ግዝረት

ጥር 5/2007ዓ.ም

ግዝረት ከጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ንዑሳን በዓላት የሚባሉትም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ግዝረት፣ ቃና ዘገሊላ፣ ልደተ ስምዖን፣ ደብረ ዘይት፣ የመጋቢት መስቀልና መስቀል ናቸው፡፡ ነቢያት ይወርዳል፤ ይወለዳል ብለው በትንቢት ይጠባበቁት የነበረው መሲሕ የዓለም ብርሃን፣ የነፍሳት ጠባቂ መሆኑን አምነን የምናከብራቸው ስብከት፣ ብርሃንና ኖላዊ ይባላሉ፡፡

ከእናቱና ከደቀመዛሙርቱ ጋር በሰርግ ቤት የተገኙበት ቃና ዘገሊላ፣ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበትና አረጋዊ ስምዖንን የሰላሳ ዓመት ጎልማሳ የሆነበት “ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና” በማለት የተናገረበት ልደተ ስምዖን ከንዑሳን በዓላት ይመደባሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግዝረት በመሆኑ ሀተታዬን ወደ እሱ እመልሳለሁ፡፡

 

ፍቅር ወልድን ከዙፋኑ ስቦት ወርዶ ሥጋ ማርያምን ተዋሕዶ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ማሕፀኗን ዓለም አድርጎ ከቆየ በኋላ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ በዘመነ ማቴዎስ ተወለደ፡፡ በተወለደ በስምንተኛ ቀኑ ሥርዓተ ኦሪትን ሊፈጽም ተገረዘ፡፡ ግዝረትን በስምንተኛው ቀን መፈጸሙ፣ በተወለደ በአርባ ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ መሔዱ ሕገ ኦሪትን ሊያጸና፣ ሊፈጽም፣ ምሳሌውን በአማናዊው ሊተካ እንጂ ኦሪትን ሊሽር ላለመምጣቱ እማኝ ምስክር ነው፡፡ የተሻረ ነገር መታሰቢያ የለውም የተፈጸመ፣ በምሳሌና በትዕምርታዊነት የተወከለ ግን ጥንተ ታሪኩን፣ ትንቢቱን ጠይቀን ምሳሌውን ከትርጓሜ መጻሕፍት እንረዳለን፡፡

 

ግዝረት አይሁድ የአብርሃም ልጅ መሆናቸውን ማረጋገጫ ማኅተም ነው፡፡ በሕግና በሥርዐት የሚመሩ መሆናቸውን አንድ አምላክ ማመናቸውን የገለጡበት ነው፡፡ አይሁድ በግዝረት የአብርሃም ልጅነታቸውን እንዳረጋገጡ፣ ክርስቲያኖችም በጥምቀት የሥላሴ ልጅነታቸውን ያረጋግጣሉ፡፡ ይህም የሚሆነው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጥምቀት እንጂ መገረዝ፣ አለመገረዝ አይጠቅምም፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግዝረት በፍቃድ እንጂ እንደ አይሁድ እኛም የአብርሃም ልጆች እንድንባል የምንገረዝ አይደለም፡፡

 

ለእኛ ለክርስቲያኖች ከሥላሴ በመንፈስ ቅዱስ መወለድ እንጂ መገረዝ የአብርሃም ልጆች አያሰኘንም፡፡ አለመገረዝ እንደማይጠቅም ቢያውቅም ጌታችን መገረዝ ያስፈለገው ሕገ ኦሪትን ለመፈጸም ሲሆን በእኔ ግን ምስጢረ ጥምቀትን ፈጽሜ አድናችኋለሁ ሲለን ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የማይጠቅምና ለነገረ ድኅነት የማያበቃ ነገር ቢያጋጥመን እንኳ በጥበብና በማስተዋል እንድናደርገው ሲያስተምረን ነው፡፡ ሥርዐተ ኦሪታችንን ስላፈረሰብን ለሞት አበቃነው ብለው ምክንያት እንዳያገኙና ይህንን ስበብ አድርገው ከነገረ ድኅነት ተለይተው እንዳይቀሩ የሚያደርጉትን በማድረግ፣ የሚወዱትን በመውደድና አብሯቸው የሥርዐታቸው ተካፋይ በመሆን በፍቅር ስቦ ወደ አማናዊው ድኅነት፣ ወደ ጥምቀትና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ወደማመን መልሷቸዋል፡፡

