በሰንበት እና በዘወትር ቅዳሴ አገልግሎት ከምዕመናንም ዘንድ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ (COVID-19 Church Re-opening Guidelines)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
COVID-19 በመባል የሚታወቀው ተላላፊና ቀሳፊ በሽታን ለማስወገድ ብቸኛው አማራጭ ጥንቃቄ መውሰድና የጋራ ኃላፊነትን በጋራ መወጣት መቻል ነው። ከሚመለከተው ክፍል መመሪያ መቀበልና የተሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ያለንን አገልግሎት ስኬታማና ውጤታማ ያደርግልናል። በመሆኑም ጊዜው ከፈጠረው ችግር በመነሣት ሁላችን የአገልግሎቱ ተካፋይ እንድንሆን በማሰብ ሰበካ ጉባኤው ከዚህ በታች በዝርዝር የተጻፉትን መመሪያዎች አውጥቷል፤ ለተግባራዊነቱም የእናንተን ትብብር አጥብቆ ይሻል፦
በሰንበት እና በዘወትር ቅዳሴ አገልግሎት ላይ የሚሰጥ አገልግሎትን በተመለከተና ከምዕመናንም ዘንድ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ፦

፩) የሚያስላችሁ ከሆነ፣ የትንፋሽ ዕጥረት ወይም የመተንፈስ ችግር ከገጠማችሁ፣ ትኩሳት ካለባችሁ፣ ብርድ ብርድ ካላችሁ፣ በተደጋጋሚ የሚያንቀጠቅጥ ብርድ ከያዛችሁ፣ የጡንቻ ሕመም፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ የማጣጣም ወይም የማሽተት ስሜት ካጣችሁና በኮቪድ 19 በሽታ ለተያዘ ታማሚ ከተጋለጣችሁ ለእናንተም ሆነ ለሌሎች ጤንነት ስትሉ ከቤት እንድትቆዩ እንጠይቃለን።

፪) ምናልባት ከምትሠሩበት መሥሪያ ቤት፣ ከምትውሉበት ቦታ፣ ከምትኖሩበት መኖሪያ አካባቢና ውስጣችሁ ከሚሰማችሁ ሁኔታ አንፃር የእናንተ መምጣት ስጋት ሊሆን ይችላል ብላችሁ ካሰባችሁ መምጣት የለባችሁም።

፫) ለቅዳሴ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት የሚችሉት ተረኞች የሆኑና በሰበካ ጉባኤው አማካኝነት የስም ዝርዝራቸው ተጽፎ እንዲመጡ የታዘዙት ብቻ ናቸው።

፬) በአዘቦት ቀን ቅዳሴ የመጣችሁና ያስቀደሳችሁ ሰዎች ያለውን ጫና ለመቀነስና ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በእሑድ ዕለት ቅዳሴ ላይ ባለመምጣት ልትተባበሩን ይገባል።

፭) ለቅዳሴም ሆነ ለሌሎች ሥርዓት የምትመጡ ምዕመናን ከአስተናጋጆች በሚሰጣችሁ የጫማ ላስቲክ ጫማችሁን ይዛችሁ እንድትገቡ ትጠየቃላችሁ። ልብሳችሁም ሆነ ጫማችሁ ከእናንተ መለየት የለበትም፤ ወደ ቤታችሁም ስትሄዱ ልብሳችሁንም ሆነ ያመጣችሁትን ዕቃ ይዛችሁ መመለስ አለባችሁ።

፮) አስተናጋጆች በሚሰጧችሁ ቦታ ላይ እንጂ እናንተ በወደዳቻሁት ቦታ ላይ መቀመጥ የለባችሁም፤ ቅዳሴ ከመጀመሩ ከ (7:00 A.M.) በፊት ብትደርሱ ለአገልግሎታችን ስኬት ጠቃሚ ስለሚሆን በጊዜ እንድትመጡ ትጠየቃላችሁ።

