ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፤ ከሴትም ተወለደ /ገላ. 4፣4/

ታኅሣሥ 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

xmas እግዚአብሔር አምላክ ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፈጠረ ዘፍ 1፡1 ሌሎች ፍጥረታት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጠሩ ሰውና መላእክት ግን መንግሥቱንና ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ተፈጠሩ፡፡

 

የሰው ልጅን /አዳምን/ ፈጥሮ የሚያስፈልገውን አዘጋጅቶ፣ ዕውቀትንና ሥልጣን ሰጥቶ፣ በጸጋ አምላክነትን ሾሞ፣ መመሪያ ሰጥቶ፣ በክብር እንዲኖር ፈቀደለት፡፡ በመጀመሪያው ዕለትና ሰዓት ከተፈጠሩት መላእክት መካከል በክብር ይልቅ የነበረው ሳጥናኤል /የኋላ ስሙ ዲያብሎስ / አምላከነት በመሻቱ ተዋርዶ ሳለ አዳምንም በተዋረደበት ምኞትና ፍላጎት እንዲወድቅ ክብሩን እንዲያጣ ከአምላኩም እንዲለይ አደረገው፡፡ እግዚአብሔርን፤ ጸጋውን፣ ሹመቱን፣ ወዘተ አጣ /ኃጥአ/፡፡ ኃጢአት የሚለው ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ የተወሰደ ነው፡፡

 

አዳም ከእግዚአብሔር በመለየቱና ክብሩን በማጣቱ ተጸጽቶ ንሰሐ በመግባቱ ለሥርየተ ኃጢአት የሚሆን መሥዋዕትም በማቅረቡ፤ እግዚአብሔር አምላክ ልመናውንና መሥዋዕቱን ተቀብሎ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ቃል ኪዳን ገባለት “መዓልትና ዓመታትን በዚህ ምድር ላይ ሠራሁልህ፡፡ ይኸውም እነርሱ እስኪፈጸሙ ድረስ በምድር ላይ ትኖርና ትመላለስ ዘንድ ነው፡፡ የፈጠረችህና የተላለፍካት ከገነት ያወጣችህና በወደቅህም ጊዜ ያነሳችህ ዳግመኛም አምስት ቀን ተኩል ሲፈጸም የምታድንህ ቃሌን እልክልሃለሁ” እንዲል ገድለ አዳም እግዚአብሔር ለአዳም ነገረው፤ አዳምም አምስት ቀን ተኩል የሚለውን ቃል ከእግዚአብሔር በሰማ ጊዜ የእነዚህን ታላላቅ ነገሮች ትርጓሜ ሊያስተውል አልቻለም፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር አምስት ቀን ተኩል ማለት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት መሆናቸውን ገልጾ አርያውና አምሳያው ለሆነው ለአዳም በቸርነቱ ተረጎመለት ያን ጊዜ እርሱንና ዘሩን ለማዳን እንደሚመጣ ተስፋ ሰጠው፡፡

 

አዳምም ይህንን ተስፋ ለልጆቹ አስተማራቸው፤ ልጆቹም ተስፋው የሚፈጸምበትን ጊዜ ለማወቅ በፀሐይ፣ በጨረቃና በክዋክብት /ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ይህንን አቆጣጠር ትጠቀምበታለች/ ዘመናትን እየቆጠሩ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ ያለውን አዳኝ ጌታ መወለድ በትንቢታቸው ይናገሩ ይጠብቁም ነበር፡፡ ከእነርሱም ውስጥ:-

 

1.ሱባኤ ሔኖክ፡- ሔኖክ ሱባኤውን ሲቆጥር የነበረው በአበው ትውልድ ሲሆን ሰባቱን መቶ ዓመት አንድ እያለ ቆጥሯል። በስምንተኛው ሱባኤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚወለድ ትንቢት ተናግሯል። አቆጣጠሩም ከአዳም ጀምሮ ነው። 8x700=5600 ዓመት ይሆናል። 5500 ዓመተ ዓለም ሲፈጸም ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተወለደ ያጠይቃል።

 

ትንቢቱም እንዲህ ይላል። “ስምንተኛይቱ ሰንበት ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅባት ሱባኤ ናት፡፡ ሰይፍም ለርሰዋ ይሰጣታል ታላቁ ንጉሥ የሚመሰገንበት ቤትም በርሰዋ ይሰራል፡፡ ምሥጋናውም ዘላለማዊ ነው፡፡” ሔኖክ 35፡ 1-2 ክፍል 91 በማለት ሲተነብይ መተርጉማን እንዲህ ይመልሱታል፡፡ ለርሰዋ ሰይፍ ይሰጣታል ማለቱ ጽድቅና ኩነኔ የሚታወቅበት ወንጌል ያን ጊዜ በዓለም ሁሉ ትሰበካለች ማለት ነው፡፡ የታላቁን ንጉሥ ቤት ይሠራል ማለቱ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመሰገንበት ቤተ ክርስቲያን ትሰራለች ማለት ነው፡፡ ምስጋናውም ዘላለማዊ ነው ማለቱ ደግሞ ሰውና መላእክት በአንድነት ሆነው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” እያሉ ዘወትር ያመሰግናሉ ማለት ሲሆን ስምንተኛይቱ ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠችበትን ዕለት ልደተ ክርስቶስ ናት ይሏታል፡፡

