የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደብረ ሊባኖስ ገዳም ይካሔዳል

 

ኅዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

hawire h 003 ማኅበረ ቅዱሳን ለ7ኛ ጊዜ ያዘጋጀውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ታኅሣሥ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም እንደሚያካሒድ የማኅበሩ ምክትል ዋና ጸሐፊና የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ አቶ ግርማ ተሾመ ገለጹ፡፡


በርካታ አድባራትና ገዳማት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር እንዲካሔድላቸው ለማኅበሩ ተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም አንዱ መሆኑን የገለጹት አቶ ግርማ፤ በ2006 ዓ.ም. ለማካሔድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ቅድሚያ የጠየቁ አድባራትና ገዳማት በመኖራቸው ወደ 2007 ዓ.ም. ሊሸጋገር እንደቻለ አስረድተዋል፡፡


hawire h 001 መርሐ ግብሩን ማካሔድ ያስፈለገበት ዐብይ ምክንያት የገዳሙ አስተዳደርና ማኅበረ መነኮሳቱ በጠየቁት መሠረት ቢሆንም፤ ማኅበረ ቅዱሳን ገዳማት በብዝኀ ሕይወት የተጠበቁና ራሳቸውን ከዓለም ለይተው በጸሎት ለሚተጉ አባቶች ጸጥታ የሰፈነባቸው እንዲሆኑ ለማድረግ እንደ ምሳሌ ሊሆን ይችላል በማለት ከገዳሙ ጋር በመተባበር በብዝኀ ሕይወት ዙሪያ ፕሮጀክት ቀርጾ ከመስከረም 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ሥራዎች በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ በገዳሙ ዙሪያ ከተራራው የሚመጣውን ናዳ ለመከላከል፤ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት እንዳይከሰት የመከላከል፤ እንዲሁም ገዳሙን አገር በቀል በሆኑ ዛፎች ለመንከባከብና ሌሎችም የልማት ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የሚያበረታታ በመሆኑ ምእመናንም በገዳሙ ተገኝተው እየተከናወነ ያለውን እንዲመለከቱ ለማስቻል ጭምር መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡


የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴም ወደ ገዳሙ በመሄድ ከገዳሙ አስተዳደርና ከማኅበረ መነኮሳቱ ጋር ውይይት በማካሔድ፤ ርቀቱን ታሳቢ በማድረግ፤ ከትራንስፖርት፤ ከዘመናዊ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አከራዮች፤ ከወንበርና ድንኳን አቅራቢ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤ የምግብ አቅርቦቱን ዝርዝር በማውጣት የትኬት ዋጋ አጥንቶ አቅርቧል፡፡ በዚህም መሠረት የጉዞው ዋጋ ብር 210.00 /ሁለት መቶ ዐሥር ብር/ እንዲሆን ወስኖ የትኬት ሽያጩን ከጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በማሰራጨት ላይ መሆኑን አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡


የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም አስተዳደርና ማኅበረ መነኮሳት መርሐ ግብሩ የተሣካ ይሆን ዘንድ ጸሎት በማድረግ ላይ ሲሆኑ፤ ከሀገረ ስብከቱ ጀምሮ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች፤ እንዲሁም የመንግሥት አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ጉባኤው በታቀደለት መሠረት ለማካሔድ የገዳሙ አስተዳደር አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡


ለ7ኛ ጊዜ በሚካሔደው በዚህ የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ ሲሆን፤ ከምእመናን ለሚመጡ ጥያቄዎች በሊቃውንቱ ምላሽ የሚሰጥበት፤ ቃለ እግዚአብሔር የሚተላለፍበት፤ የገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት ዝግጅቶቻቸውን የሚያቀርቡበትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቁ ዝማሬዎች በመዘምራን የሚቀርቡበት ይሆናል፡፡


ምእመናን ትኬቱን በማኅበሩ ንዋያተ ቅድሳት መሸጫ ሱቆች፤ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኙ የማኅበሩ ማእከላት፤ በወረዳ ማእከላት፤ እንዲሁም በዋናው ማእከል ጽ/ቤት ማግኘት እንደሚችሉ፤ የትኬቱ ሽያጭም እስከ ኅዳር 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ብቻ እንደሚቆይ አስተባባሪው አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡ ምእመናንም ትኬቱን በመግዛት ከገዳሙ በረከት እንዲሳተፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1601-2014-11-18-05-35-45