፯) ከሚታቀፍና የእናንተን ጥበቃ ከሚያስፈልገው ሕፃን በስተቀር በቤተ መቅደሱ ውስጥ መቀመጥ የምትችሉት ምልክት በተደረገበት ቦታ ላይ ለብቻችሁ በመሆን ነው። በተዘጋጀው በእያንዳንዱ መቀመጫ ላይ ከአራት ሰዎች በላይ መቀመጥ አይቻልም። ከፊተኛው ተርታ ካለው ወንበር ላይ አራት ሰው ይቀመጣል፤ ቀጣዩ ሁለት ወንበር ይዘለልና አራተኛው ወንበር ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ አራት ሰዎች ይቀመጣሉ።

፰) ለእያንዳንዳችን ጥንቃቄ ሲባል በአገልግሎት ጊዜ በተለይም በቅዳሴ ሰዓት አፋችን ላይ ጭምብል (MASK) ማድረግ ይጠበቅብናል። ይኽም አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን የከተማው ከንቲባ መመሪያ ሰጥቶበታል። ይኽን በማድረጋችን እኛንም ሆነ ሌሎችን አደጋ ላይ ከመጣል እናድናለን።

፲) ሕፃናት ልጆቻችሁ በየትኛውም የአገልግሎት ሰዓት ከእናንተ መለየት የለባቸውም። ሕፃናቱ ወደ መጸዳጃ ቤትም ሆነ ወደ ውጪ መውጣት ቢያስፈልጋቸው ወላጆች አብራችሁ ሄዳችሁ አብራችሁ መመለስ ይጠበቅባችኋል። እንደዚህ በማድረጋችን መንግሥት ያወጣውን መመሪያና የሚኒሶታ የጤና ማዕከል እንዲተገበር የሚፈልገውን ሕግ ማስፈጸም እንችላለን፤ የእኛንም ጤንነት በአግባቡ እንጠብቃለን።

፲፩) የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ ዲያቆናትና አስተናጋጆች መመሪያ በመስጠት ወደ ቅዱስ ቁርባን የሚቀርቡ ቆራቢዎችን ርቀታቸውን ጠብቀው በቅደም ተከተል እንዲቀርቡ ያደርጋሉ፤ እርስዎም በሚሰጥዎ መመሪያ ተጠቅመው ኃላፊነትዎን ሊወጡ ይገባል።

፲፪) በቅዱስ ቁርባን አገልግሎት ጊዜ ከፊትዎ ቀድሞ ካለው ሰው ጋር ተራርቀው መቆም ስላለብዎ በምንጣፉ ላይ በየስድስት ጫማ ርቀት በተለጠፈው ምልክት ላይ ሆነው ተራዎን ይጠባበቁ።

፲፫) ልጆች ወደ ቅዱስ ቁርባን ሲመጡ በተመሳሳይ ርቀታቸውን መጠበቅ ስለሚገባቸው ወላጆች በተቻለ መጠን ልጆቻችሁን በማግባባትና በመምከር ሰልፉንና ተራቸውን ጠብቀው እንዲጠቀሙ ማድረግ ይኖርባችኋል፤ ለአስተናጋጆችም መታዘዝ እንዳለባቸው ልትነግሯቸው ይገባል።

፲፬) ልጆች በቅዳሴ ላይ ካስቸገሯችሁና ከቤተ መቅደስ መውጣት ካስፈለጋችሁ አስተናጋጆችን በመጥራት ለጥያቄዎቻችሁ መልስ ታገኛላችሁ።

፲፭) ጸበል ለመጠጣት ግፊያ እንዳይሆን ቅዳሴው እንዳበቃ ዲያቆናት (አስተናጋጆች) የቅዳሴ ጸበል ይዘው በተቀመጣችሁበት ቦታ ያዳርሳሉ፤ የተጠቀማችሁበትን የጸበል መጠጫም የምትጥሉበት ዕቃ ያቀርቡላችኋል።