 

2.ሱባኤ ዳንኤል፡- ስለ ጌታችን ሰው መሆን ጊዜ ወስኖ ሱባኤ ቆጥሮ የተናገረው ዳንኤል ነው፡፡ የዳንኤል ሱባኤ የሚቆጠረው በዓመት ነው ፡፡ ዳንኤል ሰባው ዘመን በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ ተብሎ በኤርምያስ የተነገረውን ትንቢት እያስታዋሰ ሲጸልይ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በሰው አምሳል ተገልጾ እንዲህ ብሎታል፡፡ “እግዚአብሔር ልምናህን ሰምቶሃልና እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፡፡ አሁንም ነገሩን መርምር ራእዩንም አስተዋሉ ኅጢአት የሚሰረይበትን ቅዱሰ ቅዱሳን ጌታም የባህርይ ክብሩን ገንዘብ የሚያደርግበት ባለው ሰባው ሊደርስ ሊፈጸም ነው ብለህ ወገኖችህን ቅጠራቸው” ብሎታል፡፡ /ዳን 9፡22- 25፤ኤር29፡1ዐ/

 

ሰባ ሱባኤ አራት መቶ ዘጠና ዓመት ነው /7ዐX7= 490/ ይህ ጊዜ ከሚጠት እስከ ክርስቶስ መምጣት ያለው ጊዜ ነው /ትርጓሜ ሕዝ፡4፡6/

 

3.ሱባኤ ኤርምያስ፡- ኤርምያስ ከባቢሎን እንደተመለሰ በፈረሰው ቤተ መቅደስ ውሰጥ ሆኖ ሲጸልይ ሳለ ራእይ አየ በሦስተኛው ቀንም እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ፡፡ “ፈጣሪያችንን በአንድ ቃሉ አመስግኑ፤ የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን አመስግኑ፤ ከዚህ በኋላ ሰው ሊሆን ሥጋ ሊለብስ ወደዚህ ዓለም ሊመጣ የቀረው 333 ሱባኤ ዕለት ነውና እርሱ ወደዚህ ዓለም ይመጣል ዐሥራ ሁለት ሐዋርያትንም ይመርጣል…፡፡” ተረፈ ኤር 11፤37 ፣38፣42-48 ኤርምያስ ሱባኤውን የጀመረበትን ትንቢቱን የተናገረበት ራእዩን ያየበት ዘመን ዓለም በተፈጠረ በ5 ሺህ እና 54 ዓመት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ከተነገረበት እስከ ክርስቶስ ልደት ያለው ጊዜ 446 ዓመት ነው፡፡

 

ይኸውም በኤርምያስ ሱባኤ አንዱ 49ዐ ዕለት ነው መላው ሱባኤ 49ዐX333 = 163,170 ዕለት ሲሆን፤ ወደ ዓመት ሲለወጥ 163, 170÷365=446 ዓመት
ኤርምያስ ሱባኤውን መቁጥር የጀመረበት ዘመን፤ …….. 5ዐ54 ዓመተ ዓለም ትንቢቱ ከተነገረበት ዓመት እስከ ክርስቶስ ልደት ……. 446 ዓመት በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት 55ዐዐ ዓመት ሲፈጸም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ በዚህ ይታወቃል፡፡

 

4.ዓመተ ዓለም:- የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱሳት መጻሕፍትን መርምረው ሱባኤያትንና ሰንበታትን አውቀው ከአዳም እስከ ክርስቶስ ያለውን ዘመን ቁጥር 55ዐዐ ዓመት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ይኸውም፡- ከአዳም እስከ ኖኅ 2256 ዓመት፤ ከኖኅ እስከ ሙሴ 1588 ዓመት፤ ከሙሴ እስከ ሰሎሞን 593 ዓመት፤ ከሰሎሞን እስከ ክርስቶስ 1063 ዓመት፤በአጠቃላይ 55ዐዐ ዓመት ነው፡፡

 

ከልደቱ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡ የስብከትና የብርሃንን ሱባኤዎች አልፈን ኖላዊ ከገሃድ/ ጾመ ድራረ በፊት ያለ ሳምንት ነው፡፡
እነዚህ ሳምንታት ነቢያት አምላክ ይህንን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸው እና ይህንን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች እና ጌታችንም ለእነዚህ መልስ የሰጠባቸው ሁኔታዎች ይታሰቡባቸዋል፡፡