 

የመምህሩን አሰረፍኖት የሚከተለው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በደርቤን በሚያስተምርበት ወቅት ጢሞቴዎስ ሲከተለው መገረዝ አለመገረዝ ጥቅምም ጉዳትም እንደሌለው እያወቀ የገዘረው በዙሪያው ብዙ አይሁድ ስለነበሩ እነርሱን ላለማስከፋትና ላለማስደንበር መሆኑን ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “.. የኦሪት ሕግ ለማዳን ብቁ አለመሆኗን እየደጋገመ በድፍረት ይሰብክ የነበረው መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ እንኳ አይሁድን ላለማስደንበር ሲል ሥርዐተ ኦሪትን ይፈጽም ነበር፡፡” /1978፣ 29/ በማለት ገልጸዋል፡፡

 

ግዝረት ለእስራኤል ከአብርሃም ለመወለዳቸው ምልክት ብቻ ሳይሆን የአብርሃምን ሃይማኖት ለመያዛቸውም መታወቂያ ነበረች፡፡ ጌታችንም ምንም እንኳ የባሕርይ አምላክ ቢሆን በሥጋ የአብርሃም ልጅ ነውና የአብርሃም ልጅነቱን የአብርሃምን ሃይማኖት ማጽናቱን ለማስረገጥ ግዝረትን ፈጸመ፡፡ አንድም በግዝረት ደም ይፈስሳለና አብርሃም በዘጠና ዘጠኝ ዓመቱ በመገረዝና ደሙን በማፍሰስ አበ ሰማዕታት ተብሏልና ግዝረት የሰማዕትነት ምሳሌም ነው፡፡

 

ጥር ስድስት በሚነበበው ስንክሳር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አረጋዊ ዮሴፍን ሕፃኑን የሚገርዝ ባለሙያ ፈልጎ እንዲያመጣ እንደነገረችው፣ አረጋዊውም ባለሙያውን ፈልጎ እንዳመጣ ይናገራል፡፡ ባለሙያውም ሕፃንን በደምብ ያዙልኝ ብሎ ለመግረዝ ሲሰናዳ ባለሙያ ሆይ ደሜ ሳይፈስ መግረዝ ትችላለህን ብሎ እንደጠየቀው፣ ከስቅለቱ በፊት ደሙ እንደማይፈስ እንዳስተማረው፣ በዚህም ምክንያት ለመግረዝ የመጣው ባለሙያ፣ አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን አምኖ እንደሰገደለት ለመግረዣ ያዘጋጀው ምላጭም እሳት ላይ እንደተጣደ ቅቤ መቅለጡን ይተርካል፡፡

 

በመቀጠልም ክርስቶስ ዘር ምክንያት ሳይሆነው እንደተፀነሰ፣ ማኅተመ ድንግልናዋን ሳይለውጥ እንደተወለደ እንደ ነቢዩ ሕዝቅኤል “ሳይከፈት ገብቶ ሳይከፍት እንደወጣ” ስለት ምክንያት ሳይሆነው፣ በግዝረት ምክንያት ደም ሳይፈስ በተአምራት ተገረዘ፡፡ በአጠቃላይ ግዝረት በኦሪት የአብርሃም ልጅነትን፣ የአብርሃምን ሃይማኖት መያዝን ማረጋጋጫ ማኅተም ሲሆን በሐዲስ ኪዳን በጥምቀት ተተክቷል፡፡ ለአማናዊው ግዝረት /ለጥምቀት/ ምሳሌ በመሆኑም በሥራ የአብርሃም ልጅነትን፣ በእምነት የሥላሴ ልጅነትን አግኝተንበታል፡፡ ወርደህ ተወልደህ፣ በነፍስ በሥጋ፣ ከተቆራኘን ባለጋራ አድነን ብለን የተጣራነው ተሰመቶ፣ ሥርዓተ ኦሪትን ፈጽሞ ወደ ሥርዓተ ሐዲስ የሚያሸጋግረን መሆኑን ያመንበት፣ በጥምቀቱ ቦታ በዮርዳኖስ የተቀበረው የባርነታችን ደብደቤ የሚቀደድ መሆኑን በምሳሌ ያወቅንበት ግዝረት ነው፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1688-2015-01-13-06-00-29