፲፮) ከአገልግሎቱ ፍጻሜ በኋላ ወደ ውጪ ለመውጣት (ወደ ቤት ለመሄድ) ስትዘጋጁ የአስተናጋጆችን መመሪያ በመከተል እና እናንተም ርቀታችሁን ጠብቃችሁ በተራ መውጣትን አትዘንጉ።

፲፯) የመግቢያው በር ዋናው ትልቁ በር እንዲሆንና አገልግሎት ካለቀ በኋላ ግን ለመውጫ የምንጠቀምባቸው በሮች ካህናት በሚገቡበት ሁለት ተካፋች በር ያለውን፣ በጤና ቢሮ በኩል ያለውን ትንሽ በር እና እንደ አመቺነቱ የመግቢያውን ትልቁን በር በመሆኑ ያለውን ግፊያ ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት አስተናጋጆች የሚሉትን ስሟቸው።

፲፰) በቤተ መቅደስ ውስጥ የምታስቀድሱ እናቶች ወይም እኅቶች በሙሉ ለመውጫ የምትጠቀሙበት በር ካህናት በሚገቡበት ባለ ሁለት ተካፋች በር ያለውን ይሆናል። ምናልባት ግን ካህናትን ለማነጋገር፣ ሒሳብ ለመክፈል፣ ንዋያተ ቅድሳት ለመግዛት፣ ጽ/ቤት ለመድረስ፣ ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድና ለሌሎችም ተመሳሳይ ጉዳይ መቆየት ካለባችሁ እዚያው ባላችሁበት ቆይታችሁ ሌሎቹ ከወጡ በኋላ ትስተናገዳላችሁ።

፲፱) ከቅዳሴ በኋላ አዳራሽ ውስጥ ምንም ዓይነት መስተንግዶ አናደርግም። ስለዚህም አገልግሎት እንዳበቃ ቀጥታ ወደየቤታችን መሄድ ይኖርብናል። ምናልባት ሁላችንም በአካል ሳንተያይ በርካታ ሳምንታት ስለሆነን ስንገናኝ መጨባበጥና መተቃቀፍ እናስባለን። ሆኖም ግን ራሳችን ገትተን ሰላምታችን እጅ በመነሳሳት መሆን ይኖርበታል።

፳) በተቻለ መጠን ከሌሎች ሰዎች ጋር ዕቃ መቀባበልን አስወግዱ፤ የተጠቀማችሁበትን ማንኛውም ዕቃ ማስቀመጥም ሆነ መጣል ካለባችሁ ራሳችሁ በተገቢው ቦታ ላይ ማስቀመጥም ይሁን መጣል ይጠበቅባችኋል።

፳፩) የቤተ ክርስቲያን ክፍያ እና የዕድር ክፍያ ለመክፈል እንዲሁም ከንዋያተ ቅድሳት ሱቅ ዕቃ መግዛት የምትፈልጉ ከሆነ ርቀት ጠብቀው የሚቆሙበት መስመር ወይም ምልክት ስላለ በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንጠይቃለን። በተጨማሪም በየትኛውም ቦታ በእርስዎና በሌላው ሰው መኃል የስድስት ጫማ ያህል ርቀት መኖሩን በመገመት ጥንቃቄ ያድርጉ።

፳፪) በየክፍሉ ያለውን የሰው ብዛት ለመቀነስና መነካካትን ለማስወገድ ማንኛውም ምዕመን ለአገልግሎት ባልተመደበበት ክፍል ውስጥ እንዳይገባ ይመከራል።

፳፫) በቤተ ክርስቲያንም በር ላይ ሆነ በእያንዳንዱ የአገልግሎት መስጫ ክፍል የተለጠፉትን ማስታወቂያዎች አይታችሁ ተግባራዊ ማድረግን አትዘንጉ። ለምሳሌ አራት ሰዎች ብቻ እንዲገቡበት በተፈቀደ ቦታ ትርፍ ሰው መግባት አይኖርበትም።

