በአንድ ባለ ሀብት የተሠራው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ተመረቀ

ኅዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም.


በእንዳለ ደምስስ

haro 01 በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሶዶ ዳጪ ወረዳ በአንድ ባለ ሀብት የተሠራው የሀሮ ቅዱስ በዓለ ወልድ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትየጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኅዳር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ተመረቀ፡፡


ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን፤ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኑን ዙሪያ የግንብ አጥር፤ ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የእንግዳ ማረፊያ ቤት ለመገንባት ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀ ሲሆን፤ ሙሉ ወጪው የተሸፈነው ቢትወደድ ባሕሩ አብርሐም በተባሉ ባለ ሀብት ነው፡፡


haro 02 ቅዱስ ፓትርያርኩ በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ባለ ሀብቱ ያደረጉትን በጎ ሥራ አድንቀው “እግዚአብሔር በሰጣቸው ሀብት ተጠቅመው ለትውልድ የሚተርፍ መንፈሳዊ ሥራ የሚሠሩ በርካታ ሰዎች ያስፈልጉናል” ብለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንም ገዳም እንዲሆን በመወሰን የሀሮ ቅዱስ በዓለ ወልድ ገዳም በሚል ገድመውታል፡፡


የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በበኩላቸው “ሶዶ ዳጪ በሀገረ ስብከታችን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሌሎች እምነት ተከታዮች የሚገኙበት በመሆኑ የአካባቢውን ምእመናን እየፈተነ ይገኛል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ይህንን ቤተ ክርስቲያን ባለሀብቱ በመሥራታቸው ምእመናንን ከተለያዩ ኑፋቄዎች ለመጠበቅ ያግዘናል” ብለዋል፡፡


በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአካባቢው ምእመናን የቤተ ክርስቲያኑ መሠራት የሚኖረው አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑ በመግለጽ፤ እምነታቸውን አጠንክረው መያዝ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡


በባለ ሀብቱ ከዚህ በፊት የአኖ ሁዳድ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ገዳም እና በግራኝ አሕመድ ወረራ ወቅት ተቃጥላ ባድማ ሆና የቆየችውን የኬሮኒ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን መሳነጻቸው ይታወቃል፡፡

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1608-2014-11-20-06-39-00