በሐዋሳ ማረሚያ ቤት አዲስ አማንያን ተጠመቁ

የካቲት 2 ቀን 2008 ዓ.ም

ከሐዋሳ ማእከል

001hawassat በሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በሐዋሳ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙ 76 አዳዲስ አማንያን የሕግ ታራሚዎች ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነት ማግኘታቸውን የሐዋሳ ማእከል ገለጸ፡፡


ከአዳዳስ አማንያኑ መካከል 21 የሚሆኑት በ2007 ዓ.ም በነሐሴ ወር የፍልሰታ ጾም መጨረሻ ዕለት የተጠመቁ ሲሆን በቅርቡም ጥር 12 ቀን 2008 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማእከል፣ በግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ እና በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል መራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት አስተባባሪነት ሲያስተምሯቸው የነበሩ 55 ኢ-አማንያን የሕግ ታራሚዎች ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና አግኝተዋል፡፡


በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ጉባኤ ቆሞስ አባ ሀብተ ማርያም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከዚህ በፊት በማረሚያ ቤቱ በዐበይት በዓላት ላይ በመገኘት ቡራኬና ቃለ ምእዳን ሰጥተው እንደነበረ አስታውሰው ኢ-አማንያኑ አስፈላጊውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተከታትለው መጠመቃቸውና የሥላሴ ልጅነት ማግኘታቸውን በማስመልከት ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡ ይህ የተቀደሰ አገልግሎትም ወደፊት በስፋት መቀጠል እንዳለበትና ሀገረ ስብከቱ በሚያስፈልገው ሁሉ እንደሚተባበር ብሎም ቋሚ ካህን እንደሚቀጥርላቸው ጨምረው ገልጸዋል፡፡


የአብዛኛዎቹ የሕግ ታራሚዎች ንስሐ አባት የሆኑት ቀሲስ ደረጀ ሚደቅሶ ከታራሚዎቹ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና አገልግሎቱን በተመለከተ ቅዳሜና እሁድ፣ የበዓላት ቀን እንዲሁም ልዩ ጉባኤ እየተዘጋጀላቸው ሲማሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ታራሚዎቹ ቃለ ወንጌል ተምረው ንስሐ እየገቡ እንደሆነና ወደፊትም በዚሁ መንገድ እንዲቀጥሉ በየጊዜው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን አስመልከቶ ሲናገሩም የማረሚያ ቤት አገልግሎት እጅግ በጣም አስደሳች እንደሆነና ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡


የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል የመራሔ ድኅነት ሰንበት ትምህርት ቤት ጸሐፊ የሆኑት ወጣት ቴዎድሮስ ደመቀ በበኩላቸው ሰንበት ትምህርት ቤቱ ይህንን አገልግሎት አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ተናግረው ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ እስከ ምእመን ትኩረት በመስጠት አገልግሎቱን ማጠናከርእንደሚገባ ገልጸዋል፡፡


የሕግ ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤቱ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀላቸው የጸሎት ቤት ጸሎት በማድረሰ፣ እርስ በርሳቸው በመማማር የገቢ ማስገኛ ሥራዎችንም በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/2071-2016-02-10-12-44-21