፳፬) በማንኛውም የአገልግሎት መስጫ ክፍል (ቢሮዎች) ከሁለት ሰው በላይ መግባት አይፈቀድም። በጽ/ቤት የተለያየ አገልግሎት እንዲፈጸምላችሁ የምትመጡ ሰዎች ከቢሮ ውጪ ባለው መቀመጫ ላይ ወረፋችሁን በመጠበቅ ትስተናገዳላችሁ።

፳፭) የክርስትና ወረቀት (ሰርተፊኬት) ሕፃኑ/ሕፃንዋ በተነሡበት ቀን ስለሚዘጋጅላችሁ ሳትቀበሉ ወደ ቤታችሁ እንዳትሄዱ ይመከራል።

፳፮) መኪና ደርባችሁ አታቁሙ፤ የመኪና አስተናጋጆችን ትዕዛዝም በመቀበል ተባበሩ።

፳፯) ቤተ ክርስቲያን ከመግባታችሁ በፊት መኪናችሁ መቆለፉንና በመኪናችሁ ውስጥ ሊታይ የሚችል ገንዘብ፣ ሰዓት፣ ቦርሳ እና ሌሎችም ተመሳሳይ ዕቃዎች ያለመኖሩን ያጣሩ። ይኽን በማድረግዎ ንብረትዎን ከአደጋ መጠበቅ ይችላሉ፤ መኪናችሁን ለመዝረፍ የመጣውም ሰው በCOVID-19 ቫይረስ የተጠቃ ከሆነ ለሕይወት አደጋም በቀላሉ ተጋላጭ ስለምትሆኑ የእናንተንም ሆነ የቤተሰቦቻችሁን ሕይወት ለማዳን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል።

፳፰) ወደ እናንተ የሚተላለፈው መመሪያ ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለመላው ምዕመናን የሚጠቅም በመሆኑ መመሪያውን ተቀብላችሁ ተፈጻሚ ማድረግ ይጠበቅባችኋል።

፳፱) ሰበካ ጉባኤው ከላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች ውጪም ለሥራው አመቺ ነው የሚለውን ጉዳይ እንደ ሁኔታው ተፈጻሚ ያደርጋል፤ የእናንተንም ትብብር ይጠይቃል።

፴) ለመግባትም ሆነ ለመውጣት ርቀት መጠበቅ ስለሚያስፈልገን ሁኔታዎች እኛ ባሰብነው ፍጥነት ሊሄዱ ስለማይችሉ መዘግየት እንደሚኖር ከወዲሁ አስቡበት።

ከዚህ በላይ የተገለጸው መመሪያ የወጣውና ምዕመናን መመሪያውን ተከትለው እንዲተገብሩት ጥያቄ ያቀረብነው በምንኖርበት ስቴት የሚኒሶታ አገረ ገዢ COVID-19 በመባል የሚታወቀውን ቀሳፊ በሽታ ለመከላከል ያወጣውን መመሪያ እና በሚኒሶታ የጤና ማዕከል MDH ሞያዊ ጥናቱን በመጠቀም ተግባራዊ እንዲሆን የነደፈውን መርሐ-ግብር በመከተል ነው። መመሪያው እንደሚፈቅደው ጥንቃቄ ማድረግና መፈጸም ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው።
ይኽን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ ለምትወስዱት ኃላፊነት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ስም ከወዲሁ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
ልዑል እግዚአብሔር የመጣውን መቅሰፍት ይመልስልን፤ የምሕረት እጆቹንም ይዘርጋልን።
የሥሉስ ቅዱስ ረድኤት በረከት አይለየን።
መግለጫ፦
ይኽ መመሪያ እስከሚሻሻል ድረስ የጸና ይሆናል። መመሪያው ጊዜው ያመጣው COVID-19 በመባል የሚታወቀው ተላላፊ በሽታ ከተወገደ በኋላ እንደ ወትሮው ማንኛውም ዕንቅስቃሴ ሲፈቀድ ውድቅ ይሆናል።