የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም

እንዳለ ደምስስ

01 abune fil 1 የኢሉባቦርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሥርዓተ ቀብር ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ምእመናን በተገኙበት ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ተፈጽሟል፡፡

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከዋዜማው ጀምሮ ሊቃውንቱ ቅኔ ማኅሌት፤ ቀሳውስቱ ሰዓታት በመቆም፤ ንጋት ላይ ሥርዓተ ቅዳሴው በቅዱስ ፓትርያርኩ እየተመራ ተከናውኗል፡፡02abune fil

በዐውደ ምሕረት ጸሎተ ፍትሐት እንደተከናወነ ከቅዱስ ላሊበላ እንዲሁም ከአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት በመጡ ሊቃውንት ቅኔ ቀርቧል፡፡
ቅዱስነታቸው በሰጡት ቃለ ምእዳን ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ባሳለፏቸው ዘመናት ሁሉ ለሀገራቸውና ለቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ አባቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ መንፈሳዊ፤ ቅን፤ ታዛዥና ጸሎተኛ የነበሩ ሲሆን ለሌላው አርአያ በመሆን ሁልጊዜ የሚጠቀሱ አባት ናቸው ብለዋል፡፡

በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የወላይታ ኮንታ ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካነት የብፁዕነታቸው የሕይወት ታሪክ ተነቦ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡

የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አጭር የሕይወት ታሪክ፡-

 ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከአባታቸው ከአቶ ፈለቀ ለውጤ ከእናታቸው ወ/ሮ አዛልነሽ ሙሉ በ1928 ዓ.ም በወሎ ክፈለ ሀገር በላስታ ቡግና አውራጃ ሠራብጥ ካህናተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ተወለዱ፡፡
 መምሬ ኃይሉ ከሚባሉ መምህር ንባብ፤ ዳዊት፤ ሰዓታት እና አምስቱን አእማደ ምሥጢር ተምረዋል፡፡
 ወደ ገነተ ማርያም በመሄድ መሪ ጌታ ኃይለ ማርያም ከሚባሉ መምህር ፀዋትወ ዜማ፤ በአርካ አቦ ቤተ ክርስቲያን ከአለቃ ኢሳይያስ ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡
 በደሴ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ መነኮሳት ተምረዋል፡፡
 ዋልድቢት /ገዳሚት/ ከተሰኘው ገዳም ገብተው ለተወሰኑ ዓመታት አገልግለዋል፡፡
 ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከመምህር ወልደ ሰንበት ሰዋስወ ቅኔን ተምረዋል፡፡
 ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ገዳም በመሄድ ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ዲቁና ተቀብለዋል፡፡
 ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ገዳም በመሄድ ምንኩስናን ተቀብለዋል፡፡
 ማዕረገ ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ሚካኤልተቀብለዋል፡፡
 ኅዳር 4 ቀን 1987 ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ዘኢሉባቦር ተብለው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ እድ ተሾሙ

አገልግሎት፡-

 የመድኃኔዓለም በጎ አድራጎት እየተባለ ይጠራ የነበረውን ማኅበር አደራጅተዋል
 የተማሪዎች አንድነት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን አቋቁመዋል
 በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል
 በምግባረ ሠና የአረጋውያን አባቶችና እናቶች መረዳጃ ማኅበርን በማቋቋም በርካታ ችግረኞች እንዲረዱ አድርገዋል
 በሐውልተ ስምዕ መድኃኔዓለም ገዳም የገዳሙ መምህርና አስተዳደሪ ሆነው አገልግለዋል
 የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት አገልግለዋል
 የመንበረ ጸባዖት ቅድሰት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳደሪ ሆነው አገልግለዋል
 የጠቅላይ ቤተ ክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ሆነው ሰርተዋል
 የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል
 የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል
 ወደ ኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሲመደቡ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 217 የነበሩ ሲሆን ባደረጉት የማስተባበር ሥራ በአሁኑ ወቅት 320 አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ደርሰዋል፡፡
 የፈለገ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ገዳም ሆና እንደታገለግለ አድርገዋል፡፡
 ከግንቦት 22 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ የጋምቤላን ሀገረ ስበከት ደርበው እዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው አገልግለዋል
 ከሐምሌ 24 ቀን 1998 ዓ.ም ጀምሮ የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ሙዚየምና የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሠርተዋል
 ከሚያዝያ 21ቀን 2002 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው አገልግለዋል
 ብፁዕነታቸው ለሰው የሚራሩ፤ ትሁትና ደግ የነበሩ ሲሆን በርካታ የተቸገሩ ልጆችን በማሳደግ፤ በማስተማር ለሀገረ ለወገን የሚጠቅሙ ልጆችን አፍርተዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሲታከሙ ቆይተው ነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

እግዚአብሔር የብፁዕነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ነፍስ ጋር ይደምርልን፡፡ አሜን፡፡

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1976-2015-09-01-18-05-21