 

የመጨረሻው ሳምንት ኖላዊ የቃሉ ፍች እረኛ ማለት ነው፡፡ እረኞች ለበጎቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ሣር ውኃ ሳያጓድሉ እንዲጠብቁ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በነፍስ በሥጋ የሚጠብቅ ቸር እረኛ ነው፡፡ ይኽንን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ሲያብራሩ ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው 14 ትውልድ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ዘመን እሥራኤላውያን ከሀገራቸው ተሰደው በባቢሎን 70 ዘመን ከኖሩ በኋላ ዘሩባቤልን አንግሦላቸው ይዟቸው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ከዚያ በፊት እስራኤል ጠባቂ እንደሌለው መንጋ ተበታትነው ሲኖሩ ነቢያት ከኪሩቤል ላይ የሚገለጥ እረኛቸው እንዲገለጥ የእሥራኤል ጠባቂያቸው ሆይ፣ አድምጥ እያሉ የጠየቁበት መታሰቢያ ነው፡፡ መዝ.79-1-3፡፡

 

መዝሙሩም “ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃሉ እግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ፤ የእግዚአብሔር ልጅና ቃሉ የሆነ ክርስቶስ ከላይ የወረደ ወደ ዓለም የመጣ እረኛ” የሚል ሲሆን የሚነበበው ደግሞ አንቀጸ አባግዕ የተባለው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ ዮሐ.10-1-22፡፡

 

እረኛ የሌለው በግ ተኩላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ከትጉኅ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም በሲኦል አጋንንት በርትተውበት ሲጠቀጠቅ ኖሯል፡፡ እንዲሁም ከመንጋውና ከእረኛው የተለየ በግ እንዲቅበዘበዝ አምላኩን ዐውቆ አምልኮቱን ከመግለጽ የወጣው ሕዝብ በየተራራው መስገጃዎችን እየሠራ የሚታደገውን አምላክ በመፈለግ ሲንከራተት ኖሯል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበር” እንዳለ፡፡ 1ኛ ጴጥ.2-25፡፡

 

ነቢያት በዓለም ተበትነው የሚቅበዘበዙትን ሕዝቡን በቤቱ ሰብስቦ የሚጠብቃቸው እውነተኛ ቸር እረኛ እንዲወለድ ስለተናገሩ ያን ለማስታወስ ሳምንቱ ኖላዊ ተባለ፡፡ ለዚህም ነው የልደትን በዓል ስናከብር “ዮም ፍስሐ ኮነ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ”
“ዛሬ በክርስቶስ ልደት ደስታ ሃሴት ሆነ” የምንለው፡፡
“ዮም፣ ዛሬ” ማለታችን በልደቱ ቀን ከእረኞችና ከመላእክት ጋር ሆነን እንደምናከብር የሚያመለክት ነው፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተነገረው ትንቢት በተቆጠረው ሱባኤ መሠረት /ዓመተ ዓለም ፣ዓመተ ኩነኔ ፣ዓመተ ፍዳ/ አምስት ቀን ተኩል /55ዐዐ ዓመት/ ሲፈጸም /በእግዚአሔር ዘንድ 1ዐዐዐ ቀን እንደ አንድ ቀን ናት፡፡ 2ኛ ጴጥ 3፤8 / በ5501 ዓመት ማክሰኞ ታኀሣሥ 29 ቀን ተወለደ፡፡

 

“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ሥምረቱ ለሰብእ” አምላካችን እየሱስ ክርስቶስ የዘመኑ ፍጻሜ /የገባው ቃል ኪዳን፣ የተነገረው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባዔ/ ሲደርስ ከእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደው ያጣነውን ልጅነት ሊመልስልን፣ ከተቀማነው ርስት ሊያስገባን፣ የገባንበትን እዳ ሊከፍልልን እንደሆነ ሁሉ በየዓመቱ የአምላካችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር በልደቱ ያገኘናቸውን ሀብታት በመጠበቅ፣ የተማርናቸውን ትምህርቶች በመፈጸም እውነተኛ የልደት በዓል ተካፋዮች መሆን ይገባናል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን እረኞች ጋር በአንድ ላይ እንዳመሰገኑ እኛም በዝማሬና በምስጋና በፍፁም ደስታ ልናመሰግን ይገባል፡፡ፍቅሩን እያሰብን በኃጢአታችን ምክንያት ከልባችን ያወጣነውን የሁላችንንም አምላክ ዛሬም በልባችን እንዲወለድ ያስፈልጋል፡፡
“የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት አለ?” ማቴ. 2÷1

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1682--44