በዓታ ለማርያም

ታኅሣሥ 3 ቀን 2007 ዓ.ም.

በዲ/ ታደለ ፈንታው

በዓታ ለማርያም ይህ ዕለት የልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መቅደስ የምትሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበትን ዕለት የምናስብበት ነው፡፡ የአምላክ እናት ከእናት ከአባቷ ቤት ተለይታ እግዚአብሔር ወደመረጠላት ሥፍራ ወደ ቤተ መቅደስ ገባች፡፡ ዕድሜዋ ሦስት ዓመት ነበር፡፡

 

አባታችን ኢዮብ እንደተናገረው “ሁሉን ማድረግ እንደሚቻለው፤ በባሕርይው የሚሣነው እንደሌለ አሳቡንም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል” /ኢዮ 42፡2/ አውቀን ለተጠራንበት ዓላማ መልስ መስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡

 

እግዚአብሔር ሲጠራ፣ ልዑል ሲናገር የዕድሜ ጉዳይ፣ የጾታ ጉዳይ፣ የዜግነት ጉዳይ፣ የአቅም ጉዳይ፣ የጊዜ ጉዳይ፣ የስልጣን ጉዳይ፣ የእውቀት ጉዳይ፣ ሥፍራ አይገኝላቸውም፡፡ ጥያቄ ውስጥም የሚገቡ አይደሉም፡፡ እኛ ግን እንኳንስ ራሳችንን ለሕይወት ዘመን አገልግሎት ልንሰጥ ይቅርና በተወሰነ ሰዓት ለሚሆነው መውጣት መግባት እየተቸገርን ነው፡፡ አገልግሎት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍጹም ፍቅር የምንገልጽበት በሕይወታችንም ተጠቃሚ የምንሆንበት ምሥጢር ነው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ፡-

 

ጥንተ ነገር
አባቷ  ቅዱስ ኢያቄም እናቷ ቅድስት ሐና እንደ መጽሐፍ ቃል፥ እንደ አባቶች ሥርዓት፥ እንደኦሪቱ ሕግ  በእግዚአብሔር ትእዛዛትና ሕግጋት ሁሉ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ፍጹም ጻድቅ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ስዕለት ተሳሉ፤ እግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪዋን የምትወልድ ከመልኳ ደም ግባት ይልቅ የልቡናዋ ደም ግባት ደስ የሚያሰኝ፤ አሸናፊ የሚሆን የእግዚአብሔር አብን የባሕርይ ልጅ በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ነፍስ በድንጋሌ ኅሊና ጸንሳ የወለደች የብርሃን እናትን ወለዱ፡፡

 

ሊቃውንቱ “ማኅጸነ ሐና ሕያው ሰማያተ ገብረ”፤ ሕያው የሆነ የሐና ማኅጸን ሰማይ የተባለች ቅድስት ድንግል ማርያምን አስገኘ በማለት ዘመሩ፡፡ እግዚአብሔር ስጦታው ድንቅ ነው የለመኑትን ሳይሆን ሰዎች ፈጽሞ ሊያስቡት ቀርቶ ሊገምቱት የማይቻለውን ስጦታ ይሰጣል፡፡

 

የአባታቸውን የነቢዩን ዳዊት ቃል ቃላቸው አድርገው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ደጅ ይጠኑ የነበሩ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና  “እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ” /መዝ 5፡7/ በማለታቸው የጸሎታቸው ውጤት ብቻ ሳትሆን የእግዚአብሔር ስጦታ የምትሆን፣ ፍጥረት ሁሉ ተሰብስቦ ቢመዘን የአንዲቱን  የጸጉሯን ዘለላ  የማያክል ቅድስት ድንግልን ወለዱ፡፡  ከእግዚአብሔር የተቀበሉአትን ቅድስት ለእግዚአብሔር ሊሰጡአት ስዕለት ተስለው ነበር፡፡

 

 አስቀድሞ በቤተ እስራኤል ዘንድ ደናግል በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚቀመጡበት ሥርዓት አልነበረም፡፡ በርግጥ በኦሪቱ ነቢይት በአፍአ እንደነበረች ተገልጧል፤ ነገር ግን የእመቤታችን ወደቤተ መቅደስ መግባትና የነቢይት ወደ ቤተ መቅደስ መግባት የተለየ ነው፡፡ በዓይነትም በመጠንም የሚነጻጸር አይደለም፡፡

 

ቅድስት ድንግል ማርያም ከሦስት ዓመቷ እስከ አሥራ አምስት ዓመቷ ለአሥራ ሁለት ዓመታት በቤተ መቅደስ ቆየች፡፡ ሕያው መቅደስ፥ እመቤትና የአምላክ እናት የምትሆን ቅድስት ድንግል በእነዚህ ዓመታት መላእክት ምግቧንና መጠጧን እያመጡ ከዜማው ጣዕም የተነሣ አጥንትን የሚያለመልም የመላእክትን ዝማሬ እያዳመጠች በቤተ መቅደስ ኖረች፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን “ንጽሕተ ንጹሐን ከወይና ከመ ታቦተ ዶር ዘሲና ውስተ ቤተ መቅደስ ነበረት በድንግልና ሲሳያ ኅብስተ መና ወስቴሃኒ ስቴ ጽሞና” እያሉ አዲስ ቅኔን ተቀኙላት፡፡  


የበዓሉ ትርጉም በዘመኑ ለምንገኝ ክርስቲያኖች
እግዚአብሔር በማንኛውም የዕድሜ ጣራ ሥር የሚገኝ ክርስቲያንን እንደሚፈልግ የተመለከትንበት ዕለት ነው፡፡ በአቅማችን እንድንነጋገር ስለሚያስፈልግ እንጂ የበዓሉ ትርጉም ከዚህም በላይ ላይ ነው፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስንኖር ልንከተለው የሚገባ ቅድስና በእግረ ሥጋ ለምንመላለስ ወገኖች ያለው አስተማሪነት የጎላ ነው፡፡ በሕይወት ዘመን በእግዚአብሔር ቤት ለመኖር  እንፈልግ ዘንድ ፣ ሕይወታችንን በፍጹም ቅድስና እንመራ ዘንድ መቅደስ የተባለ ለእግዚአብሔር ማደሪያነት የተመረጠ ሰውነታችን ከኃጢአት ሁሉ እንጠብቅ ዘንድ የተማርነበት በዓል ነው፡፡

 

ይልቁንም በመከራ ጊዜ ከንፈሮቻችን የተናገሩትን ስዕለት ለእግዚአብሔር መፈጸም እንደሚገባን እግዚአብሔርን የሚያስደስተው ፍጹም ስጦታ ራሳችንን አሳልፈን ከመስጠት የበለጠ እንደሌለ ልንረዳ የሚገባን መሆኑን በዓሉ ያስተምራል፡፡ ልመናዋ ክብሯ የልጇ ቸርነት በሁላችን ላይ ይደርብን፡፡ 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1644-2014-12-12-20-30-51