐሳብ አማካኝነት ነው፡፡ ይህ የነ ዮሐንስ መደብርን፣ የነ አቡሻሕርንና የሌሎችንም መሠረት አድርጎ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የተዘጋጀው መጽሐፍ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ በመጀመሪያው ክፍል የዘመናት ማውጫ መንገዶች የሚጠኑ ሲሆን በመጨረሻ ደግሞ በየዘመናቱ የተከናወኑ ክንዋኔዎች በዘመን ቅደም ተከተል ይቀመጡበታል፡፡ ባሕረ ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀመረው በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በ3ኛው ዘመናቸው ማለትም በ1600 ዓም ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ጀምሮ ያለው በዘመን ተሠፍሮ ተቆጥሮ ተጻፈ፡፡

25.  መጽሐፈ አኩስም፡- መጽሐፉ ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ በአኩስም ጽዮን የነበሩ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ በሀገራችን ውሎችንና ማስረጃዎችን በማዕከላዊነት የመመዝገብ አሠራር ከጥንት እንደነበር የሚያመለክት ነው፡፡ የኋላ ሊቃውንት አስተጋብተውት ነው ‹‹መጽሐፈ አኩስም›› የሚለውን ስም ያገኘው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ነገሥታቱና መኳንንቱ ለአኩስም ጽዮን የሰጡት ስጦታ፣ ለሌሎች ቦታዎች ያደረጉት ስጦታና ሌሎች የወሳኝ ኩነት መረጃዎች ሠፍረውበታል፡፡ ይህንን መሰሉ አሠራር በሀገራችን በወምጌል፣ በግንዘትና በስንክሳር መጻሕፍት ኅዳጎች ላይ የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም የሐይቅ እስጢፋኖስና የክብራን ገብርኤል ወንጌሎች፣ የጎንደር ቁስቋም ግንዘት፣ የኤርትራ ደብረ ሊባኖስ ዘሺምዛና ወንጌል ማሳያዎች ናቸው፡፡

26. መልክእ፡- መልክእ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የረዥም ዘመን ታሪክ ያለው ግጥማዊ ሥነ ጽሑፍ  ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የተለመደውም ለቅዱሳን ሲደረስ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሃይማኖታዊ ያልሆኑ መልክኦችን እናገኛለን፡፡ የእነዚህ መልኮች ዓላማም የሚደረስለትን ሰው በጎ ነገር በማንሣት ማወደስ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን የዐፄ ምኒሊክ መልክእ ነው፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት የተጻፈው በ1915 እኤአ በሊዝበን ፖርቹጋል የታተመው ‹‹መልክእ ዘምኒሊክ ንጉሠ ነገሥት›› የንጉሡን በጎነት፣ ሃይማኖተኛነትና ጀግንነት እያነሣ የሚያወድስ ነው፡፡ በተለይም በዐድዋ ጦርነት ከጣልያን ጋር የተደረገው ተጋድሎ ታላቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ የጣልያን ጄኔራሎች ስሞችም በብዛት ተካትተዋል፡፡

ሰላም ለአእናፊከ ከመ ፄና ገነት ምዑዝ
ሱራሬሆን ሠናይ ወጥቀ ሐዋዝ
ንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ ዘኢትዮጵያ አርዝ
ሶበ ተለቅሃ ኢጣልያ ወርቀ አይሁዳዊ እንግሊዝ
ዘይከፍል ስዕነ አሐዞ ትካዝ
† † †
ሰላም ለአፉከ ለፈጣሪ ዘየአኩቶ
ኢይትናገር ስላቅ ወኢይነብብ ከንቶ
ንጉሠ ነገሥት ምኒሊክ ለኢትዮጵያ ማኅቶቶ
ሐልቀ ማንጆር ወስዕነ ፍኖቶ
ጀነራል ባራቴሪ ሶበ ገብዐ ደንገፀ ዖምበርቶ


ማጠቃለያ

ግእዝ ለረዥም ዘመናት የሀገሪቱ የመንግሥት፣ የቤተ ክህነት፣ የትምህርት፣ የውጭ ግንኙነት፣ የሥነ ጽሑፍና የሕግ ቋንቋ ሆኖ በመኖሩ አያሌ ሥነ ጽሑፋዊ ሀብቶችን አካብቷል፡፡ ብዙ ጊዜ ቋንቋውን ከቤተ ክርስቲያንና ከአምልኮ ጋር ብቻ በማያያዛችን በውስጡ ያለውን ሌላም ዕውቀት ሳንካፈለው ቀርተናል፡፡ ይህ ደግሞ በግእዝ ቋንቋ ተጽፎ ከተከማቸው ሀብት ሳንካፈል ለሌሎቹ አሳልፈን እንድንሰጠው አድርጎናል፡፡ በመሆኑም ከትናንት ብንዘገይ እንኳን ከነገ ቀድመን በመነሣት የግእዝ ቋንቋ የሚጠናበትን፣ በውስጡ ያዛቸው ዕውቀቶችም እየተተነተኑ ለሀገርና ለወገን ጥቅም የሚውሉበትን መንገድ መፈለግ የትውልዱ ድርሻ ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገራችን ውስጥ አለ የሚባለውን ነገር ሁሉ የመፈተሽ፣ የማረጋገጥና ለጥቅም የማዋል ኃላፊነት አለባቸውና በግእዝ ቋንቋ ተጽፈው የተላለፉልንን ዕውቀቶች በመፈተሽ ለጥቅም ማዋሉን ሊተጉበት ይገባል፡፡ 

Read more http://www.danielkibret.com/2014/05/2006_2419.html